Hiber Radio

Hiber Radio Hiber Radio , Las Vegas live every Sunday on www.hiberradio.com,Hiber Radio app or by phone 7124328451 and 24/7 you can listen

Hiber Radio , Las Vegas live every Sunday 6;30PM on www.KRLV1340AM.com, 1340 radio Channel or and 24/7 on www.hiberradio.com

ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 6፤30 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በ1340 ኤ.ኤም የአየር ሞገድ ወይም በድህረ ገጽ በቀጥታ በአይቱን www. KRLV1340AM.com ይደመጣል። በስልክ ለማዳመጥ ለሚቀናችሁ በቀጥታ
በአዲስ ቁጥር 712 432 8451 ያለ ኮድ በቀላሉ ማዳመጥ ይቻላል። (9፡30 በዋሽንግተን ሰዓት ) ህብር ሬዲዮ_የወቅታዊ መረጃ ምንጭ።

መልዕክተ ቅዳሜህዝብ እና እንቢተኝነት፤ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (Civil Disobedience)ክፍል ሁለት++++++++++++“The time has come, or is about to come, wh...
08/16/2025

መልዕክተ ቅዳሜ

ህዝብ እና እንቢተኝነት፤ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (Civil Disobedience)
ክፍል ሁለት
++++++++++++

“The time has come, or is about to come, when only large-scale civil disobedience, which should be nonviolent, can save the populations from the universal death which their governments are preparing for them.”

Bertrand Russell

ባለፈው ሳምንት ጀምሬ ያልቋጨሁትን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ላይ ያተኮረውን ዳሰሳዬን ክፍል ሁለት ቃል በገባሁት መሠረት እንሆ ለንባብ ይዤ ብቅ ብያለሁ፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ሕዝባዊ እንቢተኝነት በቅርቡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያለውን ቦታ፣ የጽንሰ ሐሳቡን ትርጓሜ፣ አንዳንድ ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት እና ውይይት አጫሪ ይሆናሉ ያልኳቸውን ጥያቄዎች ለአንባቢያን በማቅረብ ነበር ያቆምኩት፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ለለውጥ ዋነኛ መሣሪያ ተደርጎ እንዲወሰድ ፈቃጅ ወይም መነሻ የሚሆኑትን ምክንያቶች፣ የአንዳንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ በሚገኙ አገራት የሕዝባዊ እምቢተኝነት ተመክሮ ምን እንደሚመስል እና ሰላማዊ የሆነ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ዛሬ ላለንበት አጣብቂኝ ምን ሊፈይድልን ይችላል በሚሉት ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ፡፡

ለማስታወስ ያህል ሕዝባዊ እንቢተኝነት ወይም civil disobedience የተሰባሰቡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አስበውበት፣ ተመካክረው እና የሕግ ወይም የፖሊሲ ወይም ከፍ ሲልም የመንግስት ለውጥን ታሳቢ በማድረግ ለጋራ አላማ ሲባል ኢ፟፟-ፍትሐዊ ያሉትን የመንግስትን ሕግ ወይም ፖሊሲ ወይም መመሪያ አንቀበልም በማለት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያምጹበት የትግል ሂደት ነው፡፡ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በብዙ መልኩ ሊገለጽ የሚችል ሲሆን በዋነኝነት ግን ከዚህ በሚከተሉት መንገዶች ሊከወን ይችላል፡፡

1ኛ/ የተቃውሞ ሰልፎች (protests) ፤ በአደባባይ የሚካሄዱ ሰልፎች፣ አንድ ቦታ ላይ ተወስኖ የሚደረግ ቆይታ ወይም የሚተላለፉ የአደባባይ ምልዕክቶች ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ በታወቁ የሕዝብ አደባባዮች ወይም ጎዳናዎች ወይም ከአንድ መልዕክቱ እንዲደርሰው ከተፈለገ መንግስታዊ አካል ቢሮ ፊት ለፊት ወይም ሕዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው መናፈሻዎች ወይም ሌሎች የብዙ ሰውን ትኩረት ሊስቡ በሚችሉ ስፍራዎች ሊካሄድ ይችላለል፡፡ በአደባባይ ቅሬታን ወይም ተቃውሞን መግለጽ በአገራችን ሕገ መንግስትም ሆነ በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እውቅና እና ጥበቃ የተደረገለት መብት ነው፡፡ ለዜጎች ደህንነት ሲባል ተገቢውን ጥበቃ መንግስት ሊያደርግ ቢችልም በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር የአደባባይ ተቃውሞ ሰልፎችን ለመገደብ ወይም ለመከልከል የሚያስችል ምንም አይነት ሥልጣን የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ሕጎችም የአደባባይ ተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ ከ72 ሰአታት በፊት ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ግዴታ እንደሆነ የሚደነግጉት ደንቦች መነሻቸውም መንግስት በቂ ሃይል መድቦ ሰልፈኞቹንም ሆነ የተቀረውን ማህበረሰብ ከማናቸውም ጉዳቶች ለመጠበቅ ነው፡፡ ይሁንና ይህን የሕግ መንፈስ ሆን ብሎ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ማሳወቅ የሚለውን ማስፈቀድ ግዴታ እንደሆነ ተደጎ በባለሥልጣናት ስለሚወሰድ መንግስትን ከሚደግፉ ሰልፎች በስተቀር ላለፉት በርካታ አመታት በአገሪቱ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም፡፡ ይሄኔ ነው ሕዝባዊ ተቃውሞ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ የሚመጣው፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ የተከለከሉ ሰዎች ወይም ቡድኖች ማንንም ማስፈቀድ ብቻ ሳይሆን ማሳወቅም ሳይጠበቅባቸው ሰልፍ በመውጣት ድምጻቸው እንዲሰማ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ሌላው ጥያቄ መንግስት ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል ቢጠቀምስ? ቢያስረን፣ ቢገድለን፣ ቢከሰን ወይም ሌሎች እርምጃዎች ቢወስድስ የሚሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን ተወካይ በቅርቡ ፓርላማ ድረስ ቀርበው ሠራተኛው እየተራበ ነው፣ ልጆቹን የሚያበላው አጥቶ ከሥራ ሲወጣ ፌስታል ይዞ ከየሆቴሉ ትራፊ ይለመና የሚሉና ሌሎች ሰቅጣጭ ሁኔታዎችን በመግለጽ የደሞዝ ግብሩ ከዝቅተኛ ደሞዝ ካላቸው ሰራተኞች ላይ እንዲነሳላቸው ቢጠይቅም ፓርላማው ተማጽኖውን ወደጎን በመተው ሕጉን አጽድቆታል፡፡ እንግዲብ ይህን ተከትሎ የሠራተኞቹ ማህበር ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፍ ቢጠራ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ይቻላል፡፡

2ኛ/ አንድን የመንግስት ተቋም ወይም አካል በቁጥጥር ሥር ለተወሰኑ ጊዜያት ማዋል (Occupations)፤ ይሄም ሌላው አይነት የተቃውሞ መንገድ ሲሆን ብዙ አገሮች፤ በተለይም የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሥርአት ባለበት አገር ተደጋግሞ የሚከሰት ክስተት ነው፡፡ ከተወሰኑ አመታት በፊት በአሜሪካ ሕግ አውጪው ምክር ቤት ላይ ህንጻውን ከበው ከቆዩ በኋላ በሩን ሰብረው በመግባት ምክር ቤቱን ለተወሰኑ ሰአታት ተቆጣጥረው የነበሩ ሰዎች የፈጸሙት የተቃውሞ አይነት ነው፡፡ በዛው በአሜሪካ በ2011 እኤአ ለ58 ቀናት Occupy Wall Street በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የኒዮርክ ከተማን አስጨንቀው የከረሙበት ተቃውሞም አንዱ የቅርብ ምሳሌ ነው፡፡ የአረብ እስፕሪን እየተባለ ይሚታወሰውን ሕዝባዊ ሱናሜ የታየበት የታህሪሪ አደባባይ የቀናት አመጽ በዚህ የተቃውሞ ዘርፍ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በቅርቡም በኬኒያ በአንድ ፍርድቤት ላይ ወጣቶች ዳኞቹን ከበው ከችሎት እንዳይወጡ በማገድ የፈጸሙት የሕዝባዊ ተቃውሞ ወይም እምቢተኝነት አይነት ነው፡፡ እንግዲይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ በነቂስ ወጥቶ የከንቲባዋን ቢሮ ቢከብ ወይም የመስቀል አደባባይን ለቀናት ቢቆጣጠር ብላችው አስቡት፡፡

3ኛ/ ያለመታዘዝ ወይም በሕግ የተጣለን ግዴታ ያለመወጣት (Noncompliance)፤ ይህ አይነቱ መሰረታዊ የሆነ የህዝብ የመብት ጥያቄ እስኪመለስ፣ የተጓደለው ፍትህ እስኪቃና፣ አጥፊዎች ለፍርድ እስኪቀርቡ፣ ምንግስት ኢፍትሐዊ የሆነውን ፖሊሲ ወይም ሕግ ወይም የአፈጻጸም እርምጃ እስኪያሻሽል ወይም እስኪቀይር ድረስ ለሕግ አንታዘዝም የሚል የተቃውሞ እርምጃ ነው፡፡ ለዚህም ብዙውን ጊዜ ተጠቃሽ የሚሆነው በአድማ ግብር አልከፍልም ብሎ ለመንግስት የሚገባውን ገንዘብ የመከልከል እርምጃ ነው፡፡ Thoreau’s protest to pay taxes በአሜሪካ ሰዎችን በባርነት የማስተዳደር እርምጃ እንዲቆም ግብር አንከፍልም በማለት ያካሄዱትና በ1960 ዎቹ አሜሪካ ከቬትናም ጋር ያካሄደችውን ጦርነት ተከትሎ ለተደረገው የውትድርና ጥሪ ብዙ ጥቁር አሜሪካዊያን አንዘምትም በማለት ያደረጉት ተቃውሞ እና ሌሎችም በየጊዜው የተደረጉ ተቃውሞዎች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ የቬትናም ዘመቻን በመቃወም በተደረገው አመጽ ላይ ታዋቂው ቦክሰኛ ሞሃመድ አሊ የተናገረው ድንቅ ንግግር ሁሌም ከሕዝባዊ እንቢተኝነት ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል፡፡ ቦክሰኛው ሞሃመድ አሊ እንዲህ ነበር ያለው፤ “Why should they ask me to put on a uniform and go 10,000 miles from home and drop bombs and bullets on Brown people in Vietnam while so-called Negro people in Louisville are treated like dogs?” በአገራችን በሚካሄዱ ጦርነቶች ቻል ወንድም ከወንድሙ ስለሆነ የሚገዳደልወ “ወንድሜን ልገድል አልዘምትም” የሚል ንቅናቄ ቢኖርና መከላከያን ጨምሮ ሁሉም ሃይል ለእርስ በርስ ጦርነት አልዘምትም ብሎ ቢያምጽ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስኪ አስቡት፡፡
4ኛ/ የተከለከሉ ነገሮችን ማድረግ (Targeted defiance)፤ ይህ አይነቱ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ከላይ እንዳለው በሕግ ላይ አምጾ በመንግስት የተሰጠን መመሪያ ወይም በሕግ የወጣ ትዕዛዝን አልፈጽምም በማለት ከሚደረግ ተቃውሞ (noncompliance) ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ቢኖረውም ይሄ ግን አንድ ደረጃ በመሄድ ሕጉን የሚጥሱ ሌሎች ሕገ ወጥ ሊባሉ የሚችሉ ድርጊቶችን መፈጸም ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚቦነው በአሜሪካ የጥቁሮች ነጻነት ትግል ላይ ተደጋግሞ ሲተገበር የነበረ ስልት ሲሆን whites-only በሚል ተለይተው ነጮችን ብቻ የሚያስተናግዱ ሱቆች እና መዝናኛ ቤቶች ውስጥ ገብቶ በግዳጅ መገበያየት፣ ነጮች ብቻ እንዲቀመጡበት በታዘዘ የአውቶቢስ የፊት ወንበር ላይ ተቀምጦ አልነሳም ማለት፡፡ ይህ አይነቱ እርምጃ ሆን ተብሎ ማህበረሰብን ለማግለል በተወሰዱ የመንግስት ፖሊሲዎች ወይም ሕጎች ላይ ትኩረት ያደረገ የአመጽ ወይም የእምቢተኝነት መግለጫ መንገድ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹ እነዚህን እርምጃዎች ሲወስዱ ዋነኛ አላማቸው በቂ የሆነ የሕዝብ ትኩረት መሳብ እና በትግሉ ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ መስቀል አደባባይ እንደ ቀድሞው ማንም ሰው በፈለገ ሰአት ሄዶ በነጻ የሚዝናናበት፣ እስፖርት የሚሰራበት ወይም ቁጭ ብሎ የሚውልበት ቦታ አይደለም፡፡ በአደባባዩ ግራና ቀኝ ላይ በሚደረጉ ቁጥጥሮች የተነሳ ዜጎች በነጻነት ቦታውን አይጠቀሙበትም፡፡ ይህን አሰራር ትክክለኛ አይደለም የሚሉ ተቃውሞዎች አይቻለሁ፡፡ የከተማው ሕዝብ ግልብጥ ብሎ አንድን ቅዳሜ መስቀል አደባባይ አሳልፋለሁ ቢሊ እና በእንቢተኝነቱ ጸንቶ በመቶ ሺዎች ወደ አደባባዩ ድንገት ቢጎርፉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ በርካታ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ማሳያ የሆኑ መንገዶች አሉ፡፡ በተለይም በዚህ በድህረ መረብ ዘመን ሰዎች ድምጻቸውን፣ ቁጣቸውን፣ ሕዝባዊ ተቃውሟቸውን በአደባባይ በማሰማት በርካታ የመንግስት ኢፍትሃዊ ሕጎችን እና ፖሊሲዎችን ሲያስቀይሩና መጥፎ የሚባሉ መንግስታዊ አስተዳደሮችን ሲያርበደብዱ ታዝበናል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አንድ አይነት መልዕክት ለአንድ የመንግስት አካል ወይም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በመላቅ ቢያስጨንቁና ቢያጥለቀልቋቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ይቻላል፡፡

የ1930 እኤአ የህንዱ ሰላማዊ ታጋይ ማህተመ ጋንዲ የመሩት እንግሊዞች የጫኑባቸውን ኢፍትሃዊ የሆነ የጨው ዋጋ በመጋወም ያካሄዱት የአንድ ወር ተቃውሞ ሰልፍ እና ቆይቶም ሚሊዮኖችን ያስከተለው የጨው ሕግን የመታስ ንቅናቄ ቆይቶ ህንድን ከእንግሊዞች ቅኝ ግዢ ነጻ አውጥቷታል፡፡ በ1955 ጥቁር አሜሪካዊቷ Rosa Parks የአውቶቢስ ውስጥ ለነጮች ቅድሚያ ወንበር የሚሰጠውን የአልባማ ስቴት ሕግ በመጣስ ቀድማ የያዘችውን መቀመጫ ለነጭ ተሳፋሪ ልቀቂ ስትባል እምቢኝ፣ እኔም ሰው ነኝ፣ ሕጉን አላከብርም በማለት ያቀጣጠለችው እምቢተኝነት እሷን ለእስር ቢዳርጋትም የማይቀለበስ ሕዝባዊ የለውጥ አመጽ ለመቀጣጠል ምክንያት ሆና ህጉ እንዲሻር አድርጋለች፡፡ በ1964 ጎልምቶና ተቀጣጥሎ የወጣው የአሜሪካ Civil Rights Movement በአገራቸው የመምረጥ እድል እንኳ ያልነበራቸው ጥቁር አሜሪካዊያን ፕሬዚደንት እስከመሆን ያደረሳቸው የሮሳ ፓርክ የአውቶቢስ ላይ እምቢተኝነት ነው፡፡

የአለምን የማራቶን ሩጫ ጽዎታዊ ገደብ ታሪክ አድርጋ ያስቀረችው Kathrine Switze በቦስተን ማራቶን ላይ በ1967 የወሰደችው እርምጃ እንዲሁ የአለምን ታሪክ ከቀየሩ የሕዝባዊ እምቢተኝነት መገለጫ ታሪክ አካል ነው፡፡ ሴቶች በማራቶን ላይ እንዳይሳተፉ በቦስተን ማራቶን በተጀመረ ጊዜ በ1897 የተቀመጠውን ጾታዊ ገደብን የሚያጸናውን ሕግ በመተላለፍ ከተሳተፈች በኋላ በቀሰቀሰችው ንቅናቄ በ1972 የቦስተን ማራቶን ህግ ተቀይሮ ሴቶች በጠቅላላ መሳተፍ እንዲችሉ አድርጋለች፡፡

ሕዝባዊ እንቢተኝነት ከየትኛውም በግዳጅ መንግስታዊ ለውጥ ከሚመጣችባቸው በርካታ መንገዶች መካከል ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን ለማጽናትና ጊዜ የማይሽራቸው የለውጥ መሰረቶችን ለመጣል ተመራጭና በፖለቲካ ለውጥ ወቅት በሚቀሰቀሱ ግጭቶችና ውጥረቶች ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ ህይወትና በንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን በማስቀረት ወይም በማሳነስ ትልቅ ሚና እንዳለው ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ወደ አገራችን ሁኔአ ስንመለስ፤ የሚነሱት ጥያቄዎች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡

1ኛ/ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተመራጭ እና የሚቻል የትግል መንገድ ነው ወይ?

2ኛ/ ትግሉን ማን በባለቤትነት ሊያቅደው፣ ስልቶቹን ሊነድፍ፣ እንቅስቃሴውን ሊጠነስስ፣ ሕዝብን ሊያነቃና ሊያስተባብር፣ አቅጣጫ ሊመራ ይችላል? ይህን አይነት ትግል ለመምራት የሚያስችል ቁመና ያለው፣ በሕዝብ ዘንድ የሚታመን አካልስ አለ ወይ?

3ኛ/ ምን አይነት ግቦችን የያዘ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ቢካሄድ ነው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ክልል፣ ሃይማኖት፣ ጾታ ወይም ሌላ ክፍፍሎችን በማያጎላ መልኩ ሁሉንም በአንድ መንፈስ በጋራ ሊያሰልፍ የሚችለው?

እነዚህ ጥያቄዎች ተወያዩባቸው፡፡

በቀጣዩ ሳምንት እና የመጨረሻ ክፍል በሆነው በዚህ ርዕስ ዙሪያ በማካፍለው ጽሑፌ ከላይ ያነሳኋቸውን ጥያቄዎች በመመለስና ለእኔ የሚያዩኝን አማራጭ መንገዶች በማቅረብ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ዙሪያ የሚያተኩረውን ጽሁፌን እቋጫለሁ፡፡

መልካም ቅዳሜ!
ያሬድ ኃ/ማርያም የቀድሞው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች
Yards Hailemariam

ከጉሊት ግዙ!
08/16/2025

ከጉሊት ግዙ!

Address

Las Vegas, NV

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Hiber Radio posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share