28/08/2025
ተከፍሎህ እንጂ በነጻ አላገለገልክም!
ትናንት ከፌስ ቡክ ረዘም ላለ ወራት ራቅ በማለቴ አዳዲስ ሰዎችም ይወቁኝ የነበሩትም ያስታውሱኝ በሚል ስሜት እንዲሁም ለምን አላማ ነው እዚህ መንደር የምሟገተው የሚለውን አስምሬ ለማለፍ ስለ ፈለግሁ በአንዲት አጭር አንቀጽ "ለሀገሬ ይሄንና ያንን ሰራሁ" በማለት ባቀረብኩት ጽሁፍ ስር አንድ ስሜት ኮርኳሪ አስተያየት አነበብኩ። “ለሀገሬ ሰራሁ የምትለው ሁሉ ተከፍሎህ እንጂ በነጻ አይደለም” የምትል የዋህ የምትመስል አስተያየት....... (መልስ ልሰጣት ፈለግሁ)
በነገራችን ላይ ይህ የብዙ ሰዎች ስሜት ነው። አንድ ሰው በደሞዝ ከሰራ ሀገሩን እንዳገለገለ አይቆጠርም ብለው የሚያስቡ ተራ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ሹማምንትም አሉ። ይህ እጅግ የተሳሳተ ነው። ማንኛውም ዜጋ ተምሮ በእውቀቱ፣ ሰርቶ በጉልበቱ፣ በገንዘቡም ቢሆን ለሀገርና ለወገን ፋይዳ ያለው ስራ ከሰራ (ምንም እንኳ ከዚያ ምላሽ ገንዘብ ያገኘ ቢሆንም) ሀገሩን እንዳገለገለ ይቆጠራል። አደጉ ወደሚባሉ ሀገራት ብትመለከቱ እንደዚህ ያለ ቁም ነገር መስራት አቅቷቸው (በተፈጥሯዊም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክኒያት) ሰርተው መብላት ለማይችሉ ዜጎች ሀገራቸው የምግብ አስቤዛ ትሸምትላቸዋለች፣ ህክምና በነጻ ትሰጣቸዋለች፣ የኪስ ገንዘብም ትቆጥርላቸዋለች።
...ይሁን እንጂ ይህ የሚደረግላቸው ጤናቸው ተሻሽሎ፣ አቅማቸው ዳብሮ ወደ ስራ ወይ ወደ ትምህርት ገብተው ራሳቸውን መርዳት እንዲችሉ ነው። አንዳንዶች ይህን ነጻ ነገር ለምደው ቁጭ ብለው ይጦራሉ) ለእነዚህ ከሰውነታቸው አልፎ የሚሰጣቸው ምንም ክብር የለም። በአንጻሩ የተሰጣቸውን እድል ተጠቅመውም ይሁን በማንኛውም መንገድ ራሳቸውን ችለው ለተሻለ አላማ፣ ግብ፣ ስራ ሲበቁ ከፍተኛ ከበሬታ ይሰጣቸዋል። በተለይም በስራ አለም ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተው በጡረታ ሲገለሉ ምስጋና ይቸራቸዋል፣ ስጦታ ይጎርፍላቸዋል፣ ስማቸው በአንቱታ ይጠራል፣ በምሳሌነት ይወደሳሉ። ምክኒያቱም የእነዚህ ሰዎች ጉልበት፣ እውቀትና ነዋይ ጥርቅም ነው ሀገር ማለት። ሀገር በእንደዚህ ባሉ ሰዎች ነው በልጽጋ አድጋ ታፍራና ተከብራ የምትኖረው። እነዚህ ሰዎች ባይኖሩ ሀገርም ባልነበረችና.....
ረዢሙን ወሬ እናሳጥረውና ማናችንም ሀገሬን አገለገልኩ ለማለት በነጻ እስክናገለግል መጠበቅ የለብንም። የሀገር ሸክም ካልሆንን፣ ዘርፈን ሰርቀን ሀገርና ህዝብን ካልበደልን፣ ለሀገር እድገት መሰናክል ካልሆንን ተምረን አንድ ቁም ነገር ላይ በመድረሳችን ብቻ ኩሩ የሀገር ዜጎች ነን። ያውም እንደ ኢትዮጵያ ባለች ድህነት ባጎሳቆላት፣ ተስፋ በጭላንጭል በሚታይባት፣ እድል እኩል በሯን ለዜጎች በማትከፍትባት ሀገር ውስጥ ተምሮ ለቁም ነገር መብቃት ጀግንነት ነው! ለራሷ ለኢትዮጵያም ውለታ ነው!!!
እንዳልኩት ምንም እንኳ በነጻ የሚያገለግሉ ቅን ልብ ያላቸው ዜጎች ታላቅ አክብሮት ቢቸራቸውም “ሀገሬን አገልግያለሁ” ለማለት የግዴታ በነጻ መስራት አይጠበቅብንም። ጠዋት ማልዶ ወደ ስራው የሚሄድ፣ ተግቶ የሚሰራ፣ ተምሮ የሚሻሻል፣ ነግዶ የሚያተርፍ፣ መርቶ ወደ ተሻለ ግብ የሚያደርስ፣ በታማኝነት ተመርቶ ሀላፊነቱን የሚወጣ ሁሉ ለሀገሩ የሰራ የደከመ ታላቅ ሰው ነውና ምንም እንኳ ሀገር ለዚያ ደረጃ ደርሳ አክብራ ባታስከብረውም በራሱ እጅግ ሊኮራ ይገባል!!!!