09/24/2025
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
• መንፈሣዊ ተልዕኮ ተቀብላችሁ ለአገልግሎት የምትፋጠኑ ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ካህናት እና ዲያቆናት
• ከፍተኛ የመንግስት እና የግል ሚዲያ ተቋማት
• የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላችሁ ተጋባዥ እንግዶች ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለተገኛችሁ በልዑል እግዚአብሔር ስም ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።
ወደ ዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመግባታችን በፊት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ "እነሆ ዅሉን አዲስ አደርጋለሁ … አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛቱ ምድር አልፈዋልና። ባሕርም ወደ ፊት የለም››(ራእ. 21፥1-5) በማለት እንደተናገረው በማያልቀው ቸርነቱ መግቦቱ እና ጠብቆቱ የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ወቅትን እያፈራረቀ አዲስ ዓመትን ይሰጠናል። ዛሬም ቁጣውን በምህረት በደላችንን በትዕግስት አሳልፎልን ለ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ደርሰናል። እዚህ የተገኛችሁ እንግዶቻችን ፣ ይህን መርሃ ግብር በቀጥታ ስርጭት የምትከታተሉ ፣በተለያየ ሁኔታ ውስጥ እና በተለያየ የዓለም ክፍል የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን ከዘመነ ማቲዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አሸጋገረን።
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ “ገዳማዊ ህይወት” ራስን ለእግዚአብሔር በማስገዛት ትህትናን ገንዘብ አድርጎ እያንዳንዷን ሰዓት ፣ አንደበትን ፣ ጉልበትን እና ሃሳብን ለእግዚአብሔር በመስጠት የዓለም ዝና ሃብት ንብረት አላፊ የሆነውን ንግሥናን ውበትን በመናቅ ቤተሰብ እና ዘመድን ተለይቶ በመውጣት በገዳም ውስጥ በስርዓተ አበው ተወስኖ መስቀሉን ተሸክሞ መኖር መሆኑን ትነግረናለች።
ለዚህም ፋናዎች በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ታላላቅ ነብያት ውስጥ የነብዩ ኤልያስን ፣ የነብዩ ኤልሳዕ እና የነብዩ ሄኖክን ህይወት መመልከት ይቻላል። ኤልሳዕ አባት እና እናት ያለው በአስራ ሁለት ጥማድ በሬ የሚያርስ የነበረ ፣ በዓለማዊው ህይወት ሲኖር ምንም ያልጎደለበት ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ነብይ ኤልያስ ተከተለኝ ብሎ ጥሪ ሲያቀርብለት ምንም ሳያቅማማ በሬዎቹን አርዶ ለህዝቡ አብልቶ አባት እና እናቱን ተሰናብቶ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወደ ምድረ በዳ ወደ በርሃ ነብዩን ኤልያስን ተከትሎ ወጣ። ነብዩ ሔኖክም ቤተሰብ መስርቶ የሚኖር የነበረ ነገር ግን የበለጠ እግዚአብሔርን ለማገልገል ስለፈለገ አኗኗሩን እና አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ እግዚአብሔር ሰውሮታል።
በሐዲስ ኪዳንም ገዳማዊ ሕይወትን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተባርኮ እና ስርዓት ተዘርግቶ ተሰጥቶናል። የአዳምን በደል ይሽር ዘንድ በስጋ ከድንግል የተወለደው መድኃኔዓለም ይህ ህይወት የቅድስና መሆኑን እንድረዳው ከሁሉ አስቀድሞ የባረከው መሆኑን ልብ ልንለው የሚገባ ነው።
በነብያት እና በሐዋርያት ያላበቃው የገዳም ህይወት በእግረ ልቦና የሚከተሏቸው ብዙ ቅዱሳን ንዑዳን ብሩካን ጻድቃን አባቶቻችን እና እናቶቻችን በፍጹም ተጋድሎ ለጽድቅ በቅተው ገዳማዊ ህይወትን ገድሉን እና ትሩፋቱን ኖረው አሳይተውናል። ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልዕክቱ ላይ የነብያት እና የሐዋርያትን ተጋድሎ እንዲህ ሲል ያስረዳናል። ''በድንጋይ ተወግረው ሞቱ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳ በተራራ በዋሻ እና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ ይላል።
ስለ ስሜ ቤቱን ፣ ወንድም እህቶቹን ወይም አባት እናቱን ፣ ሃብት ንብረቱን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የተባለው ዓለምን ንቀው ለተከተሉት ገዳማውያን ጭምር የተነገረ ቃል መሆኑን ቤተክርስቲያናችን ታስተምራለች። ዛሬም በተለያዩ ገዳማት ውስጥ ግርማ ለሊቱን ድምጸ አራዊቱን ታግሰው ስለ ዓለም ሰላምን ፣ ድኅነት ሌት ተቀን የሚማጸኑ በሱባኤ እና በአርምሞ ያሉ መነኮሳይት እና መነኮሳት ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል በሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም የሚገኙ መነኮሳትን መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህም ቀደም እንደሚታወሰው የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በገዳሙ የነበሩ ችግሮች የተሰሩ ስራዎችንና በቀጣይ የሚሰሩ ዕቅዶችን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች ተነስተዋል። ገዳማውያኑ የሚቀምሱት እህል የሚለብሱት ልብስ እንዲሁም በሱባዔ የሚወሰኑበት በዓት እንደሌላቸው በተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እየተፈተኑ መሆናቸው ይታወሳል።
ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ከግምት በማስገባት ከህዝበ ክርስቲያኑ እና ከተቋማት በተገኙ ድጋፎች የእህል እና የአልባሳት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን የእናቶች በዓት ግንባታ ተጠናቆ እናቶችን ማስገባት ተችሏል። ገዳሙ በኢኮኖሚ ነጻነት እንዲኖረው ራሱን እንዲችል ለማድረግ በጠቅላይ ቤተክህነት እና በሐገረ ስብከቱ እውቅና በገዳሙ ስም የባንክ አካውንቶች ተከፍተው ይፋ ተደርጓል።
ገዳሙም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በወረዳ ቤተክህነት ፣ በሐገረ ስከብት እና በጠቅላይ ቤተክህነት ጸድቆ በሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬና የቅርብ ክትትል እየተደረገበት ከምዕመናን በሚገኘው ድጋፍ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
እነዚህን የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ገቢ የማሰባሰብ ሂደት ዕቅዶችን በመንደፍ እና በመቅረጽ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ለአብነትም ገዳሙ ያለበትን አሁናዊ እና ተጨባጭ ሁኔታ የሚገልፁ እና የሚያሳዩ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ዶግማ፣ ቀኖና እንዲሁም ትውፊት በጠበቀ መልኩ፦
• በቴሌቪዥን እና ራዲዮን ማስታወቂያዎችን በማስተላለፍ ህብረተሰቡ መረጃው ኖሮት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ተደረጓል።
• በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ለታቀዱት የልማት ስራዎች የሚያስፈልገውን ገቢ ለማሰባሰብ ጥረት ተደርጓል። በዚህም እስከ አሁን 29,750,620 /ሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ስድስት መቶ ሃያ/ ብር። የገንዘብ ድጋፍ እና 6,208,810 /ስድስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ አስር/ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል።
በሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም የተጀመረው ፕሮጀክት 18 (አስራ ስምንት) ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት በመጀመሪያው ምዕራፍ የፕሮጀክቱን ከ45% በላይ ማሳካት ተችሏል። ከእነዚህም መካከል፦
• የእናቶች በዓት እና የእንግዳ ማረፊያ በጥሩ ሁኔታ ተገንብቷል።
• ለገዳማውያኑ ለእንቅስቃሴ የማይመች እና አዳጋች የነበረው መንገድ 179 ሜትር ተራራ ተቦርቡሮ በአርማታ ደረጃ ተሰርቶለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
• የቤተ እግዚአብሔር ግንባታ ተከናውኖ ሙሉ ቁሳቁስ ተሟልቶ እየተገለገሉበት ይገኛል።
• በተደጋጋሚ የሚገጥመውን የምግብ አቅርቦት ችግር እና የአቅም ውስንነት በተወሰነ መልኩ ተፈቷል። በዘላቂነት ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
• ምንኩስና እና ሥራ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው ገዳማውያኑ የእደ ጥበብ ውጤቶችን የሚያመርቱበትን ማምረቻ ሼድ ግንባታ ተከናውኗል ለስራው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች እና የጥሬ ዕቃ ግብአቶች ተሟልተዋል። ስለ ስራው ክህሎት እና ዕውቀት እንዲኖራቸው መነኮሳት ሙያዊ ስልጠና በብቁ ባለሙያዎች እንዲወስዱ ተደርጓል።
• የሻማ እና የጧፍ መስሪያ ማሽኖች ግዢ ተፈጽሞ ወደ ምርት ተገብቷል።
• አካባቢው በረሃማ እና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
• ወደ ገዳሙ የሚያደርስ 8 (ስምንት) ኪሜ ደረጃ አንድ የጠጠር መንገድ ተሰርቶ ለአካባቢው ህብረተሰብ ጨምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
• አስቸጋሪ የነበረው የጋቢዮን መልከአ-ምድር እጅጉኑ ባመረ መልኩ ተገንብቶ ተጠናቋል።
• በሐሙሲት ከተማ የገዳሙን እራስን የመቻል እንቅስቃሴ ለማጠናከር የንዋያተ ቅዱሳን መሸጫ እንዲሁም የችርቻሮ እና የጅምላ መሸጫ ሱቅ ተከፍቷል።
• በገዳሙ የአረጓዴ ልማትን ለማስፋፋት አመርቂ የሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል።
• ለእናቶች መነኮሳይት ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ ሻወር እና መጸዳጃ ቤት ተገንብቷል ።
• ለግንባታ አገልግሎት የሚውል የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽን የብረታ ብረትና የእንጨት መስሪያ ማሽነሪ ግዢ ተፈጽሟል።
• ከመንግሥት ተቋማት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ የገዳሙ ይዞታ ህጋዊ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል።
• ለአብነት ት/ቤት ፣ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ መካከለኛ ደረጃ ጤና ጣቢያ እና ሌሎች አስፈላጊ የልማት ስራዎች የሚሰሩበት ህንጻ ግንባታ የሚገነባበት 30,000(ሰላሳ ሺህ) ካሬ ሜትር ቦታ በሀሙሲት ከተማ ላይ ከመንግስት በሊዝ ተረክቧል።
• ገዳሙን ከማስተዋወቅ እና ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚገኙ ብጽዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል እና ዘማሪያን ቦታው ድረስ ተገኝተው ገዳሙ ያለበትን ሁኔታ እና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እንዲመለከቱ ተደርጓል።
• የቅዱስ ሚካኤልን በረከቱን ፣ ምልጃውን እና ተዓምሩን የሚገልጽ እና ገዳሙን ከማስተዋወቅ አኳያ በዲ/ን አቤል መክበብ "ማር ሚካኤል" የሚል ዝማሬ ተሰርቶ እና ቀረጻው በገዳሙ ላይ ተከናውኖ በማኅቶት ሚዲያ አማካኝነት ለህዝብ እንዲደርስ ተደርጓል አሁንም በእይታ ላይ ይገኛል።
• ቤተክርስቲያን አሐቲ እንደመሆኗ ትኩረታቸውን ሐይማኖታዊ ይዘት አድርገው ከሚሰሩ ሚዲያዎች ጋር በመተባበር ገዳሙን ለምዕመናን ተደራሽ እናደርጋለን ባልነው መሰረት በተለያዩ ሚዲያዎች ዘጋቢ ፊልሞችን እና ሰፊ ማብራሪያዎች ለምዕመኑ ተደራሽ ተደርጓል።
• ከገዳሙ ወደ ጸበል ቦታ እና ከጸበልተኞች ማደሪያ ወደ ጸበል ቦታ የሚወስደው አስቸጋሪ የተራራ መንገድ የነበረ ሲሆን ተራራው እየተቆረጠ ደረጃ ተሰርቶለት ለአቅመ ደካሞች እና በህመም ላይ ሆነው ፈውስን ለሚጠብቁ ጭምር ለእንቅስቃሴ ምቹ ተደርጎ ግንባታው ተጠናቋል።
በገዳሙ የሚታየው የልማት እንቅስቃሴ አበረታች የሚባል ቢሆንም ገዳማውያኑ ካሉበት ችግር አንፃር በተሻለ ፍጥነት ሥራዎች እንዳይከናወኑ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸው አልቀረም። ከነዚሀም መካከል ፦
• በግንባታ ዕቃዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚስተዋል የዋጋ ልዩነት።
• ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ዛሬም ድረስ የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠራቸው።
• በገዳሙ ውስጥ ስራ የሚሰራባቸው ቀናት ውስን መሆን ማለትም ገዳማውያኑ የሚያከብሯቸው በዓላት ሲቀነሱ በወር ውስጥ የሚሰራባቸው ቀናት ከ4-14 የሚሆኑት ቀናት ብቻ መሆኑ በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ እያለፈ እስከአሁን የተከናወኑ ሥራዎች በተለይም የእናቶችን ችግር በመቅረፍ ደረጃ ጥሩና ገንቢ ናቸው።
ይህ የልማት ስራ ቀጣይነቱን ወደ አባቶች መነኮሳት በማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል። በትኩረት እየተሰሩ ከሚገኙ ስራዎች መካከል፦
• የአባቶች በዓት ግንባታ ሥራ
• የአባቶች ቤተ እግዚአብሔር ግንባታ ሥራ
• የእንጨት እና የብረታብረት ውጤቶች ማምረቻ ሼድ ግንባታ ሥራ
• የእህል መጋዘን ግንባታ ሥራ
• የጸበልተኞች ማረፊያ ቤት ግንባታ ሥራ
• የቅዱስ ሚካኤል ህንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ ሥራ
• የውሃ እና የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ
• የአብነት ትምህርት ቤት ፣ የአስኳላ ትምህርት ቤት ፣ መካከለኛ ደረጃ ክሊኒክ ፣ የንጽህና መጠበቂያ ማቴሪያሎች ማምረቻ ፣ የምግብ ማቀነባበሪያ እና የከብት እርባታ በቀጣይ ከሚሰሩት ስራዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
በገዳሙ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ከፍጻሜ አድርሶ ገዳማዊያኑም ካሉባቸው ተደራራቢ ችግሮች እንዲወጡ ለማድረግ በቀጣይ ለሚሰሩት የልማት ሥራዎች ማከናወኛ 210,000,000 /ሁለት መቶ አስር ሚሊዮን/ ብር የሚያስፈልግ ሲሆን ሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስከ ሶስት ዓመት ያህል ይህንን የልማት ስራ ለማጠናቀቅ የግንባታ ወቅት የሚያስፈልግ በመሆኑ ለዚህም የሚሆን ድጋፍ ለማሰባሰብ የተለያዩ መርሀ-ግብሮች የሚከናወኑ ይሆናል።
ለአብነትም፦
ጥቅምት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ “ገዳማዊ ልማት ለቤተክርስትያን ትሩፋት’’ በሚል መሪ ቃል ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በተገኙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ይኖረናል፤ ይሄ ጉባኤ ሰፊና ከ10,000 ሰዎች በላይ ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቅ ጉባኤ ሲሆን በኛ በኩልም ዝግጅታችንን አጠናቀናል።
በተመሳሳይ መልኩ በጎንደር እና በባህር ዳር ከተማዎች ላይ ጉባኤዎች የሚካሄዱ ይሆናል።
የተለያዩ ባዛሮችን በማዘጋጀት በገዳሙ ላይ የሚመረቱ ምርቶችን ለምዕመኑ ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል ።
የተለያዩ ሽልማቶችን የያዙ የሎተሪ እጣዎች ተዘጋጅተው ለምዕመኑ የሚቀርቡ ይሆናል።
በተለያዩ ሚዲያ ገጾች አሁን እየሰራናቸው ያሉ ገዳሙን የማስተዋወቅና ገቢም የማሰባሰብ ስራ ይቀጥላል።
በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 16 ቊ125-127 እንደተገለጠው ምጽዋት ምሕረት ነው።እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ ከተቀባዮች ጋር ሁኖ የሚቀበል በመስጠትና በመቀበል በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር ባለጸግነትን ለባለጸጋዎቸ የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው ይላል። “ስጡ ይሰጣችኋል” ተብሏልና በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው።
በቅዱስ ወንጌል እንደምናነበው ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር፤የጌታን ትእዛዝ፣ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውት እናገኛለን።
ከዚህም በተጨማሪ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ (የሐዋ.ሥራ 20 ፥ 35) (ማቴ. 10 ፥ 8)
(2ኛ ቆሮ. 9፥7-12) እና (መፅሀፈ ዕዝ 9፥5) ላይ በሰፊው ስለምጽዋት እና ከመስጠት ስለሚገኘው በረከት ተፅፎ እናገኛለን።
ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹ለድሃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሄር ያበድራል፣በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል› ይላል ፤ ዛሬም በዚህ በእኛ ዘመን ፣ ለዓለሙ ሰላም፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ድህነት ዘወትር የሚማጸኑት እነዚህ ገዳማዊያን በተለያዩ ችግሮች እየተፈተኑ ነውና ፣ ያሉባቸው ችግሮች ተፈተውላቸው፣ ዓለሙን ትተው የሄዱበትን የምንኩስና ህይወት ፈጣሪን መማጸን ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ሁሉም ምዕመን ባለው በጸጋ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ እና በገንዘቡ ድጋፍ እንዲያደርግ በልዑል እግዚአብሄር ስም ጥሪ እናቀርባለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
መስከረም ፲፬ ቀን ፳፲፻፲፰ ዓ.ም