12/30/2025
በዓመት ከ2 ሚ. ብር በላይ የሚያገኙ ቲክቶከርና
ዩቲዩበሮች ግብር እንደሚከፍሉ ተገለጸ
*ከ2 ሚ. ብር በታች ገቢ ማግኘታቸው ከገቢ ግብር ነጻ አያደርጋቸውም
እንደ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ ካሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያገኙ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች፤ እንቅስቃሴያቸው "በንግድ ሥራነት" ተቆጥሮ ግብር እንዲከፍሉ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ ደንብ፤ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች "ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰርሺፖችን" ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ያገኙትን "ሁሉንም የገቢ መጠን" የሚያሳይ "የሂሳብ መዝገብ" እንዲይዙ ያስገድዳል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ለማይባሉ ወጣቶች የገቢ ምንጭ በሆነው የዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ ላይ ታክስ የሚጣልበት ሁኔታ በዝርዝር የተቀመጠው የገንዘብ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የገቢ ግብር ረቂቅ ደንብ ነው።
የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የገቢ ግብር ከፋይ ዝርዝር ውስጥ የገቡት ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2017 ዓ.ም. በጸደቀው "የገቢ ግብር አዋጅ" ነው። አዲሱ ረቂቅ ሕግ፤ በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ነው። ከአምስት ወራት በፊት የጸደቀው አዋጅ፤ ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ ገቢ የሚያገኝ "አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅቶች" ግብር መክፈል እንዳለባቸው ደንግጓል።
'የዲጂታል ይዘት ፈጣሪ' በሚባለው ዝርዝር ውስጥ እንደ ዩትዩብ እና ቲክቶክ ያሉ "የቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎቶችን" እንዲሁም እንደ ፌስቡክ ያሉ "የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን" ተጠቅመው ገቢ የሚያገኙ ግለሰቦች ተጠቅሰዋል።
"የድምጽ ማስተላለፊያ (ፖድካስት)" እና "የቀጥታ ሥርጭት መድረኮች" ላይ ገንዘብ የሚሠሩ አካላትም እዚህ ውስጥ እንደሚካተቱ አዋጁ ያስረዳል።
ግብሩ የሚከፈለው እነዚህ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች "በኦንላይን መድረኮች ላይ የዲጂታል ይዘትን በመፍጠር እና በማሠራጨት" ከሚያገኙት "ማንኛውም ገቢ" ላይ እንደሆነም ተጠቅሷል። ይህ ገቢ "በጥሬ ገንዘብ ወይም በዓይነት የሚገኝ" ሊሆን እንደሚችልም ያስገነዝባል።
"ማስታወቂያዎች እና ስፖንሰርሺፖች" እንዲሁም "የገንዘብ ስጦታዎች እና የብዙኃን የገንዘብ ማሰባሰብ" ግብር ከሚከፈልባቸው የገቢ ምንጮች መካከል ተጠቅሰዋል።
ይዘት ፈጣሪዎች "በማስተዋወቂያ እንቅስቃሴ ምትክ" ከሚያገኟቸው "ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች" እንዲሁም ከሚፈጽሟቸው "የምርት ስም ስምምነቶች እና ድጋፎች" ግብር እንዲከፍሉ በአዋጁ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ግብር የሚከፍሉት ከምን ያህል ገቢ ጀምሮ የሚያገኙ ይዘት ፈጣሪዎች እንደሆነ የተገለጸው ደግሞ አሁን በተዘጋጀው የገቢ ግብር ረቂቅ ደንብ ነው። ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገንዘብ "የንግድ ሥራ ገቢ" እንደሆነ ተቆጥሮ ግብር እንዲጣልበት የሚያደርጉ ሦስት ሁኔታዎች ረቂቁ ላይ ተቀምጠዋል።
የመጀመሪያው ሁኔታ ከይዘት ፈጣሪዎቹ ዓመታዊ ገቢ ጋር የተያያዘ ነው። የይዘት ፈጣሪው "ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ" ተግባሩ እንደ 'ንግድ ሥራ ገቢ' ተቆጥሮ ግብር ይከፈልበታል።
"በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማራው ግብር ከፋይ በድርጅት መልክ የተቋቋመ" ከሆነም የንግድ ሥራ ገቢ ግብር እንዲከፍል ይገደዳል። ይዘት ፈጣሪዎች በዚህ ምድብ ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርገው ሌላኛው ሁኔታ ደግሞ "ግብር ከፋዩ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ወይም ተቀናሽ ወጪ ያለው ከሆነ" የሚል ነው።
ይዘት ፈጣሪዎች በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር በታች የሆነ ገቢ ማግኘታቸው ወይም እንደ ድርጅት አለመቋቋማቸው ግን ከገቢ ግብር ነጻ አያደርጋቸውም። እነዚህን ሁኔታዎች የማያሟሉ ከሆነ "ሌሎች ገቢዎች" በሚለው ምድብ ውስጥ ገብተው "ከጠቅላላ ገቢያቸው 15 በመቶውን" የመክፈል ግዴታ እንደሚኖርባቸው ባለፈው ዓመት ለጸደቀው አዋጅ የተዘጋጀው ማብራሪያ ላይ ተገልጿል።
"የንግድ ሥራ ገቢ ግብር" የሚለው ምድብ ውስጥ የሚገቡ ይዘት ፈጣሪዎች ከገቢ መረጃ እና መዝገቦች ጋር የተያያዙ ግዴታዎች በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ይጣልባቸዋል።
ቢቢሲ -