
07/25/2025
“ወደ ማዶ”
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ30 የአለም ሀገራት መድረኮች የሚታይ ወደ ማዶ" አለም አቀፍ የትያትር ጉዞ ሊጀመር ነው
በኢትዮጵያ የትያትር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ30 የአለም ሀገራት መድረኮች የሚታይ ወደ ማዶ" አለም አቀፍ የትያትር ጉዞ ሊጀመር እንደሆነ የትያትሩ አዘጋጆቹ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አንጋፋ ተዋንያን የሚተውኑበት ይህ "ወደ ማዶ" የተሰኘው ትያትር በውጭ ሃገር መድረክ እንደሚመረቅም ተገልጿል፡፡
ይህን እስካሁን ባልተለመደ መልኩ በ30 አለም አቀፍ መድረኮች የሚታይ ትያትርን ፕሮዲውስ ያደረገው ዋካ ፕሮሞሽንና ኢቨንት ነው፡፡
"ወደ ማዶ" የተሰኘው እና ኮሜዲ ዘውግ ያለው ትያትር ን ለመስራት ብዙ አመታትን የፈጀ ሲሆን በትወና ብቃቷ ከፍተኛ የተመልካች ፍቅርና አድናቆት ያላት ሃረገወይን አሰፋን ጨምሮ ሸዋፈራው ደሳለኝ እና የኋላእሸት ዘሪሁን ይተውኑበታል፡፡
በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ተደርሶ በሴም አማኑኤል የተዘጋጀው "ወደ ማዶ" ትያትር ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሳ የሚሄድ፤ ሲሆን በሕይወታችን የሚገጥሙን ችግሮች ለማውጣት የሚደረግን ትንቅንቅ የሚያሳይ ነው፡፡
ወደ ማዶ" አለም አቀፍ የትያትር ጉዞ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ አህጉራት በሚገኙ ሀገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ30 በላይ መድረኮች ይታያል ተብሏል፡፡
የትያትሩ ይፋዊ የመክፈቻ መርሃ ግብር ታላላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የጥበብ ወዳጅ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በነሐሴ ወር በአፍሪካ የተለያዩ ሃገራት ይደረጋል፡፡
በተጨማሪም እስካሁን ባልተለመደ መልኩ ትያትሩ በሚታይባቸው ሀገራትና መድረኮች ከትያትሩ ጎን ለጎን ለ"የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል" የገቢ ማሰባሰቢያ እንደሚካሄድም ተነግሯል፡፡ ይህንንም በጎ አላማ ለማሳካት ከማዕከሉ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ትያትሩን ፕሮዲውስ ያደረገው ዋካ ፕሮሞሽንና ኤቨንት በኪነ ጥበቡ ሰፊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የረጅም ጊዜ ልምድ የካበተ ሲሆን ትያትርና ፊልሞችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡