
17/07/2025
በፈዋሽነታቸው የሚታወቁ የሸኮ የባህል መድኃኒቶች በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ ነው
============================
ሐምሌ 10/2017ዓ/ም በፈዋሽነታቸው የሚታወቁ የሸኮ የባህል መድኃኒቶች በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የሸኮ ወረዳ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ለተግባራዊነቱ ለባህል ህክም አዋቂዎች ስልጠና በሸኮ ወረዳ እየተሰጠ ነው።
የወረዳው ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ ቡይትን ፈዋሽ የሸኮ የባህል መድኃኒቶችን በመሰነድ ለትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የሸኮ ማህበረሰብ የበርካታ የባህል እውቀት ባለቤት መሆኑን የመሰከሩት ኃላፊው ዘመናዊ ህክምና ባልነበረበት ወቅት የተለያዩ በሽታዎችን በመፈወስ ለማህበረሰቡ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል ።
የባህል ህክምና ከእጽዋቶች የሚቀመም መሆኑን ጠቅሰው በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እጽዋቶችን ማቆየት እንደሚገባ አንስተዋል ።
የባህል እውቀቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ፣ለትውልድ እንዲተላለፉ ፣እውቅና እንዲያገኙና የባህል እውቀት ባለቤቶችም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል ።
የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኝ ይርዳ በበኩላቸው የሸኮ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ በባህል እውቀቱ ጤናውን ሲጠብቅ እንደነበረ አመልክተዋል ።
በሸኮ የባህል ህክምና በርካታ በሽታዎችን የሚፈዉሱ የአገር በቀል እውቀት ባለቤቶች መኖራቸው ገልጸው የወረዳው ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት በባህል እውቀት ጥበቃ ዘርፍ እያከናወነ ላለው ተግባር አመስግነዋል ።
የስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የባህል ህክምና አዋቂ ወይዘሮ ጣይቱ ተረፈ፣አቶ ሃብታሙ ፈጠነ እና አቶ ተመስገን ቴንባብ በርካታ በሽታዎችን በባህል ህክምና ማዳን እንደሚቻል ተናግረዋል ።
የባህል ህክምና ሲሰጥ በእውቀትና በጥንቃቄ መሆኑን እንዳለበትም አክለዋል ።
ለባህል መድህኒት መሰረቱ እጽዋቶች በመሆናቸው የተለያዩ በሽታዎችን የሚፈውሱ እጽዋቶች በአንድ አካባቢ ተተክለው ጥበቃና ክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
የሸኮ የባህል ህክምና አዋቂዎች በስልጠናው መድረክ በርካታ ሰዎችን አክመው ማዳናቸውን ገልጸዋል ።
የባህል እውቀት እውቅና አግኝቶና ተሰንዶ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በተሰጠው ስልጠና ግንዛቤ መጨበጣቸውን ተናግረዋል ።