
23/07/2025
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ አከባቢን ለመፍጠር ህብረተሰቡ ችግኝ መትከልና ማሳደግ ይገባል፦ አቶ ግዛቴ ግጄ
ሐምሌ 16/2017 የወላይታ ዞን ደን አከባቢ ጥበቃና ልማት መምሪያ ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመሆን የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት በድጉና ፋንጎ ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አካሂዷል።
በመርሃግብሩ የተገኙት የክልሉ ደን አከባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ ሀገራችን ኢትዮጵያ የአየር ለውጥ ተፅዕኖን ለማቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ አሻራን ቀርጻ እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።
በክልሉ አንድ ተራራን በአንድ አከባቢን ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ አከባቢን ዕውን ለማድረግ የአረንጓዴ አሻራ ሚናው የጎላ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ተራሮች የስጋት ቀጠና ሳይሆኑ የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይም የካርቨን ፕሮጀክት በመቅረጽ ሀብት ለመፍጠር ከወርልድ ቪይዥን ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው፥ በአረንጓዴ አሻራ በአለም አቀፍ አቅፍ ደረጃ ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች በክልሉ መኖሩንም ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ህብረተሰቡ የአከባቢ ሥነ ምህዳር የሚቀየር ችግኝ በመትከል አካባቢውን መጠበቅና መንከባከብ እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደዞን ለአየር ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ አካባቢን ለመጠበቅ አንድ ተራራን የማልማት እና አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል።
ሁሉም ህብረተሰብ አካባቢውን ለመጠበቅ በየአካባቢው ችግኝ መትከል እንዳለበት ያሳሰቡት ዋና አስተዳዳሪው፥ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከለውን መጠበቅምና ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በድጉና ፋንጎ ወረዳ የተጎዳውን 'ዩሪያ' ተራራን መልሶ ለማልማት ከወርልድ ቪዥይን ጋር በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የወላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር አማረ አቦታ ችግኝ መትከል ከምንም ነገር በላይ እንደሆነና ጠቀሜታውም እጅግ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
አካባቢያችን ለመጠበቅ ችግኝ መትከል አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፥ ህብረተሰብ ችግኝ የመትከል መርሃግብር አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉና የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በድጉና ፋንጎ ወረዳ ፋንጎ ቦሎሶ ቀበሌ 'ዩሪያ' ተራራን ለማልማት "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።