
08/28/2025
እመን እንጂ ቀላል ነው!
እያንዳንዷን የደስታ ቅጽበት፣ እያንዳንዷን የጭንቀት ሰዓታት የምትፈጥራቸው አንተ ነህ። የአእምሮ ህዋሳቶችህ አዛዥ አንተ ነህ። የስሜቶችህ አብሪ እና አጥፊም አንተው ነህ። እጣ ፈንታህን አንተው ነህ የምትቆጣጠረው።
አጠገብህ ያሉ ነገሮች እና እምነቶችህ አንተ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብህ ከሆነ፣ ልክ እንደ ኮምፒዩተር ፕሮግራም የምታስበውን፣ የምትሆነውን እየሰረዝን እና እየጻፍን መቀየር እንችላለን? ብዙውን ጊዜ ስሜቶች የድርጊቶች ውጤት ናቸው።
የምትከፋውም፣ የምትጸጸተውም ወይም የምትደሰተውም መጨረሻ ላይ ነው። ሆኖም መጨረሻው አስደሳች እንደሆነ በመንገር ብቻ ሰውነትህን ልታሳምነው እና ልታነቃቃው ትችላለህ? ነገ ትድናለህ ስላልከው ብቻ ሰውነትህ ዛሬ ላይ መድኃኒት ብሎ የወሰደው ንጹህ ውሃ ያድነዋል?
ሁሌም ቢሆን መጨረሻ ላይ ስለሚመጣው ውጤት መልካም እሳቤ ካለን መንገዱም ምንም ቢጎረብጥ፣ ጉዟችን መልካም ይሆናል። ህቡዕ አእምሯችን የእውነታውን ዓለም ከሃሳብ ዓለም መለየት አይችልም። እናም ሰውነታችን ነገው ያማረ እንደሆነ ካመነ፣ ዛሬ ላይ ጉልበት ያገኛል፤ ዛሬ ላይ ይደሰታል።
ሰውነትህን በማመንህ ልክ መግዛት እና መምራት ትችላለህ። ሀብታም መሆን ትፈልጋለህ - እንደምትሆን ማመን አለብህ። እንደማትወድቅ ስታምን መውደቅ ታቆማለህ። ደፋር መሆንህን ስታምን - ፍርሃትህ ይተናል። እውነታውን ዓለም መምራት ካለብህ፣ ከውስጥህ፣ ከህቡዕ ህሊና መጀመር አለብህ።
ከተአምረኛው አእምሮህ መጽሐፍ