
09/10/2025
እውነት ይነገር ከዳር እስከዳር !!
=================
ራስህን "ነቢይ ነኝ" ብለህ ከመሾምህ በፊት ነቢዮ ኢሳይያስ እኛ አሁን እየታነጽንበት ላለው ወንጌል በመጋዝ ሁለት ቦታ ተሰንጥቆ መሞቱን ታውቃለህ!?
ራስህን "ነቢይ ነኝ" ብለህ ከመሾምህ በፊት ለዚህ የወንጌል እውነት ሐዋርያውዮሐንስ በሚፈላ ዘይት በርሜል ውስጥ ተዘፍዝፎ መሞቱን: እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ "እንደ ጌታዬ በቁሜ አልሰቀልም" ብሎ ወደታች ተዘቅዝቆ በመሰቀል መሞቱን ታውቃለህ!?
የጥንቱ ሐዋርያት ዘመናዊ ውድ መኪና የመንዳት: ዘመናዊ ቪላ የመስራት: የቱርክ ሱፍና የፈረንሳይ ሽቶ የመቀባት አባዜና ጥማት አልነበረባቸውም::
የጥንቱ ሐዋርያው በጥቁር ገበያ በተጭበረበረ ዶላር: ዮሮና ፓውንድ: ከድሆች መቀነት በተዘረፈ ብር ቢሊየነር የመሆን ሕልም አልነበራቸውም::
የጥንቱ ሐዋርያት ዘይት: ውኃና ጨርቃ ጨርቅ ሽጠው ባለጠጋ የመሆን ሕልም አልነበራቸውም:: ትልልቅ አዳራሾች አልገነቡም:: የተሸቃቀጠ ወንጌል ሰብከው ዝና አላካበቱም:: ሐሰትን ከእውነት ቀላቅለው እንደ ሸቀጥ ለገበያ አላቀረቡም!!
ዛሬ ዛሬ ነቢይ: ሐዋርያ: ቢሾፕ እያሉ የተለያዩ ስሞችን ለራሳቸው የሚሰጡ ሰዎች የስሙን ዋጋና ክብር አላወቁም:: ስሙን የያዙ የጥንቱ እውነተኛ አገልጋዮች ስሙ የሚጠይቀውን እውነተኛ የሕይወት መስዋዕትነት እንደከፈሉ እነዚህ መክፈል አይፈልጉም!!
ዛሬ ማንም ስሙን የያዘው ሰው ስሙ ለሚጣይቀው እውነት ኑሮና ሕይወት መከራ መቀበል: ዋጋ መክፈል አይፈልግም:: የገዛ ምኞታቸው አገልጋይ እንደመሆናቸው መጠን እግዚአብሔርን ማገልገል ለሚያመጣው መስዋዕትነት ዝግጁ አይደሉም:: ፈቃደኛም አይሆኑም!!
የጥንቱ ነቢያትና ሐዋርያት ዓለማና ግብ ለወንጌሉ እውነት መጋደልና ነፍሳቸውን መስጠት ነው:: የዘወትር ትጋታቸው ነፍሳትን ለጌታ መማረክ: የክርስቶስ ክብር: ደቀ መዝሙራዊ ሕይወትና ተግባራዊ ክርስትና ነው !!
NB:-መታሰቢያነቱ እውነትን ተናግረው እውነትን ለሚኖሩ ወገኖች ይሁንልኝ ።
በወንድም ይድነቃቸው
fromJohannesburg