27/04/2026
የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የሙስና ወንጀል ክስ መዝገብን መርምሮ በተከሳሾች ላይ የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ፣
የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት ሁለት ተከሳሾች ጥፋተኛ በተባሉበት የመንግስትን የሥራ ኃላፊነት በማይመች አኳኋን መምራት እና የሙስና ወንጀል በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 መሠረት ደረጃ የወጣለት መሆኑን ፍ/ቤቱ አስታውቋል።
ፍ/ቤቱ የወንጀሉን ድርጊት ፈጽመዋል ያላቸው 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዳዊት ገበየሁ ዱባና የዞኑ የቀድሞ ዋና አስተዳዳሪ፤ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ገደኖ ካዋይታ በዞኑ ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት የቀድሞ ኃላፊ ሲሆኑ፤ በመመሪያው አንቀፅ 98(4) እና (5) መሰረት የስልጣን ደረጃቸው መካከለኛ በመሆኑ፣ ተከሳሾቹ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉት የመንግስትና የህዝብ ሀብት ብር 3,702,466.67 (ሶስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሁለት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ስድስት ብር ከስልስ ሰባት ሳንቲም) የሚገመት መሆኑን፣ የተገኘው ጥቅምና በህዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን እንደዚሁም ተከሳሾቹ ወንጀሉን የፈፀሙበት ዓላማ ከባድ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለወንጀሉ ደረጃ አውጥቷል።
በዚህም መሠረት ፍ/ቤቱ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መነሻ ቅጣት የወሰነ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ "የወንጀል ድርጊቱን በጋራ ፈፅመዋል" በሚል ቅጣቱ እንዲከብድ በዐቃበ-ሕግ በኩል የተነሳውን የቅጣት ማክበጃ ተከትሎ ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት የስነ-ምግባር ችግር ወይም የወንጀል ሪከርድ የሌላቸው በመሆኑ፣ ሁለቱም የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸውና ለረዥም ጊዜያት መንግስትንና ህዝብን ያገለገሉ በመሆናቸው፤ በተለይ 1ኛ ተከሳሽ "እምርታ" የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ የነበሩ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ቀርበዋል።
በዚህም መሠረት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዳዊት ገበየሁ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉበት ከሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 20,000 (በሃያ ሺህ ብር) የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ፤ እንደዚሁም 2ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ገደኖ ካዋይታ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉበት ከመስከረም 14 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 20,000 (በሃያ ሺህ ብር) የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል።
በሌላ በኩል ተከሳሾቹ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትን የህዝብ ንብረት የዋጋ ግምት እንዲመልሱ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀጽ 101 መሰረት በክስ 2 ስር በፍትሐ ብሔር የተከሰሱበትን ብር 3,702,466.67 (ሶስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሁለት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ስድስት ብር ከ ስልስ ሰባት ሳንቲም) ለመንግስት በጋራ እንዲመልሱ ተወስኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍ/ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዳዊት ገበየሁ በዚሁ ፍ/ቤት በሌላ የወንጀል መዝገብ ከየካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና በ5,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን፤ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትን ግምቱ ብር 472,500 (አራት መት ሰባ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር)
የሆነ ንብረት ለመንግስት እንዲከፍሉ የተወሰነ በመሆኑ በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁጥር 186 መሰረት ሁለቱም የወንጀል ቅጣቶች ሲደመሩ ተከሳሹ በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በ25,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፏል።
መረጃው
የኮንሶ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ነው