Ethiopia Daily

Ethiopia Daily 24 hours News About Ethiopia!

11/06/2023

የቤት ኪራይ ንረት
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሐገሪቱ ከተሞች የቤት ኪራይ እየናረ በተለይም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች የኑሮ ውድነቱ ተጨምሮ መክፈል የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ለጣቢያችን የሚላኩ ጥቆማዎች ያመላክታሉ። የአዲስ አበባ መስተዳደር በየጊዜው አከራዮች የቤት ኪራይ እንዳይጨምሩና ተከራይን እንዳያስወጡ መመሪያ ቢያወጣም ተግባራዊነቱ ግን እምብዛም እንደሆነ ተከራዮች በምሬት ይገልጻሉ።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አከራዮች ቤቱ ለሌላ ሥራ ይፈለጋል፣ ቤተሰብ ከውጭ መጥቶብኛል፣ ለእድሳት ወዘተ በሚሉ ሰበብ አስባቦች ተከራዮችን እንደሚያስወጡ ይነገራል። የከተማዋ አስተዳደር በቤት ባለቤቶች ላይ ያወጣው አዲስ የንብረት ባለቤትነት ታክስ ምጣኔም ጫናው በይበልጥ በተከራዮች ጫንቃ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ችግሩን እንዳወሳሰበው መረጃዎች ያመላክታሉ።
በተለያየ ጊዜ ተገንብተው ያለቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶችም የማጠናቀቂያ ሥራዎች በአፋጣኝ ተጠናቀው ወደሚመለከታቸው ባለቤቶች ባለመተላለፋችው ችግሩን ይበልጥ እንዳከበደው ይነገራል።

10/31/2023

አዲስ አበባ : ጋብቻ ሲቀንስ ፍቺ ጨምሯል
| በአዲስ አበባ ከተማ የሩብ ዓመት የስራ ክንውን ከዓመናው ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር የጋብቻ ምዝገባ በ14% መቀነሱን እና የፍቺ ምዘገባ በ44.5% መጨመሩ ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የ የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በሶስት ወራት አፈፃፀም 7,090 ጋብቻ እና 1,172 ፍቺ መዝግቦ ማስረጃ የሰጠ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን ከ2015 ዓመት የምዝገባ ሽፋን አንፃር ሲታይ የጋብቻ ምዝገባ በ14% መቀነሱን እና የፍቺ ምዝገባ በ44.5% መጨምሩን አሳውቋል።
የኤጀንሲው የሲቪል ምዝገባ መረጃ እና ማስረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ቤተልሄም ታደሰ እንደገለፁት ምዝገባው በባህል ወይም በሃይማኖት የጋብቻ ስነ-ስርዓት ፈፅመው ወደ ኤጀንሲው ጽ/ቤቶች ቀርበው ያላስመገቡትን የማይካተት መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ከምዝገባ ተደራሽነት ባሻገር የወቅታዊ ምዝገባ ሽፋኑ መጨመሩንና በቀን በአማካይ 91 ጋብቻ እና 15 ፍቺ እየተመዘገበ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የታሪፍ ጭማሪ ተደረገ።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በተሰማሩ የሚዲ-ባሶች እና የሚኒ-ባስ ታክሲዎች ላይ   አድርጓል።አዲ...
10/31/2023

በአዲስ አበባ የታሪፍ ጭማሪ ተደረገ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በተሰማሩ የሚዲ-ባሶች እና የሚኒ-ባስ ታክሲዎች ላይ አድርጓል።

አዲሱ ታሪፍ ከነገ ጥቅምት 20 ቀን 2016 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ቢሮው አስታውቋል፡፡

10/30/2023

ጸሎትና ምሕላ ታውጇል!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
✞ ከህዳር 15 ቀን 2016 እስከ ታህሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ጸሎትና ምሕላ አውጇል

10/30/2023

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና በናይጄሪያ መንግስት መሐል የተፈጠረው ምንድነው?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የናይጄሪያ አየር መንገድ ለማቋቋም የወጣውን ጨረታ በማሸነፍ 49 በመቶ ድርሻ ይዞ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ በሁለቱ አካላት መሃከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የናይጄሪያ አየር መንገድ ኦፕሬተሮች (AON) ስር ያሉ የሀገር ውስጥ አቪዬሽን ድርጅቶች የናይጄሪያ አየር መንገድ አብላጫውን ድርሻ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመስጠት ማቀዱ ሀገሪቱን የሚጎዳ ነው በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።

በመቀጠል በናይጄሪያ ሌጎስ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የናይጄሪያ ፌደራል መንግስት የናይጄሪያ አየር መንገድ ድርሻን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይሸጥ የከለከለ ሲሆን ከወር በፊት የናይጄሪያ የአቪዬሽን ሚኒስትር የሆኑት ፌስቱስ ኬያሞ፥ ፕሮጀክቱ መታገዱን አሳውቀዋል።

ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረዥም ጊዜ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጦ የነበረ ሲሆን ከቀናት በፊት የአየር መንገዱ ቡድን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ምን አሉ?

ዋና ስራ አስፈፃሚው በመጀመሪያ አየር መንገዱ የናይጄሪያ አየር መንገድን ፕሮጀክት ለመውሰድ ተነሳሽነት እንዳልነበረው የገለፁ ሲሆን የናይጄሪያ መንግስት አየር መንገዱን ለማቋቋም ያደረገውን ግፊት ተከትሎ ወደ ጨረታው እንገደቡ ገልፀዋል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጪ በጨረታው ሌሎች አየር መንገዶች ይሳተፉ አይሳተፉ መረጃው እንደሌላቸው አቶ መስፍን ሲገልፁ ፥
ጨረታውን ከተወዳደሩ በኋላ "የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጄሪያን አየር መንገድ ለማቋቋም አጋር ሆኖ ተመርጧል" የሚል ደብዳቤ ከአቪዬሽን ሚኒስቴር ከደረሳቸው በኋላ የማቋቋሙ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አስረድተዋል።

አቶ ጣሳው ስለ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት ሁኔታ ምን አሉ?

አቶ ጣሳው የናይጄሪያ መንግስት የተቋማቸውን እገዛና ስትራቴጂ የሚፈልግ ከሆነ ተቋማቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀው የናይጄሪያ መንግስት ፕሮጀክቱን የሚሰርዝ ከሆነ ተቋማቸውን የሚያሳስብ እንዳልሆነ በማስረዳት "የናይጄሪያን መንግስት ውሳኔ እናከብራለን" ብለዋል።

10/25/2023

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ የአሜሪካን ብሄራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ሽልማትን ከፕሬዚደንት ጆ ባይደን እጅ ዛሬ ተቀብለዋል።

በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ዘርፍ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ የአሜሪካ ዜጎች በሚሰጠው በዚህ ሽልማት 19 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ፕሮፌሰር ጋቢሳ አንዱ ሆነዋል።

መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጄታ ለሽልማቱ ያበቃቸው በከፍተኛ የምርምር ስራቸው የእፅዋት ዘረመል ምህንድስና በመጠቀም በረሃማ የአየር ንብረት እና ነፍሳትን የሚቋቋሙ የአዝርዕት ዘሮችን በማግኘታቸው ነው። ግኝታቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የምግብ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ ታምኖበታል።

ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጄታ በምግብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅዖ ከዚህ በፊት ከዓለም የምግብ ፕሮግራሙ ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው።

10/25/2023

ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የላከቻቸው ሳተላይቶች ሥራ አቆሙ።

ለመሬት መልከታ ሥራ ወደ ሕዋ የተላኩት ሳተላይቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ሥራ ማቆማቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገልጿል።

ወደ ሕዋ የሚላኩ ሳተላይቶች የቆይታ ጊዜ (ሕዋ ላይ የሚቆዩበት) ቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን Ethiopian Remote Sensing Satellite - 01 (ETRSS - 01) የተሰኘች 70 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ታኅሣሥ 10/2012 ዓ. ም. ከቻይና ማምጠቋ ይታወሳል።

ይህች ሳተላይት ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ እና ለመልከዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎትን ስትሰጥ የቆየች ሲሆን ከተያዘላት ቀነ ገደብ ተጨማሪ 9 ወራት ሰርታለች ተብሏል።

ከ ETRSS - 01 መምጠቅ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ አገልግሎት የምትሰጥ ET-Smart-RSS ሌላ ሳተላይትም ማምጠቋ ተዘግቦ ነበር።

ሳተላይቶቹ መጨረሻቸው ምን ይሆናል?

ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የላከቻቸው የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ከመሬት ያላቸው ከፍታ 628 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ይህም የመሬት ስበትን ለመቋቋም እንዳይችሉ ስለሚያደርጋቸው እድሜያቸው አጭር ነው።

የሳተላይቶቹ ስሪትም በረዥም ጊዜ በራሳቸው ተሰባብረው ወደ ጥቃቅን ስብርባሪ እንዲቀየሩ ተደርገው ስለተሰሩ “በ15 እና 20 ዓመት ወደ ጥቃቅን ስብርባሪ ተቀይረው ይጠፋሉ።” ሲሉ አቶ አብዲሳ ያስረዳሉ።

አሁን ላይ ከሌሎች አገራት ሳተላይቶች መረጃ እየተቀበሉ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ምክንያት የሚፈጠር ክፍተት አይኖርም ብለዋል።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ለተመሳሳይ ዓላማ የሚውል ሌላ የበለጠ የጥራት ደረጃ ያለው ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት ላይ መሆኗን አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።

ስለ ኮሚኒኬሽን ሳተላይት አቶ አብዲሳ ምን አሉ?

ከመሬት ምልከታ ሳተላይት በተጨማሪ ኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት አቶ አብዲሳ፦

“የአዋጭነት ጥናት አካሂደን አዋጭነቱን ተመልከተናል። ፍላጎቱም አለ። ከፋይናንስ አንጻር የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ ስለሆነ ፋይናንሱ በሚገኝበት ወቅት አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት አለን” ብለዋል።

የኮሚኒኬሽን ሳተላይቶች እስከ 15 ዓመት አገልግሎት እየሰጡ ሊቆዩ ይችላሉ። እነዚህ ሳተላይቶች ወደ 36 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ርቀው ነው የሚቀመጡት። በዚህ ቦታ የመሬት ስበት አነስተኛ ስለሆነ ብዙ ዓመት የማገልገል አቅም አላቸው።

Credit : BBC Amharic

10/24/2023

የተመድና ኢሰመኮ የጋራ ምክረ ሀሳብ የኢትዮጵያውያንን ውሳኔ የሚሹ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጉዳዮችን እንዳይነካ ተጠየቀ::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋራ የሚሰጡት ምክረ ሐሳብ፣ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሊወስኑ በሚገባቸው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ እንዳያተኩር ማሳሰቢያ ተሰጠ።

ማሳሰቢያውን የሰጠው በኢትዮጵያ የታቀደውን የሽግግር ፍትሕ ሒደት የማማከርና ፖሊሲውን የማርቀቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት በፍትሕ ሚንስቴር አማካይነት የተቋቋመው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ነው።

የተመድና ኢሰመኮ የሽግግር ፍትሕ አማራጭ የፖሊሲ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ የባለሙያዎች ቡድኑ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ሲያካሂድ የቆየውን ውይይት አጠናቆ፣ ወደ ፖሊሲ ማርቀቅ ምዕራፍ እየተሻገረ መሆኑን በማስመልከት የጋራ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችን መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ አቅርቧል።

ተመድና ኢሰመኮ ባቀረቡት የጋራ ዝርዝር ምክረ ሐሳብ ላይ የተካተቱ የተወሰኑ መሠረታዊ ነጥቦች፣ የፖሊሲ ማርቀቅ ኃላፊነት በወሰደው የባለሙያዎች በድን ተቀባይነት አላገኘም። የባለሙያዎች ቡድኑም ይህንን መነሻ አድርጎ ለተመድና ኢሰመኮ ምላሽና ማሳሰቢያ የሰጠበትን መግለጫ ጥቅምት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. አውጥቷል።

‹‹የፖሊሲ ማርቀቅ ሒደቱ በኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታዎች ላይ በመመሥረት በኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫና ፍላጎት ብቻ መመራት አለበት፤›› ያለው የባለሙያዎች ቡድኑ መግለጫ፣ ‹‹ከዚህ አንፃር የተመድና የኢሰመኮ የኢትዮጵያ የሽግግር ፖሊሲ ማርቀቅ ሒደትን አስመልክቶ በቀጣይ በጋራ የሚያቀርቡት ማንኛውም ምክረ ሐሳብ የፖሊሲ ማዕቀፉ በምንና እንዴት መደራጀት እንዳለበት የሚወስኑ መሠረታዊ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማንሳት መቆጠብ አለበት፤›› ሲል ማሳሰቢያ አዘል ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል።

የባለሙያዎች ቡድኑ ይህንን ማሳሰቢያ ለመስጠት መነሻ የሆነው ተመድና ኢሰመኮ በጋራ ያወጡት ምክረ ሐሳብ ላይ በዳኝነትና በዳኝነት የማይታዩ ዕርምጃዎች ጥምረት (Combination of judicial and non-judicial measures) በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ያስቀመጡት ምክረ ሐሳብ ይዘት ነው።

ተመድና ኢሰመኮ ከላይ በተጠቀሰው ንዑስ ርዕስ ሥር ካስቀመጧቸው ምክረ ሐሳቦች አንዱ በባለሙያዎች ቡድኑ የሚረቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በዳኝነት ሊታዩ የሚገባቸውንና ከዳኝነት ውጪ የሚታዩ ጉዳዮችን በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ እንዳለበት ይገልጻል።

ተመድና ኢሰመኮ በጋራ በሰጡት ምክረ ሐሳብ፣ ‹‹የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው አጠቃላይ ይዘት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የቀድሞ የመብት ጥሰቶች ውርስ በአገሪቱ የፈጠረው ውስብስብ ችግርን ለመፍታት ሲባል የሚረቀቀው ፓሊሲ ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች በአገሪቱ የተፈጸሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ላይ ክስ መመሥረትን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በዳኝነትና ከዳኝነት ውጪ የሚታዩ ጉዳዮችን እንዲሁም ሒደትና ዘዴዎቹን በግልጽ ተርጉሞ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል።

በማከልም፣ ‹‹የሚረቀቀው ፖሊሲ ለዓለም አቀፍ ወንጀሎችና ለከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምሕረት መስጠትን ክልክል መሆኑን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፤›› ብሏል።

የፖሊሲ ማርቀቅ ኃላፈነቱን የወሰደው የባለሙያዎች ቡድን ማሳሳቢያ አዘል ምላሽ የሰጠውም ከላይ በተጠቀሱት የተመድና ኢሰመኮ የጋራ ምክረ ሐሳቦች ተገቢነት እንደሌላቸው በማመን ነው።

የባለሙያዎች ቡድኑ ከተመድና ኢሰመኮ ጋር ለሚሰጡት ድጋፍ ከፍተኛ አድናቆት ያለው መሆኑን፣ በቀጣይ የሚሰጧቸው ምክረ ሐሳቦችም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟላ የሽግግር ፖሊሲ ማርቀቅ ሒደትን ለማረጋገጥ ወሳኝነት መሆኑን ጠቁሟል። አጋርነቱ በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያን ብቻ ሊወስኑ በሚገባቸው የሽግግር ፍትሕ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማቅረብ መቆጠብ እንደሚገባቸው ማስገንዘብም አስፈላጊ መሆኑን የባለሙያዎች ቡድኑ አስረግጦ ተናግሯል።

‹‹ማንኛውም የሽግግር ፍትሕ ምርጫ በኅብረተሰቡ ሐሳብ እንዲሁም የፍትሕና የዕርቅ ፍላጎቶች ላይ ተመሥርቶ መወሰን አለበት፣ ይህም ማለት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ትኩረት በዕርቅ፣ በፈውስና በፍትሕ ላይ ነው ወይም በራሱ ልዩ ዓውዶችና እውነታዎች ላይ የተመሠረቱ ዕርምጃዎች ጥምረት ነው፤›› ሲል የባለሙያዎች ቡድኑ መግለጫ አስረድቷል።

10/24/2023

በ2015 በኢትዮጵያ ላይ 7 ሺህ የሚጠጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል ተባለ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ)ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት፥ በተቋማት መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች እየጨመሩ ነው።

ሳይበር በባህሪው ድንበር የለሽ፣ ውስብስብ እና ኢ-ተገማች በመሆኑ የሳይበር ደህንነት አቅምን ማሳደግ ካልተቻለ የሀገር ሉአላዊነት አደጋ ላይ ይወድቃልም ነው ያሉት።

ባለፈው አመት የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን መከላከል በመቻሉም በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረ 23.2 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

10/12/2023

አገር በቀል የማንጎ ዝርያ በተባይ ምክንያት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ተሰማ

10/12/2023

የፕሬዚዳንቷ የፓርላማ የመክፈቻ ንግግር ወቅታዊ ጉዳዮችን ያላብራራ ነው ተባለ

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከሁለት ቀናት በፊት ለሁለቱ ምክር ቤቶች የፌዴራል መንግሥትን አቋም አስመልክተው ያደረጉት ንግግር፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተገቢው መንገድ ያብራራና የመፍትሔ አቅጣጫዎቸን ያመላከተ አለመሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተናገሩ፡፡

በየዓመቱ መስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሚከፈተው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት አንደኛ ዓመታዊ የመጀመሪያ የጋራ ስብሰባ፣ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ መከፈቱ ይታወቃል፡፡

ከሁለቱም የምክር ቤቶች 469 አባላት የተገኙ ሲሆን፣ ከትግራይ ክልል በስተቀር የሁሉም ክልል ፕሬዚዳንቶች ተገኝተው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ዲፕሎማቶችና የበርካታ ተቋማት ተወካዮች የተገኙበት ይህ የመጀመሪያ ስብሰባ መርሐ ግብር 50 ያህል ደቂቃ የፈጀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቷ ለ40 ደቂቅ ያህል ንግግር አድርገዋል፡፡

Address

Washington D.C., DC

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Ethiopia Daily posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share