14/10/2022
የቦረን ዋሻ ደብረ - እንቁ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ታሪክ
በባሶና ወራና ወረዳ በርከት ያሉ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የተፈጥሮ ስፍራዎች እና ታሪካዊ የሃይማኖት ተቋሞች ናቸው፡፡ ከተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የምኒሊክ መስኮት ፣ የሙሽ አርኪኦሎጂ ስፍራ ፣ ራስ ጎበና ዋሻ ፤ ደጃች መንገሻ ዋሻ --- እና እንደ ቶራ መስክ ያሉ የጦር ሜዳዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከታሪካዊ የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ እድሜያቸው በመቶ የሚቆጠሩ ከ50 በላይ ሲሆኑ ከመቶ አመት በታች የሚሆናቸው እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከእድሜያቸው ባሻገር አሰራራቸውና ሃይማኖታዊ ይዘታቸው እንዲሁም በያዙት ጥንታዊ ቅርስ አንፃር የጎብኝን አይን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ አዕምሮንም ጭምር በደስታ የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ዘጎ ቅድስት ማርያም ፣ ሚጣቅ አማኑኤል ፣ መጥቆሪያ ተክለሃይማኖት ፣ ወርቄ ሚካኤል ፣ ጌጣት ስላሴ ፣ ገነት ዋሻ ማርያም ፣ መለጥ መድሃኒአለም የመሳሰሉት ሲገኙ በ2004 ዓ.ም ተጠንቶ በቅርስነት ከተያዙ እና ለጎብኝዎች መዳረሻ ከሆኑት መካከል የወረዳውን ገፀ በረከት ፍንትው አድርጋ የምታሳየውን የቦረና ዋሻ ደብረ እንቁ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ታሪክን ልናስጎበኛችሁ ወደድን፡፡
ባለ አንድ ድንጋይ ፍልፍል የተፈጥሮ ዋሻ ዉስጥ ያለችዉ የቦረና ዋሻ ደብረ እንቁ ቅድስት ማሪያም በባሶና ወረና ወረዳ በዘንደጉር ቀበሌ ልዩ ስሙ ቦረና ዋሻ በተባለ ጎጥ ዉስጥ ከወረዳዉ ዋና ከተማ ደብረብረሀን 26 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ገዳማትን በማቃጠል ጉዳት በደረሰበት በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ይገመታል፡፡ የዘመኑ አባቶች ፅላቷን ለመሸሸግ በዚህ ደን በተሸፈነ ዋሻ ዉስጥ ከመላዕኩ ሩፋኤል ጋር በሳጥን አድርገዉ እንደአስቀመጧት አዋቂ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ይህ ታቦተ ህጉን በዉስጡ ይዞ የሚገኘዉ ዋሻ በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መግስት ብልሽት ደርሶበት ከየካቲት 10 ቀን 1947 ዓ.ም እስከ ግንቦት 21 ቀን 1949 አ.ም ድረስ ዕድሳት የተደረገለት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡ አባቶች እንደሚሉት በአካባቢዉ በጎችና ቦሮች ሲያግድ አንዷ በግ በዋሻዉ ዉስጥ ገበታ ስለወለደች እና ስለጠፋች እረኛዉ ለፍለጋ በገባበት አጋጣሚ ግልገሏ አልነሳ ብላዉ ቅጠል ሲያፈላግ ወላዷ በግ መጎናፀፊያ ከሳር ጋር በአፏ አንጠልጥላ አየ፡፡ አትኩሮ ሲመለከት ደግሞ በግንብ ዉስጥ በወርቅ የተለበጠ ሳጥን በማየቱ ለሰዉ ተናግሮ የማሪያም እና ሩፋኤል ፅላት እንዲገኝ ያደረገ ሲሆን ቦታዉም ቦሮች እረኛ ከሚለዉ ተወስዶ ቦረን ዋሻ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በሌላ በኩል ይች ቤተክርስቲያን ከ 900 ዓመታት በፊት እንደተመሰረተች አባቶች ሲናገሩ በአጥር ግቢዉ ዉስጥ የሚገኙት ዕድሜ ጠገብና ወፋፍር የሃገር በቀል ዛፎች ቤተክርስቲያኗ እድሜ ጠገብ ለመሆኗ ምስክርነታቸዉን ይሰጣሉ፡፡