10/23/2024
የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በአገው ህዝብ ላይ የሚደርሰው መከራና የማያባራ ስቃይ ልያበቃ ይገባል ስል ጠየቀ።
የአገው ብሄራዊ ሽንጎ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በፃፈው ደብዳቤ፣ በአገው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን በደልና አሰቃቂ ተግባር እንዲያስቆሙልን ስል ጠይቋል።
የአገው ብሄራዊ ሽንጎ በአገው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን በደልና አሰቃቂ ተግባር በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ እካላት ስያሳውቅ መቆየቱን ገልጿል።
ይሁን እንጂ በህዝባችን ላይ የሚደርሰው በደል እየቀነሰ ከመሄድ ይልቅ አሁንም እየተባባሰ መጥቷል ብሏል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርቲዎች ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ ከሸንጎው መሪ ለቀረበለት ጥያቄና ሮሮ ሲመልሱ የአገው ህዝብ ጥያቄ የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የአገው ፓርቲዎች እውነተኛውን ምክንያት መሬት ወርደው ከህዝቡ እንዲያረጋግጡ አቅጣጫ መስጠታቸውን የገለፀው ደብዳቤው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአገው ህዝብ በተለይ ወጣቱ ላይ ግልፅ ጦርነት መታወጁን አስረድቷል።
የአማራ ክልል መንግስት ያለ አገው ህዝብ ፍላጎት የሾማቸው የአዊ አገው ምድር የዞን አመራሮች የፋኖን አላማ እንደሚደግፉ በመግለፅ የክልልነት ጥያቄ የሚያቀነቅን ሁሉ ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ በመዛት በኛ መቃብር ላይ ነው አገው ክልል የሚሆነው ማለታቸውን የአገው ሸንጎ በደብዳቤው ገልጿል።
ይሄ ሁሉ የሚፈፀመው የአገው ህዝብ ዕንፈኛውን ፋኖ በመቃወም ከመንግሥት ጎን በመቆሙ ምክንያት መሆኑንም አስረድቷል።
ለዚህም ማረጋገጫው በክልሉ የሚታዘዘው አድማ ብተና በእዊ ምልስ ልዩ ኃይል ደግሞ በአዊና በዋግ ኽምራ ዞኖች በአገው ወጣቶችና ባለሃብቶች ላይ የሚፈጽሙት ግፍ በቂ ማስረጃ መሆኑን ገልጿል።
የአዊ ዞን አስተዳዳር የአገውን የክልል ጥያቄ ለማዳፈን በዞኑ የአገውን ወጣትና የነቁት ዜጎች መግደል ማሰርና ማሳደድ መቀጠሉን ደብዳቤው ገልጿል።
ይሄን ደብዳቤ ፕሪንት እያደረግን ባለንበት ሰዓት በአገው ህዝብ ተወዳጅና ተደማጭ የሆኑ በአዊ አገው ምድር ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ለፌደራል ፍትህ ሚኒስትርና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለማቅረብ በህዝቡ ተወክለው የመጡ አገዎችን የሚያስሱት መልክተኛ ፖሊሶች አያት አካባቢ ዶክተር መዝገቡ ቦጋለና ቀሲስ ስንታየሁ የኔአባትን ለመያዝ ተንቀሳቅሰው ዶክተር መዝገቡ ሲያመልጣቸው ቀሲስ ስንታየሁን ይዘውት አስረዋል ብሏል።
ጥቅምት 6/2017 በአዊ ዞን በቻግኒና ዚገም ከተሞች በክልሉ አድማ ብተና በተደረገው የጅምላ እስር 17 ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም በ2016 ክረምት የቋራ አገዎች ላይ ከፍተኛ ግፍ ተፈጽሞባቸው በቂ የዕለት ደራሽ እርዳታ እንኳን እጥተው ወደ ከተማ ገብተው እንዳይጠለሉ በጽንፈኛው ኃይል መከልከላቸውን የአገው ሸንጎ ገልጿል።
ከመስከረም 25 እስከ 30/2017 በቋራ አገዎች ላይ በተደረገ ጭፍጨፋ 45 ሰዎች በአሰቃቂ ግፍ ተገድለው 9 ሴቶች በባሎቻቸውና በወላጆቻቸው ፊት በአደባባይ ተደፍረው የቁም እንስሳ በሙሉ ተዘርፎ ቤታቸው ተቃጥሎ ዳግመኛ ህዝቡ በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛል ነው ያለው የሸንጎ ደብዳቤ።
እንዲሁም በዋግ ኽምራና በቅማንት ህዝሁን ለማጥፋት የሚካሄደው እንግልት እጅግ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን ደብዳቤው አስረድቷል።
የአገው ሸንጎ የአገው ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብት እውን እንዲደረግ እንዲወሰን እና በሁሉም የአገው አካባቢዎች ማንነት መሠረት ተደርገው የተፈጸሙ የዘር ማጥፋትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።