
26/07/2025
የኢራን ዲፕሎማቶች የኒውክሌር ንግግርን በድጋሚ ለማስጀመር ከአውሮፓ ባለስልጣናት ጋር ተገናኙ
እስራኤል ሰኔ ላይ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ከፈፀመች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራን ዲፕሎማቶች የኒውክሌር ንግግር ለማድረግ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከጀርመን እና ከፈረንሳይ አቻዎቻቸው ጋር ተገናኙ።
የ12 ቀናት ጦርነት ያስነሳው እና አሜሪካ በበርካታ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የቦምብ ጥቃት እንድፈጽም ያደረገው የእስራኤል ጥቃት መከሰቱን ተከትሎ አሜሪካ እና ኢራን ሲያደርጉት የነበረው የኒውክሌር ድርድር በድንገት ተቋርጦ ነበር።
'ኢ3' በመባል የሚታወቁት በድርድሩ ላይ የተሳተፉት ሶስቱ የአውሮፓ ኃያላን ሀገራት፤ አሁን በተጀመረው የኒውክሌር ድርድር ላይ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ ምንም መሻሻል የማይታይ ከሆነ በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ካዜም ጋሪባባዲ "ከባድ፣ ግልጽ እና ዝርዝር" ውይይት ማድረጋቸውን እና ምክክሩን ለመቀጠል መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ጋሪባባዲ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ፤ በኢራን ላይ ማዕቀብ መጣል የሚለውን ሀሳብ መቀስቀስ "ሙሉ በሙሉ ህገወጥ" እንደሚሆን ተናግረው ነበር።
ከዚህ ቀደም በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ የተነሳው፤ በ2015 ቴህራን ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ጀርመን ጋር የኒውክሌር ስምምነት ከፈጸመች በኋላ ነበር።
ይሁን እንጂ አራን የኒውክሌር መሳሪያ ለማምረት ጥረት እያደረገች ነው መባሉን ተከትሎ ለዓመታት የዘለቀ ውጥረት ተፈጥሮ ቆይቷል። ኢራንን ይህንን ክስ አትቀበለውም። በስምምነቱ መሰረት ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን ለመገደብ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች እንዲገቡ ለመፍቀድ ተስማምታ ነበር።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2018 በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ስምምነቱ ኢራን የኒውክሌር ቦምብ እንዳትሰራ ለመከላከል ያደረገው አስተዋጽኦ እምብዛም ነው በማለት ሀገራቸውን ከስምምነቱ አስወጥተው ነበር።
ሁሉም የአሜሪካ ማዕቀቦች በድጋሚ በኢራን ላይ ጥለዋል።
ኢራን በበኩሏ በስምምነቱ የተጣለባትን ገደብ በመጣስ ለዚህ የአሜሪካ እርምጃ የአጸፋ ምላሽ ሰጥታለች።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ፤ ኢራን እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት ውስጥ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመገደብ ካልተስማማች ከባድ ማዕቀቦችን በድጋሚ እንደሚጥሉ ዝተዋል።
አዲሱ ንግግር አርብ ዕለት ከጀመረ በኋላ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፤ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ በቴክኒክ ደረጃ ውይይቶችን እንደገና ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ጠቁማለች ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ራፋኤል ግሮሲ አክለውም ኢራን ስለ ተቋማቷ እና ስለ እንቅስቃሴዎቿ ግልጽ ልትሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
"የሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ምን መሆን አለባቸው የሚለውን በተመለከተ ኢራንን ማዳመጥ አለብን" ብለዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ፤ የኢ3 ሀገራት ስብሰባውን "የቀድሞውን ገንቢ ያልሆነ ፖሊሲያቸውን ለመካስ" ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ ለሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ሶስቱም ሀገራት ሰኔ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል ያደረሱትን ጥቃት በመደገፍ "ለህግ ጥሰት እና ጥቃት" አመክንዮ ሲሰጡ ነበር በማለት የከሰሱት ቃል አቀባዩ፤ ኢራን በአሁኑ በሚካሄደው ውይይት ላይ ይህንን ድርጊት በመቃወም አቋሟን እንደምታሳውቅ ጠቅሰዋል።
የኢራን ፓርላማ ሰኔ ላይ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር የተፈጠረው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ሀገሪቱ ከተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት ጋር ያላትን ትብብር ማቋረጡ ይታወሳል።
BBC