15/07/2026
ድምፅህን ሳይሆን አእምሮህን አሳድግ!
በዚህ ዘመን ሰዎችን የሚለያቸው የወሪያቸዉ ብዛት ሳይሆን የሀሳባቸዉ ጥልቀት ነው። ድምፅን ከፍ አድርጎ ማጮህ እውነትን አያረጋግጥም፤ ቁጣም ጥበብን አይተካም። ብልህ ሰው በጩኸት አይታወቅም፤ በረጋ አእምሮው፣ በትዕግሥቱ እና በአክብሮቱ እንጅ።
አእምሮውን ያቀጨጨ ሰው ሁልጊዜ ሌሎችን ለማሸነፍ ይጣደፋል፤ አእምሮውን ያበለጸገ ግን ራሱን ለማሸነፍ ይጥራል። የቀጨጨ አእምሮ በጩኸት እንዲሰማ ይፈልጋል፤ የበለጸገ አእምሮ ግን በተግባር የመታወቅ ዕድልን ያሰፋል።
የበለጸገ አእምሮ ያለዉ ሰው ከመናገሩ በፊት ያስባል፤ ከመፍረድ በፊት ይመረምራል፤ ከመቆጣት በፊት ራሱን ይቆጣጠራል። ሁሉንም አውቃለሁ ብሎ አይኮራም፤ ዛሬም እየተማርኩ ነኝ ብሎ ያስባል። ስለዚህ የበለጠ እውቀት ሲያገኝ ትህትናውም አብሮ ይጨምራል።
ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚጮኽ ሰው ሰዎችን ለጊዜው ሊያደናግር ይችላል፤ ነገር ግን በረጋ መንፈስ የሚናገር ሰው የሰዎችን ልብ ይገዛል። ጩኸት ጆሮን ያደነቁራል፤ ጥበብ ግን ልብን ያፈካል።
🌱 ለሕይወት አስፈላጊ ምክሮች
✔️ለመመለስ ሳይሆን ለመረዳት አዳምጥ።
✔️ክርክርን ከማሸነፍ ይልቅ ግንኙነትን ለማስጠበቅ ሞክር።
✔️ሰዎችን በቃል ከመጉዳት በፊት ቃልህ ሕይወት ይሰጣል ወይስ ይገድላል ብለህ ጠይቅ።
✔️እውነተኛ ጠንካራ ሰው ሌሎችን የሚያሸንፍ ሳይሆን ቁጣውን፣ ኩራቱን እና ምላሱን የሚቆጣጠር ነው።
✔️በየቀኑ አንድ አዲስ ነገር ተማር፤ አንድ መጥፎ ባህሪ ተው፤ አንድ ሰው አክብር።
➾በመጨረሻም፦
ሕይወት አጭር ናት። ሰዎች ከአንተ የሚያስታውሱት የጮኽክበትን አይደለም፤ ክብር ያሳየኽበትን ነው። የተከራከርክበትን አይደለም፤ ያስተማርካቸውን ነው። የሰበርከውን አይደለም፤ የገነባኸውን ነው።
ስለዚህ ወዳጄ...
አእምሮህን በእውቀት አበልጽግ፤ ልብህን በፍቅር ሙላ፤ ምላስህን በጥበብ ግዛ፤ ባህሪህን በትህትና አስውብ። ምክንያቱም የሰው ትልቁ ሀብት የሚያውቀው ነገር ብቻ አይደለም፤ የሚያውቀውን በምን ዓይነት ሥነ-ምግባርና ጥበብ እንደሚጠቀምበት ነው።
"ባዶ አእምሮ ጩኸትን ያመነጫል፤ የበለጸገ አእምሮ ግን ሰላምን፣ ጥበብን እና ተስፋን ይዘራል።" 🌿🤍