06/02/2024
በቡርጂ ከፍተኛ የማዕድናት ክምችት መኖሩ ተገለፀ።
፣ ጥር 27/2016 ዓ.ም በቡርጂ ዞን ከፍተኛ የማዕድናት ክምችት መኖሩን በቡርጂ ዞን የሶያማ ዙሪያ ወረዳ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ግና ገለፁ።
ኃላፊው እንደገለፁት ጽ/ቤቱ በውሃ እና በማዕድን ዘርፍ በትጋት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ማዕድናቱን በአለኝታ ደረጃ ተለይቶ በጥናት ያልተረጋገጡ እና መኖሩን በጥናት የተረጋገጡ በማለት በሁለት መልኩ ከፍለው አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት በጥናት ተለይተው የተረጋገጡ ግሪን ሳፋየር፣ የድንጋይ ከሰል፣ ስሞክኳርቲዝ እና ቤንቶናይት ሲሆኑ ግሪን ሳፋየር የተባለውን የጌጣጌጥ ማዕድን "ዎደ" ማህበር እና "ሠላም" የተባሉ ቡድኖች ለሙከራ በሦስት ወር ውስጥ በተደረገ የማምረት ሂደት ከ182 ሺህ 6ዐዐ በላይ ብር መሸጡን ገልፀዋል።
የድንጋይ ከሰል በጥናት ከተረጋገጡት ውስጥ አንዱ ሲሆን ጴጥሮስ እና ጓደኞቹ ማህበር 11 ሄክታር ቦታ ላይ የማምረት ፈቃድ ተሰጦቶት ለመሬት ባለይዞታ ክፍያ ፈጽሞ በሂደት ላይ መኖሩን ተናግረዋል።
በገምዮ አካባቢ ጥራትና ከፍተኛ ክምችት ያለው የቤንቶናይት ማዕድን እንዳለና ግዛቸው የሚባል አንድ ባለሀብት በ2014 ዓ.ም የቤንቶናይት ማዕድን የማምረት ፍቃድ አውጥቶ ወደ ሥራ ስላልገባ ፈቃዱ ተሰርዞ ሌላ ፍቃድ የጠየቀ ስለሌለ እየጠበቀ ይገኛል።
ሌላው ደግሞ በአለኝታ ደረጃ ተለይቶ በጥናት ያልተረጋገጡ ማዕድናት የብረት ማዕድን፣ ክርስታይል ኦፓል፣ አጌት፣ ፊልድስፓር፣ ብሉ ሳፋየር እና ኢመርላንድ ሲሆኑ በቡርጂ ሌሎችም ማዕድናት ሊኖሩ የሚችሉ አመላካች ነገሮች መኖራቸውን አብራርተዋል።
ኃላፊው በማብራሪያቸው ላይ በአካባቢው የሚገኙ ማዕድናትን በጥናት ለማረጋገጥ በቂ በጀት እንደሚጠይቅ ጠቁመው የዞኑና የወረዳው መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበው በማዕድን ማምረት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ድርጅትችና ማህበራት ቡርጂ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
በአጠቃላይ ከጽ/ቤቱ ከአገኘነው መረጃ መገንዘብ የሚቻለው ጽ/ቤቱ ከሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራሉ አካላት ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሆነና ቡርጂ ላይ በአለኝታ የተለዩ ማዕድናት ጥልቅ ጥናት ለማድረግ በቂ በጀት ተመድበው በዘመናዊ መሳሪያ ክምችቱን መለየት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ይቻላል።
በዞኑ በአለኝታ ጥናት ከተገኙት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ያልተጠቀሱ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ዓይነቶች መኖራቸው ስለተጠቆመ ለማዕድን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።