23/09/2025
የስኳር በሽታና እና የአይን ጤና
የስኳር በሽታ ትናንሽ የደም ስሮችን ከሚያጠቃባቸው ዋንኛ የሰውነት አካሎቻችን አንዱና ዋንኛው አይናችን ነው። በዚህ ፅሁፍ የስኳር በሽታ እንዴት የአይን ጤናን እንደሚያናጋ (በዋናነት የስኳር ሬቲና በሽታን (Diabetic retinopathy))፣ እነማና የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፣ ስንት አይነት የስኳር ሬቲና በሽታ አለ፣ምልክቶቹ እና መፍትሄውስ እሚለውን እንመለከታለን።
የስኳር በሽታ እንዴት የአይን ጤናን ያናጋል?
የደም የስኳር መጠን ከተለመደውና መሆን ካለበት መጠን በላይ ሆኖ ለረጅም ጊዜያት በሚቆይበት ጊዜ ለእይታ የሚያገለግለን የውስጠኛው የአይናችን ክፍል ላይ የሚገኙ ጥቃቅን የደም ሰሮች ህዋሳትን በመጉዳት፣ በመግደል፣ ህብርነታቸውን በማሳጣት በዉስጣቸው የሚያለፍው ደም ከደም ቧንቧ ሾልኮ በመውጣት ሬቲና እሚባለው የአይናችን ክፍል ላይ እንዲረጭ ያደርጋል። ከዚህም ባስ ሲል የውስጠኛውን የአይን የደም ስር በማጥበብ እሚፈሰውን የደም መጠንና የኦክስጅን አቅርቦት በማሳነስ አዳዲስ ደካማ፣ ደም ወደ ውጪ እንዲፈስና ሬቲና እንዲያብጥ የሚያደርጉ የደም ስሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪነት የስኳር በሽታ የሌንስን ጥራት በማሳጣት የአይን ሞራ እንዲከሰት ያደርጋል።
እነማና የበለጠ ለስኳር የሬቲና በሽታ (Diabetic retinopathy) ተጋላጭ ናቸው?
* ደካማ የሆን የስኳር መጠን ቁጥጥር ያላቸው ታካሚዎች
* ለረጅም አመታት ከስኳር በሽታ ጋር የቆዩ ታካሚዎች
* በተጨማሪነት የደም ግፊት በሽታ ያላቸው (75% ያህል በሚሆኑት ይህ በሽታ ይከሰትባቸዋል)
* ከፍተኛ የሆነ የኮሌስትሮል መጠን ያላቸው እንዲሁም (50% ያህል በሚሆኑት ይህ በሽታ ይከሰትባቸዋል)
* ሲጃራ ማጤስ የበለጠ ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ስንት አይነት የስኳር ሬቲና በሽታ አለ?
በዋንኛነት ሁለት አይነት የስኳር ሬቲና በሽታዎች አሉ
1. የደም ስር ያላበቀለ (Non prolifrative diabetic retinopahty)፦ በዚህኛው ስር የሬቲና ደም ስሮች ህዋሳት ተጎድተው፣ ህብርነታቸውን አጥተው፣ አንዳንድ ቦተዎች ላይ ወደ ውጪ አብጠው (Microaneurysms) ባስ ሲልም ደም እረጭተው የሚገኝበት ነው። ነገር ግን በዚህኛው አይነት ስር ምንም አይነት አዳዲስ የደም ስሮች በቅለው አናገኝም።
2. የደም ስር ያበቀለ (prolifrative diabetic retinopahty)፦ በዚህኛው ስር በዋናነት አዳዲስ የደም ስሮች በቅለው የሚገኝበት ነው።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
90% እሚሆኑ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች የበሽታው ምልክት እማያጋጥማቸው ሲሆን ሲከሰት ግን
* የእይታ ብዠ ማለት
* ቀለማትን ለመለየት መቸገር
* የእይታ መቀነስና ማጣት
* የአይን ግፊትን በመጨመርና ግላኮማን በማምጣት የአይን ውስጥ ህመም መፈጠር
* አይናችን ውስጥ እንደፀጉር ያለ ውር ውር እሚሉ ነገሮችን መመልከትን ያጠቃልላል
መፍትሄውስ?
መከላከሉንና መፍትሄውን ስንመለከት አራት አይነት ስትራቴጂዎች ይኖሩናል
ሀ. አጠቃላይ ህክምና
*ታካሚዎች የደም ስኳርን፣ HbA1cን፣ የደም ግፊታቸውንና የኮሌስትሮል መጠናቸውን በየጊዜው መለካትና ማወቅ
*የልብ፣ የኩላሊትና የነርቭ መርመራዎችን ማድረግ ሲኖርባቸው ከነዚህ በተጨማሪነት
1. የስኳር መጠናቸውን መቆጣጠር። እንዴት?
* ከሀኪም ጋር በመነጋገር አመጋገብን ማስተካከል
* መድሀኒትን በተገቢው ሰዓትና ተገቢውን መጠን መውስድ
* ቋሚና ተከታታይነት ያለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
2. የደም ግፊት ፣ የኮሌስትሮል መጠኖን መቆጣጠር
3. ሲጃራ ማጤስ ማቆም
4. የክትትል ጊዜዎን ሳያዛንፉ ሀኪሞን መጎብኘትና የደም ስኳር መጠኖን መለካት።
ለ. የመድሀኒት ህክምና ለስኳር ሬቲና በሽታ
- በሽታውን ተከትሎ የሚመጡ አዳዲስ የሬቲና የደም ስር እድገቶችን እሚከላከል፣ያሉትንም የሚያጠፋልን፣ የማዕከላዊ ሬቲና እብጠትን(Diabetic macular edema) የሚያሟሽሽልን በአይን ውስጥ በመርፌ እሚሰጡ የተለያዩ መድሀኒቶችን በአይን ሀኪም እንዲሰጥ በማድርግ እይታን መጠበቅ።
ሐ. የጨርር ህክምና
ጨረርን በመጠቀም አላስፈላጊ አዳዲስ የበቀሉ የደም ስሮችን እንዲከስሙ ያደርጋል።
መ. ቀዶ ህክምና
በቀዶ ህክምና፤ በሽታውን ተከትሎ የፈሰሰ ደም ካለና በራሱ መጥራት ሲገባው ሳይጠራ ለረጅም ጊዜ ሲቆይ ማጠብ፣ ከሬቲና ተያይዘው ያሉና እየሳቡ ያሉ ነገሮችን ማላቀቅና ሬቲናው ከቦታው ተላቆ ካለ መመለስ።
** ቀዶ ጥገና አንዱ የህክምና አማራጭ ቢሆንም ነገር ገና እይታ ጥርት ብሎ እንደድሮ አለመመለስ፣ ቁስሉ በቶሎ አለመዳን እንዲሁም ቁስለት የመያዝ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ።
*** በስኳር በሽታው የተነሳ ሞራ ሰርቶ ካለ በቀዶ ጥገና መገፈፍ ይኖርበታል።
መቼ የአይን ሀኪም ይጎብኙ?
የስኳር በሽታ ታካሚ ከሆኑ ምንም አይነት የእይታ መረበሽ ባይኖርቦትም እንኳ የአይን ሀኪም ጋር ሄደው መታየት አለቦት። መቼ?
* አይነት ሁለት የስኳር በሽታ እንዳለቦ ካወቁ የመጀመሪያ የአይን ምርመራዎን ወዲያውኑ የአይን ሀኪም ጋር በመሄድ ማድረግ አለቦት።
* አይነት አንድ ያለቦት ከሆኑ እንዳለቦት ባወቁ በ5 አመታት ውስጥ የመጀመሪያ የአይን ምርመራዎን ማድረግ አለቦት።
***በማንኛውም የጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች የስኳር በሽታ ታካሚዎቻቸው የአይን ምርመራን በተገቢው የጊዜ ሰሌዳ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ፣ ያላደረጉትን እንዲያደርጉ ማበረታታትና ወደአይን ሀኪም ጋር በመላክ የስኳር ሬቲና በሽታን መከላከልና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል።
ዶ/ር በእምነት ተረዳ ፤ የአይን ህክምና ስፔሻሊስት