09/19/2025
የ1860ዎቹ የሰቆጣ መድኃኒ-ዓለም አርክቴክት፤ ስዊዛዊ!
በ1860ዎቹ መጨረሻ አካባቢ "Reputed Capital of Lasta" የተባለችውን ሰቆጣ ተላምደው ቋሚ መኖሪያቸውን ካደረጓት አውሮፓውያን ተጓዦች መካከል ሚስተር "ዱቦይስ" የተባለ ስዊዘርላንዳዊ ይገኝበታል። ከእርሱ በኋላ ሰቆጣን የጎበኘው ፈረንሳያዊ "አሽል" በጉዙ ማስታወሻው እንደጠቀሰው "ዱቦይስ" የአገውኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ስለመቻሉ፤ በሰቆጣ መደበኛ ኑሮውን እየገፋ እንደነበር፤ በኋላም የነበረውን የኪነ-ሕንፃ አቅም የተገነዘቡት ዋግሹም ተፈሪ ወሰን ግዙፍ ቤተ-ክርስቲያን እንዲያንፅላቸው እንዳዘዙት አትቷል።
በዚያን ወቅት ሰቆጣን የጎበኘው ፈረንሳዊው አሳሽ አሺል እንዳሰፈረው፣ ዱቦይስ የኪነ-ሕንፃ ሰው ብቻ አልነበረም፤ የአውሮፓ ተጓዦች ሰቆጣንና ዕሴቷን እንዲተዋወቁ የሚረዳቸው አስጎብኚም ጭምር እንጂ። ዱቦይስ በወቅቱ በጣም ግዙፍና ቄንጠኛ የተባለውን የመድኃኒ-ዓለም ቤተ-ክርስቲያን የአውሮፓን እደ-ጥበብ፤ ከአገዋዊ የኪነ-ሕንፃ ልማዶች ጋር በማስማማት እውን አድርጓል።
በአሽል ሐተታ "ተቀዳሚዋ የኢትዮጲያ የንግድ ማዕከል" ተብላ የተጠቀሰችው ሰቆጣ ከንግድ ባሻገር የኪነ-ሕንፃ መናኸሪያም ነበረች። በርካታ ተጓዦች እንደጠቀሱት የዋግ-ላስታ ካፒታል የነበረችው ሰቆጣ በፖርቹጋል አርክቴክቶች የተገነባ ባለ ሁለት ፎቅ ቤተ-መንግሥት ባለቤትም ነበረች። ኦግስተስ ዋይልዲ ደግሞ በ1889 ዓ.ም በሰቆጣ በነበረው ጉብኝት በከተማዋ በህንድና ፋርስ መጋረጃና ምንጣፍ ካሸበረቀው ቤተ-መንግሥት በተጨማሪ ከ300 በላይ ፎቅ ቤቶች [ሕድሞ] መመልከቱን ገልጿል። ይህ ተጓዦችን በኢትዮጵያ ከጎበኟቸው እንደ ዓድዋ፣ አክሱም፣ እንጣሎ፣ ጎንደር ከተሞች በላቀ ቄንጠኛና ስልጡን ከተማ እንደሚያደርጋት እንዲመሰክሩ አድርጓቸዋል።
አሽል ከሰቆጣ በስተ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ለ2 ሠዓት በመጓዝ የአገው ነገሥታትን ]የዋግሹሞችን] መካነ-መቃብር የሆነ ቤተ-ክርስቲያን እንደጎበኘ የጠቀሰ ሲሆን፤ ይህ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ግዙፍ የግራናይት ተራራ ተጠርቦ የተሰራ አስደናቂ ቅርጽ ያለው መየአገው ሕዝብን የኪነ-ሕንፃ አቅም የሚያሳይ ነው ብሎታል። ተጓዡ "በአገው ተራሮች መካከል" በሚል ርዕስ በሰጠው የ30+ ገፅ ሐተታ ከተምቤን፣ ሳቃ፣ ሰቆጣ፣ ቡግና፣ ስድቭ፣ ዳህና እና አዲአርቃይ ባደረገው ጉዞ ያየውንና የገጠመውን ሁሉ ከትቧል።
ከስር ያያዝኩት የዱቦይስ የሰቆጣ መድኃኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን ንድፍ ከታሪካዊ ማስታወሻነት ባለፈ የአገው መሪዎችን ዓለማቀፍ ግንኙነትና የማኅበረሰቡን እንግዳ አላማጅነት የሚያሳየን የምልሰት ንድፍ ነው።
ብሩክ ሙላት
መስከረም 9 ፡ 2018፤ አዲስ አበባ!