
15/11/2024
ዜና: ብሔራዊ ባንክ ላኪዎች ካመነጩት የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶውን በመሸጥ ቀሪውን ላልተወሰነ ጊዜ በአካውንታቸው እንዲያስቀምጡ ፈቀደ
#የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላኪዎች ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውን 50 በመቶ ላልተወሰነ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ አካውንታቸው ማስቀመጥ የሚችሉበት አሰራር ከዛሬ ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እንዳሉት፣ ላኪዎች ካመነጩት የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶውን ለባንኮች ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውንም በአንድ ወር ውስጥ መሸጥ ይገደዱ ነበር።
በወቅቱ አሰራሩ በጊዜያዊነት ተግባራዊ ሲደረግ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲኖር ከመፈለግ እንደነበር አቶ ማሞ አስታውሰዋል።
ከዛሬ ህዳር 5 ቀን ጀምሮ ግን ላኪዎች ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውን 50 በመቶ ላልተወሰነ ጊዜ በአካውንታቸው ማስቀመጥ ይችላሉ ሲሉ መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ይህም ማለት ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ በአንድ ወር ውስጥ እንዲሸጡ አይገደዱም ማለት መሆኑን አመላክተዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በአሁኑ ወቅት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጸዋል።
የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሀብት መጨመሩን ጠቅሰው፤ ከሪፎርሙ በፊት ከነበረባቸው 518 ሚሊዮን ዶላር አሁን ላይ ከእዳ ነፃ መሆናቸውን ተናግረዋል።