
25/09/2025
ኤችአይቪን የሚከላከል መድኃኒት በአነስተኛ ዋጋ ሊቀርብ ነው
አዲስ ኤችአይቪን የሚከላከል መድኃኒት በአነስተኛ ዋጋ ተደራሽ ሊደረግ ነው።
በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ100 በላይ አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት መድኃኒቱ እንደሚቀርብ ተገልጿል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መድኃኒቱን እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ ይሆናል። ዓለም የኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝን ለመግታት አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትጓዝም ይረዳል ተብሏል።
ሌናካፓቪር (Lenacapavir) የተባለው መድኃኒት በመርፌ የሚሰጥ ነው። በዚህ ዓመት ማገባደጃ መድኃኒቱን ማቅረብ ይጀመራል።
መድኃኒቱ በነፍስ ወከፍ ለአንድ ዓመት የሚያስከፍለው 28,000 ዶላር ሲሆን፣ አዲስ በተደረገ ስምምነት መሠረት ግን ዋጋው ወደ 40 ዶላር የሚወርድ ይሆናል።
እአአ በ2027 የመድኃኒቱ ዋጋ ቀንሶ በ120 አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ይሰራጫል።ሳይንቲስቶች እንዳሉት ቫይረሱ ራሱን እንዳያባዛ መድኃኒቱ ይከላከላል።
በታዳጊ አገራት የሚኖሩና ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች መድኃኒቱን በርካሽ እንዲያገኙ የሚያስችለው ስምምነት እንዲፈረም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ከመድኃኒት አምራች ተቋሞች ጋር ድርድር አድርገዋል።
ክሊንተን ኸልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ፣ ከጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካው የምርምር ተቋም አርኤችአይ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።
መድኃኒቱ በተደረገበት ሙከራ አስደናቂ ውጤት ማሳየቱ ተገልጿል። ከሁለት ወራት በፊትም የዓለም ጤና ድርጅት ፀረ ኤችአይቪ ክፍል ይሁንታ ሰጥቶታል።
መርፌው በዓመት ሁለት ጊዜ ይወሰዳል። ለስድስት ወራት ኤችአይቪን ለመከላከል ይረዳል። ባለሙያዎች እንዳሉት አዲስ ኢንፌክሽንን ለመከላከል መድኃኒቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
በተለይም ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ወጣቶችና ሴቶች፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች እና በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሰዎችን ከበሽታው ለመከላከል ያግዛል።
አሁን ኤችአይቪን ለመከላከል ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን መድኃኒት (PrEP ወይም pre-exposure prophylaxis) እንደሚተካ ተገልጿል።
ይህ እንክብል በነፍስ ወከፍ በዓመት 40 ዶላር ያስከፍላል። እንክብሉ በየቀኑ ስለሚወሰድ ለሕሙማን ምቹ አይደለም። የበለጠ እንዲገለሉም ያደርጋል።
በየቀኑ የሚወሰድ መሆኑ በቀላሉ እንዳይገኝም ምክንያት ሆኗል። ጌትስ ፋውንዴሽን እንዳለው ከዚህ መድኃኒት ተጠቃሚ መሆን ከሚችሉ ሰዎች 18% ብቻ ናቸው እያገኙት ያለው።
አዲሱ መድኃኒት በአሜሪካና አውሮፓ መድኃኒት ተቆጣጣሪ ተቋማት ፈቃድ አግኝቷል።
አምና ሰኔ ላይ ጊሌድ የተባለ የአሜሪካ መድኃኒት አምራች መድኃኒቱ ላይ በሠራው ምርምር 100% ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።
ከ18 ወራት በኋላ መድኃኒቱ ተደራሽ እንደሚሆን ይጠበቃል።አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው አዲሱ መድኃኒት 4 በመቶ ተደራሽ ቢሆን 20 በመቶ አዲስ በሕመሙ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ይቀንሳል።
ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ ከማገዙ ባሻገር ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ለማከምም ይውላል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለኤችአይቪ/ኤድስ የሚደረግ ዓለም አቀፍ እርዳታ ላይ ቅነሳ ማድረጉ ቀውስ በፈጠረበት ወቅት ነው የአዲሱ መድኃኒት አቅርቦት ይፋ የተደረገው።
የመንግሥታቱ ድርጅት ፀረ ኤድስ መረጃ 40 ሚሊዮን ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ያሳያል።
እአአ ከ2000 ጀምሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ንቅናቄዎች ተደርገዋል። ሆኖም ባለፈው ዓመት ብቻ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ከ600,000 በላይ ሰዎች ከኤድስ ጋር በተያያዘ ሞተዋል። ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የሕሙማን ቁጥር ያላት አገር ናት። አደሱ መድኃኒት ከሚቀርብባቸው አገራት መካከል ትገኛለች።
የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር "አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት ነፍስ አድን መድኃኒትን የማቅረብ እንቅስቃሴን እንደግፋለን" ብሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።