In Christ

In Christ Blessed is the man who gets the opportunity to devote his life to something bigger than himself.

ሰላም ለሁላችሁ ከዚህ በፊት እንዳልነው የስነ አፈታት ትምህርታችን በዚህ ሳምንት እንጀምራለን ለሶስት ወር እስከ ጁን (June) ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ሁልጊዜ ሐሙስ ማታ  8:15 to 9:30...
03/29/2025

ሰላም ለሁላችሁ ከዚህ በፊት እንዳልነው የስነ አፈታት ትምህርታችን በዚህ ሳምንት እንጀምራለን ለሶስት ወር እስከ ጁን (June) ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ሁልጊዜ ሐሙስ ማታ 8:15 to 9:30 እና በዚህ ቀን ለማትችሉ በድጋሚ ቅዳሜ ጠዋት 8:15 to 9:30 am ክላሱ ይደገማል።

በዚህ አጋጣሚ ተመዝግባችው whats up መልእክት ያልደረሳችሁ ካላችሁ እንድታሳውቁኝ ይሁን እንዲሁም የተለያዩ መልእክቶችን whatsup ግሩብ ላይ ታገኛላችሁ።
ተባረኩልኝ

Shalom, everyone! As mentioned before, our hermeneutics class starts this week and will continue until June 30. The class will be held every Thursday from 8:15 to 9:30 PM, with a repeat session on Saturday morning from 8:15 to 9:30 AM. Calgary time

If anyone registered but still hasn't recieved whatsup notification, please let me know. Also, check WhatsApp for updates and communication.

Blessings,

Henok

02/11/2025
02/06/2025
02/04/2025

የእግዚአብሔር ፀጋ

ቲቶ 2 :12-13 ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል።

ከመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፀጋን በሙላት በመግለፅ ከሚታወቁ ጥቅሶች ውስጥ አንዱ ይህ ነው። ቲቶ 2:11-13 በክርስቶስ የተቀበልነው ፀጋ የሰውን ሁለንተና የሚሸፍን መሆኑን በጥልቀት ያስረዳል።

ሰው በትላንት ማንነት ፣ በዛሬው ኑሮ እና በነገ ተስፋው መካከል ያለ ፍጡር ነው። ህይወቱ እስካለ ድረስ ሶስቱ ግዜያቶች በላዩ ላይ አሉ። እግዚአብሔርም ከሰጠን ስጦታዎች ሁሉ ሶስቱንም የህይወት መስመራችንን ማስተካከል የሚችል ፀጋው ብቻ እንደሆነ ጳውሎስ ገላጭ በሆነ መልኩ በዚህ ጥቅስ አስቀምጦልናል።

ጥቅሱንም ስንበትነው ፀጋ በሶስቱ የግዜ ዓለም ላይ ያስገኘውን ውጤት ይነግረናል።

1. የትላንት ዓለምህ...ፀጋው ጨለማን ገፋፊ ነው። ዓለማዊ ምኞትን እና ኃጢአተኝነትን የለወጠልን፣ የትላንት ብሉሽነታችንን በደሙ ያጠበልን እንደሆነ ይነግረናል። እውነት ነው ይህ መጀመሪያ ከፀጋው ጋር ስንገናኝ የነበረንን ዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት የለወጠልን የእግዚአብሔር ኃይል ነው።

2. የነገው ተስፋ ...ፀጋው ተስፋ ሰጪ ነው። በትላንት ህይወት ብቻ አያበቃም። የትላንቱን ህይወት ለውጦ ዛሬና ነገን ለራሳችን የተወ ፀጋ አልተቀበልንም። በዳንክበት ክብር ከተጠጋኸው የክብር ተስፋችንን መገለጥ ሁልጊዜ እየናፈቅን እንድንኖር ያደርገናል።

3. የዛሬ ህይወት...ፀጋው አስተማሪ ነው። ይህንንም ተስፋ በመጠበቅ ህይወት ውስጥ ሳለን ራሳችንን የመግዛት እና የፅድቅ ህይወት እግዚአብሔርን ከመምሰል ጋር እንድንኖር ያው ፀጋ ያስተምረናል።

ስለዚህ በክርስቶስ የተገኘው ፀጋ የትላንት ህይወት መሻገሪያ ብቻ ሳይሆን የዛሬ መንገዳችንን በማስተማር የክብር ተስፋ የሆነውን የልጁን መገለጥ የሚያስናፍቅ ለህይወት ዘመን ሁሉ የተሰጠ ሙሉ ስጦታ ነው።

In Christ
Henok

02/03/2025

አዋጅ
ይህ ሰሞን የምኖርባት ምድር ሃገረ ካናዳ ላይ በወጣ የንግድ አዋጅ ምክንያት መንግስት ባልተለመደ ሁኔታ የፖለቲካውን አካሄድ ሲለውጥ አስተዋልኩ። እዚህ ሐገር ከገባው ጊዜ አንስቶ ያላየሁትን መነቃቃት በዘርፉም ያሉ ሙያተኞች ሲተነትኑም ተመለከትኩ።

ከሁሉ የወደድኩት ደግሞ የconservative party leader Pierre poiliovre የተናገሩት ነው። Its a wake up call and Its time to meet our potential የሚለው ። ከአዋጅ ጀርባ ያለውን የተረዱበት እና ለእኔ ትርጉም የሰጠኝ ንግግር።

ከንግዱ ጋር ስለወጣው ህግ...አዋጅ... ፖሊሲ ብዙም እውቀት የለኝም ፖለቲካዊም ስለሆነና የራሱም አካሄድ ስላለው መነካካት አልፈለኩም እንዳለ ለሞያተኞች ልተወው።

ላወራ የፈለኩትም ስለ ንግዱና ፖለቲካው ሳይሆን ይህን አስታክኬ በሁለንተና መልኩ አዋጅ ይዞት ስለሚመጣው ትሩፋት ነው።

አዋጅ ማንም ያውጀው ከታወጀ ለጥቅምህ ነው። የተለየ መንገድ እንድትመለከት የማሳየት አቅም በውስጡ ስላለው ይጠቅምሃል። በተለይ አንተን የሚያጠፋ ሆኖ ሲሰማህ ብዙ አትሸበር አቅምህን ሊያወጣው ነውና። ተጠቀመው

አዋጅ በየቀን ህይወትህ በሰውነትህ ውስጥ አለ። አንድን ነገር ለማሳካት ስትነሳ የመጀመሪያው አዋጅ አውጪ የራስህ አዕምሮ ነው ። አትችልም፣ አይሆንም፣ እድሜ ሄዷል፣ ገንዘብ እያለ የአዋጅ አይነት ይደረድራል።

ይህ ግን እንደማትችል ሳይሆን በደንብ እንድታስበው እና ግዜ እንድትወስድ ከተጠቀምክበት አልፈኸው ላለመሄድ የሚከለክልህ አይደለም።

በእስራኤል ላይ አዋጅ ባይ ወጣ ኖሮ ሙሴ እንደማንኛውም ልጅ በቤት ውስጥ ነበር የሚያድገው። ከሰፈር ወቶ ቤተ መንግስት የከተተው የወጣውን አዋጅ በብልሃት ያለፈች እናት ስለነበረችው ነው።

አዋጅ ሌላ መንገድ እንዳለ የሚያሳይህ መጠቆሚያ የውስጥ አቅምህ በሙላት እንዲገለጥ የሚረዳህ መሳሪያ ነው። በጥንቃቄ ከተገበርከው ትላንት ያላየህበትን መንገድ ሊያሳይህ ነውና አትፍራው።

ቀላል ነው እያልኩ አይደለም ለተወሰነ ግዜ የምታጣው ነገር ሊኖር ይችላል። በተለይ የተማመንክበት ነገር ባልጠበከው መንገድ ሲከሰት ያሳምማል። ግን ለጥቂት ግዜ ነው የተለየ መንገድ ልትሄድ ነውና አትፍራ።

ሌላ አዋጅ በራስህ እንድታምን አቅም ይሰጥሃል። እምነትህን በራስህ ላይ እንድታደርግ፣ በሰው ላይ ያለህ መተማመን በጥንቃቄ እንድትይዘው ያበረታሃል። ይህም ጥቅም ነው።

አዋጅ የውሳኔ ሰውም ያደርግሃል። ለመወሰን ሁልግዜ አዋጅ ይምጣ ባልልም፣ ከመጣ ግን ቁርጠኞች ስለሚሻገሩበት ምርጥ ነገር ነው። ታሪካቸው የተፃፈላቸው ሰዎች በሙሉ ይህንን የውሳኔ አቅም የተጠቀሙ ናቸው።

ስለዚህ በየትኛውም መንገድ ላይ የታወጀብህ ሲመስልህ ቀጣዩ አለምህን አስብና በደስታ ተቀበለው። አትርሳ አዋጅ ሙሴን ሰፈር ውስጥ እንዳያድግ ነው የረዳው

In Christ
Henok

01/30/2025

ያዕቆብ 4:10
በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።

01/21/2025

Both Faith and Fear demand you to believe in some thing you can't see.

You choose!

01/17/2025
01/06/2025

ኢየሱስ የትህትና ተምሳሌት

01/18/2023

ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን ማለት ስብስብ፣ ጉባኤን ያማከለ መሰባሰብን የሚወክል ቃል ሲሆን ይህም ስብስብ ለአንድ አላማና ተልዕኮ የተዋጀ ህዝብ የሚገናኝበትና ለአምላካቸው መሰዋእት የሚያቀርቡበትን ቦታ ሁሉ የሚሸፍን ህብር ቃል ነው። ይህም ህዝብ ሰማያዊ ጥሪን የተቀበሉ (ዕብ3፡1) በክርስቶስ እየሱስ ሞትና ትንሳኤ በማመን ዳግመኛ የተወለዱ (ዮሐ3፡16) እና በስሙ የተዋጁ (ኤፌ1፡7) የጌታ ልጆች ስብስብ ነው።

ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ህዝብነት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አካልና ሙላት እንዲሁም በአለም ላይ የተተወላትን ተልዕኮ ለመጨረስ የምትሰራ ሰማያዊ ውክልና ያላት መንፈሳዊ ቤት ናት። በብሉይ ኪዳን የመገናኛው ድንኳን(ዘፀ 27፡21) የምስክሩ ማደሪያ(ዘኁ1፡50) የእግዚአብሔር መቅደስ (ዘኁ19፡20) የእግዚአብሔር ቤት ይባል እንደነበረ በዚህ አዲስ ኪዳንም ህዝቡ ለእግዚአብሔር አላማና እርሱን ለማምለክ የሚሰባሰብቡት ስፍራን ያጠቃልላል።

ይህ ስብስብ ሰዎች በራሳቸው መነሳሳት ያቋቋሙት የራሳቸው ማኅበር ወይም ለአንድ ግብና ለተወሰነ አላማ በህብረት በመደራጀት የጀመሯት ተቋም አይደለችም። ይልቁን በአላማዋም ሆነ አቋሟ ፍፁም የተለየች፣ መገኛዋ ይህ አለም ቢሆንም ከዚህ አለም ፍጹም ያይደለች ሰማያዊ ውልደት ናት።(ዮሐ 17፡14)

ቤተ ክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ህዝብ

ከላይ እንዳየነው ባጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የአማኞች ስብስብ ናት። በመስቀል ላይ በተሰራው ስራ አምነው ይህንን ታላቅ እርቅ የተቀበሉና እንደገና በአባታቸው ጉያ መግባት የቻሉትን ልጆች ያጠቃለለች ነች። እነርሱም "ያመኑት" በሚል መጠሪያ የሚታወቁ ሲሆኑ ያላቸው ሁሉ የጋራ ሀብት እንደሆነ የሚያስቡ ባህሪያቸው እምነት፣ መንፈሳቸው የአንድነት፣ አካሄዳቸው የሰላም የሆነ የእርሱ ህዝቦች ተብለዋል።

አብርሃም ለሚያምኑት ሁሉ አባት የተባለው ልጅነት በእምነት በሚገኘው ጽድቅ ብቻ ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር በአብርሃም ህዝብን መረጠ። ይህም ህዝብ እስራኤል የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ከብዙ ባርነት በኋላ ከግብጽ አወጣው እንደ ህዝብም የሚሰፍርበትን፣ የሚያመልክበትን ቦታ ሰጠው። ይህ ከባርነት የወጣ ህዝብ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ምርጦች በመባል ይኖሩ እንደነበርና አምላካቸው እግዚአብሔርም መሐከላቸው እንደሚኖር ይመሰከርላቸው ነበር። 2ሳሙ 5፥2

በአዲሱ ኪዳንም ከዚህ አለም በክርስቶስ አምነው በመሸሽ ወደዚህ መንግሥት የፈለሱ ሁሉ በእግዚአብሔር ህዝብነት ይታወቃሉ። መጽሐፍም ሲናገር "ሕዝቤ ያልሆኑትን፣ ሕዝቤ ብዬ እጠራቸዋለሁ" ሮሜ 9፥25 ምንም ቀድሞ በደቀደቀ ጨለማ ይኖሩ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወደ ሚደነቅ ብርሃን እንደወጡና የእርሱ የተመረጠ ትውልድ እንደሚሆኑ ይናገራል።

በብሉይ ኪዳን እስራኤልን ከግብጽ ሲወጣ የተናገራቸው "የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ህዝብ ትሆኑኛላችሁ" ዘጸ 19፡5−6 የሚል ሲሆን ይኸው ድምጽ በአዲስ ኪዳን ከአለም ለተለዩት ህዝቦቹ ተሰጥቷል። የመንግሥቱ ካህናት እና የተቀደሰ ህዝብ የመሆን ጥሪ። እግዚአብሔርም ለመረጠው ህዝብ ባለሙሉ መብትና ጠባቂው እረኛ ነው።
ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካልና ሙላት (ኤፌ1፥23)

የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ነው። የወደዳት እርሱ ነው፣ የሚያጸናትም ሆነ የሚያኖራት እርሱ ነው። ይህች ቤት በምድር ላይ አካሉ ሆና እንድትመላለስ እውቅና የሰጠ ጌታ ኢይሱስ ነው። ይህም ንጽህትና ሙሽራ ሆና እንደተዋበች፣ ጉድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ ሆና ጌታዋን እንድትጠብቅ ያስፈልጋታል። ለዚህም እርሱን ልትታዘዘው በእርሱ ልትኖር ግድ ይላታል።

በሌላም በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ በስማይም ሆነ በምድር ሁሉን በሁሉ የሚሞላ ነው። ምድር ሁሉ የእርሱ ነች። የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና ተብሎ ይህ ሰማያዊ ሙላት በክርስቶስ በኩል እንደተገለጸና እኛም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል ተብሎ እንደተነገረልን(ቆላ 2፥10) ይህ የእርሱ ሙላት በልጆቹ አማካኝነት በቤቱ በኩል እንዲታይ የተቀመጠች አካሉ ነች።

ይህ ማለት አካልነቷን በተሰራላት ሰራ ስታገኝ፣ ሙላትነቷን ግን የተቀበለችውን በተሰጣት መሰምር ላይ በመጓዝ የምታቆየው ነው። ይህም በእግዚአብሔር የተወደዳችሁና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ የሚለውን ሐሳብ የያዘ ነው። በምድር ላይ ስላለች ግን በስመ አካልነት የራሷን መንገድ ቀይሳ ልትንቀሳቀስ ትችል ይሆናል። ያኔ ታዲያ አንዴ የተሰጣት አካልነት ከእርሷ ውስጥ ባይጠፋም የተመደበላት ሙላት ግን ፈጽሞ ልታመጣው አትችልም።

ስለዚህ ይህ ሙላት በቅድስና በመጓዝ የሚቀጥል፣ ለዘላለም ሕይወት በሚመጥን ኑሮ የተገነባ እና በክብርና ሽልማት የሚጠናቅቅ የህይወት ጉዞ ነው። ይህም በምድር ላይ ተሰሚነትን የምታገኝበት ዋናው መስመሯ ሲሆን፣ ከሌሎች ምድራዊ ተቋማትም የምትለይበት ሰማያዊ ባህሏ ነው።

ሌላው ሙላትነቷ ምስጢርን ገላጭ መሆኗ ነው። በቤተ ክርስቲያን እና በክርስቶስ መካከል ያለው ግንኙነት ታላቅ ሚስጥር ነው። ይህንን የቀደመ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ ምስጢር በዚህ ዘመን ለአለም ሁሉ ለመግለጥ የሚጠቀምባት የእግዚአብሔር ብቸኛ ልሳን ቤተ ክርስቲያን ነች። ለዚህም "ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል. . ." ማር 4፥11 ተብሎ የተነገረላት።

ከእነዚህ ምስጢራት መካከል የሰው ልጅ ዳግም የመወለድ ምስጢር፣ የመስቀሉ ስራ፣የመነጠቅ ምስጢር፣ የቅዱሣን ትንሳኤና ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው መነሣታቸው፣ የሐሰተኛው ክርስቶስ ምስጢር የመሳሰሉት በአለም ዘንድ እንደቀልድ የሚታዩት ወይም የማይታውቁት ምስጢራት በቤተ ክርስቲያን በኩል ግን እምነቷና የህይወቷ መርህ ሆነው ያቆይዋታል።

In Christ
ሄኖክ ዘውዴ

01/18/2023

የካህናት ተግዳሮት
ከባለፈው የቀጠለ
በዚህ አገልግሎት ላይ አንዳንድ ማንነታቸውን ያልለወጡ ካህናት በአገልግሎቱ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ቢሞክሩም እግዚአብሔር ግን አስፈላጊውን ቅጣት እየሰጠ ሕዝቡን እና ቤቱን በመጠበቅ እንዲጓዙ ያደርግ ነበር። በጉዞው ላይም ከታዩት ችግሮች ውስጥ ዛሬም ድረስ ለአገልግሎት እንቅፋት የሆኑትን በመምረጥ ለማየት እንሞክር።

1. ለብቃት ያለመኖር

የእግዚአብሔርን ቤት የሚያገለግለው ካህን ወይም ሌዋውያን ሁሉም በሌዊ የዘር ሀረግ ውስጥ መገኘት እንዳለባቸውና ለመቆጠር ከአንድ ወር ጀምሮ እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም ለማንኛውም አገልግሎት በቂ የሚሆነው ግን እድሜው ሠላሳ አመት እና ከእዚያ በላይ ሲሆን ብቻ ነበር። ከዚህ ዘር መወለዱ ለቤቱ አገልጋይነት ሙሉ ፍቃድ ይሰጠዋል ሙሉ እድሜ ላይ መሆኑ ደግሞ በአገልግሎቱ የሚገጥሙትን የጉልበትም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንዲሽከም አቅም ይሆነዋል።

ስለዚህ በመወለድ ያገኘውን አገልግሎት ከአባቶቹ በመማር ወደ ብቃት ማድረስ ተገቢ ነበር። ስለዚህ ከቀን ውሎው ጀምሮ ከሚመስለው ጋር በመሆን የሚማረው ሁሉ ስለ አገልግሎቱ ብቻ ነበር። መዳን በጸጋ ሲሆን ክህነት ግን በእውቀት የሚሆን ነው።

ኢየሱስም በምድር ላይ ባሳለፈው የሰላሳ ሶስት አመት እድሜው ውስጥ የመጀመሪያው የተናገረውና ሕይወቱን አሳልፎ ሊስጥ ባለበት በመጨረሻው ሰአት የተናገረው ይህንን የመጣበትን አላማ በማሳወቅ ነው። በአስራ ሁለት አመቱ በአባቱ ቤት ሊገኝ እንደሚገባው በማሳወቅ ሊፈልጉት ለመጡት ቤተሰቦቹ ሲናገር ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የኢየሱስ የመጀመሪያው ንግግር ነው። "ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን? ሲላቸው፣ በዮሐ 17 ላይ በታላቁ ጸሎት ጊዜ ደግሞ "የሰጠኽኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ በማለት" የምድር ቆይታውን ባጠቃላይ የተላከበትን በማድረግ ሊቀ ክህነቱ ላይ እንዳሳለፈው አሳይቷል።

ለዚህም ትልቅ ብቃት ይሆነው የነበረው ከእግዚአብሔር በአላማ መወለዱ እና በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት በሞገስና በጥበብ ማደጉ ሲሆን፣ የየእለት ህይወቱም ከተላከበት አላማ ጋር ብቻ ማዋሀድ መቻሉም የሚጠቀስ ነው። ዮሐ 4፥34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው "የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውንም መፈጸም ነው።

ሐዋሪያው ጳውሎስም ዳግም የተወለደበትን ሐሳብ ጠቅልሎ ሲያስቀምጠው እንዲህ ይላል፤ "ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የእራሱ ያደረገበትን ያንን እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ" ፊል 3፥12 ይህ ሰው ጌታ ለምን እንደፈለገው በአንደበቱ
ሲናገር ". . . ሂድ፤ በሩቅ ወዳሉት አሕዛብ እልክሃለሁና" አለኝ ብሏል። በህይወቱ ቆይታውም ይህንን ጥሪ የራሱ በማድረግ ለመፈጸም ሩቅ ጉዞ ሲያደርግ፣ አባቶችን ሲጠይቅ እና ከቀደሙት ሲማር ታይቷል። (ገላ 2፥2)

ለክህንነት ስራ መወለድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ስለተወለድንበት አላማ ያለን እውቀትም በጣም አስፈላጊ ነው። "ካህኑ የሁሉ ገዥ፣ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ስለሆነ ከንፈሮቹ ዕውቀትን ሊጠብቁ፣ ሰዎችም ከአንደበቱ ትምህርትን ሊፈልጉ ይገባል።" ሚል 2፥7 እግዚአብሔር ለሌዋውያን በብሉይ ኪዳን የማገልገያ ጊዜ እንዳስቀመጠ ሁሉ ለእኛም ወቅትን መድቦልናል። አንዳንድ ጊዜ ከወቅታችን ቀድመን በመነሳት ወይም በጣም በመዝገየት የተሰጠንን ሐላፊነት በሙላት ለመወጣት ሲታክተን ይታያል።

በጊዜያችንም ልንጠቀም ስንችል በተለያየ ምክንያት ከሐሳባችን ዞር እያልን ጊዜውን የምናቃጥል፣ ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች መሆን ሲገባን ገና ባለማደግ ውስጥ የምንዳክር ወይም ደግሞ ብቁ ሆነን ሳለን በፍርሐት ውስጥ የምንመላለስ ስንቶች ነን።

በእርግጥ የቤተ ክርስቲያን አንዱ ስራ ሰዎችን ለአገልግሎት የበቁ ማድረግ ቢሆንም ለዚህ ጉዳይ ከእራሳችን ውጪ ግን ማንንም ተጠያቂ ልናደርግ አንችልም።
"ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ" 2ኛ ጴጥ 3፥18

2. ያልተሰጠንን መፈለግ

ለሁላችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እርሱ እንደወደደው ጸጋውን አካፍሏል። ማንኛውም የአገልግሎት በረከታችን ያለው በእዚህ በተሰጠን ጸጋ ላይ ነው። ሰዎች በፍላጎታቸው ጸጋዎችን ቢያበላልጡም ሁሉም ጸጋዎች ቤቱን የሚጠቅሙ፣ ቅዱሳንን የሚያነቁ እንደሆነ መገንዘብ አለብን። የቀዓት ልጅ የሆነው ቆሬ ከሌዋውያን ወገን አንዱ ሲሆን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመግባት ንዋየ ቅዱሳቱን በመጠበቅና መገናኛው ድንኳን ከሰፈሩ ለመነሳት ሲዘጋጅ በአሮን እና ልጆቹ የተሸፈነውን መገልገያ ለመሸከም የሚመጣ ነበር። ዘኊ 4፥15 " አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ንዋየ ቅዱሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታዊያን ለመሽከም ይምጡ"

ሆኖም ግን ከሮቤል ነገድ ልጆች ጋር ሆኖ ሰዎችን ለክፋት በማስተባበር በሙሴ እና በካህኑ አሮን ላይ ተቃውሞ አነሳሳ። የተቃውሞውም መሪ ሐሳብ ከተሰጣቸው አገልግሎት በላይ የክህንነቱን ስራ ደርቦ ለመስራት አቅሙ አለን የሚል ነው። ሁላችንም የሌዊ ልጆች ነን እናንተን ብቻ የቤተ መቅደሱን ሙላዊ አገልግሎት መያዝ አይገባችሁም ለእኛም የሚሆን ስፍራ ያስፈልገናል ሁልግዜ በሽክም ብቻ አለቅን የሚል አይነት ነበር። በእርግጥ ከእግዚአብሔር የተሰጠህ እስከሆነ ድርስ በሸክምም ይሁን በማጠን ቤቱን ማገልገል ለእግዚአብሔርም ሆነ ለህዝቡ ያለው ጠቀሜታ እኩል ነው።

የሰው ሁሉ ችግር በተሰጠው ነገር ሳይሆን ለአይን ታይታ በሚስብ ቦታ ላይ ማገልገል መፈለጉ ነው። ዛሬ በሚያሳዝን መልኩ ወንጌል ወጥቶ መስበክ ያለፈበት እየመሰለ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ በመመማርና ማስተማር ሂደት ውስጥ መካፈል የልጆች ስራ እየመሰለ፣ በጸሎት አገልግሎት መታቀፍ ማንም የማያየው የጓዳ አገልግሎት ስለሆነ በሰው መመናመን እየተጎዳ በአጠቃላይ ቤቱ በሙሉነት እንዳይንቀሳቀስ የእራሳችንን አስተዋጽኦ እያረግን እንገኛለን።

ይህንንም ተገን በማድረግ ሰዎች ሁልጊዜ ከምዕመን ያለፈ ተግባር እንደሌላቸው የሚያስቡ መሪዎችም በጣት የሚቆጠሩ አይደሉም። ካልሞቱ በስተቀር ቦታውን ማስነካት የማይፈልጉ፣ እነርሱ ጠቅልለው ከሚያጎርሱት ውጪ ሌላው ምግብ ሁሉ የተበላሸ የሚመስላቸው፣ ልጄ አደገልኝ ሳይሆን አደገብኝ የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ይህም ቤቱን በተሻለ እንዳይንቀሳቀስ ከማድረጉም በላይ የህዝበ ክርስቲያኑን መንፈሳዊ እድገትም እንዲቀጭጭ አድርጓል። ይህ ሁለት የየራስ አመለካከት በማህበረሰባችን ውስጥ ዳርና ዳር በመጓተት ወርቃማ ጊዜ ያለምንም የተሻለ ውጤት ለማለፍ ትልቅ ምክንያት ሆኗል።

በእርግጥ ህዝበ ክርስቲያኑ መቶ ከመገልገል ውጪ የሚጠበቅበት ያለፈ ተልዕኮ እንዳለው ያወቀም አይመስልም። በቤቱ ውስጥ አስርና ሀያ አመት መቀመጪያ ስፍራቸውን እንኳን ሳይቀይሩ በአንድ ቦታ ላይ ሆነው የመርዶኪዮስን ታሪክ መጽናኛ አድርገው አንድ ቀን ንጉሱ ያስበኛል የሚሉ ብዙ፣ በጣም ብዙ ናቸው። እንደምናውቀው መርዶክዮስም ቢሆን በባቢሎን በስደት ምድር ላይ አይሁዲነቷን ጠብቃ በማንነቷ እንድታድግ ያስቻላት አስቴር የምትባል ለአይሁድ መዳን ምክንያት የሆነችን ሴት አሳድጎ አበርክቷል። ስለዚህ ባለህበት ዘመን ምንም ያህል ትንሽ ትሁን ለመንግስቱ ስራ አደራ አለብህ።

3. ፅናት ማጣት

ክህንነት ጠላት ክፉኛ የሚያጠቃው አገልግሎት ነው። ብዙ ድካምም ይጠይቃል አንዳንዴ በጸጋው ላይ ያለን እምነት የጠነከረ ስለሆነ እንጂ የሚቻል አይደለም። ለዚህ አገልግሎት እግዚአብሔር ለእነርሱ ብቻ ለይቶ የሰጣቸውና ከማንኛውም ህዝብ የሚለዩበት እንዲሁም በምድሪቷ ላይ የእግዚአብሔር ተወካዮች መሆናቸው የሚታዩበት የተለየ ክብር ነበራቸው።

ከዚህም ክብር ውስጥ አንዱ ልብሳቸው ነበር። ይህ ልብስ በታወቁ ጥበበኞች የተሰራ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ንድፉ የእግዚአብሔር ነው። ይህ ካህኑ ብቻ የሚለብሰው በጨለማው አለም ላይ ብርሃን እንዳለ፣ እግዚአብሔር እንዳልተዋቸው የሚመለከቱበት ልብስ ነበር። ካህኑ ልብሱን ለብሶ ሲመጣ በላዩ ላይ ባለው ክብርና ሞገስ የተነሳ አምላካቸው ምንኛ የተዋበ እንደሆነ ከማሳየቱም በላይ፡ ይህንን ልብስ ለመልበስ የታደለው ካህን ምንኛ በአምላኩ ዘንድ የተመረጠ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር።

ሰዎች እንደአካባቢያቸው፣ ባህላቸው፣ እምነታቸውና ባሉበት ስፍራ ባለው አየር ንብረት መሰረት ሁሉም የየራሱ መለያ ያለው አለባበስ ይጠቀማል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ልብስ ዘመንን፣ ስልጣንን፣ እውቀትንና ውበትን መገለጫም ሆኖ ያገለግላል። አሁን አሁን አልባሳት ትልቁን የአለም የንግድ ክፍል የተቆጣጠረ ሲሆን የሰዎችም የኑሮ ደረጃ መለኪያ ሆኗል። አለም ወደ አንድ መንደር በመለወጥ ላይ ስላለች የአለባበስም አይነት መወራረስና አንዱ የአንዱን በመከተል በሁሉም ዘንድ አንድ የሆነ የአለበበስ ስርአትን መመልከት የተለመደ ነው።

ሆኖም ግን ለካህናት በብሉይ ኪዳንም እንኳን ሊለብሱት የተሰጣቸው ልብስ ክብርን፣ ውበትን ዝናን ሁሉ አጠቃሎ የያዘ ሲሆን ማንም እንደፈለገው የሚለብሰው አይነት ልብስም አልነበረም።

01/18/2023

የጊዜ ጠላቶች

1. ጊዜ እንዳለን ማሰብ፡−
ጊዜ ዞሮ የሚመለሰው ግርግዳ ከሰቀልነው ሰዓት ላይ ብቻ ነው። ሰአቶቻችን ይህን ሊያስታውሱን ይገባል። ጊዜ የለም ልትሰራው በልብህ ያለ ነገር ካለ ተነስና አድርገው። ታውቃለህ ትልቁ ሰአትህን የሚወስደው ምን እንደሆነ፤ ልትሰራው የምትፈልገውን ነገር እስክትጀምረው ድረስ የምታቃጥለው ጊዜ ነው። ገና ነው፣ ምንችግር አለው ትደርሳለህ፣ ዋናው መድረሱ እንጂ በስንት ሰአት መድረስህ አይደለም የሚባሉት የህዝባችን አባባሎች ሁልጊዜ በጊዜ መትረፍረፍ ውስጥ የምንኖር አስመስለውናል። እውነታው ግን ጊዜያችንን እያጠፉት ነው። The most trouble thing in time is, you think you have more time. ከቡድሀ አባባሎች ውስጥ አንዱ።


2. በተሳሳተ መንገድ መጓዝ (Misdirection)፡−እረጅም ከተጓዙ በኋላ መንቃትን የሚያህል የሚያናድድ ነገር የለም። በርግጥ ከሚቀጥለው ኪሎ ሜትር በፊት መንቃትና መመልስ የተሻለ ቢሆንም። መንገድ ከመጀመሩ በፊት ሁሉን መጠየቅና በማወቅ እንደመጀመር ትርፋማነት ያለው አይደለም። አንዳንድ ሰው ከዘመናት በፊት ይህን ባደርግ ኖሮ እያለ አሁን ያለበትን የህይወት ሩጫ ይገታዋል። አንዳንዱ ደግሞ የትላንት ስህተቱን ለማካካስ በሚመስል ሌላ የስህተት ጎዳና ይጀምራል። ሌላው ደግሞ ብዙ ነገሮችን ለመስራት በብዙ ቦታ ይባክናል በመጨረሻ ሁሉም ጅማሬ ብቻ ይሆንበትና አንዱንም ሳይጨርስ ይደክማል። እነዚህ ሁሉ የተሳሳቱ መንገዶች ናቸው። ከታዘብኩት ውጤታማ የሚያደርግህ አንድ ነገር ለመስራት መነሳትህ እና የምትጓዝበትን መንገድህ መምረጡ ላይ ነው።

3. ግብ የለሽ ህይወት፡

ማለት የምትኖርለት አላማ ያለመኖር፣ በህይወትህ ግብህ ምንድነው?የቱንም ያህል ትንሽ ሊመስል ይችላል ሆኖም ግን ለይተህ ታውቀዋለህ ወይ። ግብህንስ ለማሳካት የቀየስከው መንገድ አለ ወይ? እንደምትጨርሰውስ ምን ያህል እርግጠኛ ነህ? እያንዳንዱ ሰከንድ ለአላማህ ወሳኝ እንደሆነስ አስበህ ታውቃለህ? ከተሰጡህ 24 ሰአት ውስጥ ለአላማህ ምን ያህሉን ታውላለህ . . .

ዕቃ ለመግዛት ሃያ ብር ኖት ይዘን ብንገበያይ እና ከገዛነው ላይ ሁለት ብር ቢመለስልን የተመለስልንን ትንሽ ገንዘብ ለሌላ አላማ እንደምንጠቀምበት (እንደማንጥላት) ሁሉ በቀን ውስጥ ሁሉን አድርገህ የሚተርፍህን አንድ እና ሁለት ሰአት ለምን ያለምንም ውጤት አልባሌ ቦታ ትጥለዋለህ. . . እነዚህ ጥያቄዎች እንዴትና ወዴት መሮጥ እንዳለብህ ያሳይሃል።

ግብ ህይወትህን በብዙ መንገድ ይጠቅመዋል

የህይወት ግብ ካለህ የምትሮትበት አላማ አለህ
የህይወት ግብ ካለህ የተቃና እይታ ይኖርሃል
የህይወት ግብ ካለህ ሁሌ መነቃቃት ይታይብሀል
የህይወት ግብ ካለህ ለመወሰን አትቸገርም . . . ግብ የለሽ ህይወት ስንፍናን (Laziness) ድብርትን (depression) ያስከትላል።(God is not disorganized- why are you?

4. አፍቅሮተ ስክሪን (Entertainment‚ phone‚ tv . . . )

አንድ ወዳጄ ስለ ኢንተርኔት ሲያጫውተኝ አልገባንም እንጂ ስሙ እራሱ መረብ ውስጥ መያዝ (inter−net) ነው ያለኝ አይረሳኝም። ድሮ ድሮ ሐብታሙ ብቻ ነበር ለመዝናናት የተፈጠረ የሚመስለው አሁን ግን በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ ሰው ኪሱ ውስጥ ይዟት በሚዞረው የህልም አለም፤ (ስልክን ማለቴ ነው)የፈለገበት በክሊክ (click) እየተጓዘ፤ የተጠራበትን እውነተኛ ህይወት የማይኖርበት ያህል እየመሰለ ያለበት ወቅት ነው። ያለ አግባብ ለሰአታት በሚዲያ ላይ ማሳለፍ ሰአትን መዋጀት ሳይሆን ሰአትን መግደል ነው። ይህን ስል ህዝባችን ሶሻል ሚዲያውን በብዛት ለምን አላማ እየተጠቀመው እንዳለ ስለሚታወቅ ነው። አባባሉ እራሱ ጊዜ ማሳለፊያ አይደል የሚባለው። በአግባቡ እና ለነገ ማንነት ገንቢ የሆነውን እየመረጥን የምንመገብ ከሆነ ዘመን ባመጣው መሳሪያ እየተጠቀሙ ከዘመኑ ጋር መፍሰስን የመሰለ ነገር የለም።

In Christ
ሄኖክ ዘውዴ

Address

Calgary, AB
T2C3R6

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when In Christ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share