19/09/2026
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከስልጤ ዞን አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ!
የዞኑ መንግስት በያዘው ጠንካራ ህዝብን የማሻገር አቋምና ወደ ተግባር የመቀየር አቅም ለረጅም ጊዜ ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶችን አልቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻልና የተቀሩትም በቅርብ ጊዜ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በዞኑ በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች በርካታ ፕሮጆክችን ጀምሮ በመጨረስ የዞኑ መንግስት ለተግባራቱ ስኬት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በዚህም ሂደት ዞኑ ፕሮጀክቶችን የመጀመር ብቻ ሳይሆን ጀምሮ የመጨረስ ልምምድ ማደጉን ያረጋገጠበት ነው።
በተመሳሳይ በዞናችን በፌዴራል መንግስት እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜያዊነት ቆመው እና ተጓተው የነበሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንደገና ወደ ሥራ ተመልሰው ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ። ለአብነትም እንደ ካሊድ ድጆ የመስኖ ፕሮጀክት፣ ፋን 1 የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ አንጀሌ የውሃ ፕሮጀክቶች፣ የአስፓልት መንገድ እና ሌሎችም። በልዩ ትኩረትና በተከታታይ ክትትል የቆሙ ሥራዎች እንደገና ነብስ ተዘርቶባቸው ወደ ምረቃ የሚቃረቡ መሆናቸው ችግር ሲፈጠር መፍትሔ መፈለግ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው።
ስለሆነም ወራቤ ከተማ የጋራ ማረፊያ፣ የዞኑ መዲናና የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር መቀመጫ መሆኗን ተከትሎ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ መዕከል እንድትሆን እንዲሁም መሠረተ ልማት የተሟላለት ፣ በተለያዩ የፓርክና የመዝናኛ ፕሮጀክቶች ውበቷ ደምቆ ለነዋሪዎቿ ምቹና ማራኪ እንድትሆን በልዩነት መስራት ግድ ይላል።
እንደሚታወቀዉ የወራቤ ዋና አስፓልት መንገድ የፌዴራል መንገድ በመሆኑ ኮሪደር ልማቱም በፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንዲፈጥን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተጀመረ ፕሮጀክት ነው። በተለይ ከተማዋ የሚገባትን የልማት ደረጃ እንድትይዝ ታሳቢ ተደርጎ በጥሩ ዲዛይን ተጀምሮ በትኩረት የተያዘ ጉዳይ ነበር። ስለሆነም የወራቤ ዋና አስፓልትና ኮሪደር ልማት የተዘነጋ ወይም የተተወ ፕሮጀክት አይደለም።
ፕሮጀክቱ የዋናው አሰፖልት ከቡታጀራ ሆስዕና አካል የነበረ ለኮሪደር ስራው ሲበል ብቻ የከተማው ተለይቶ ቀድሞ የሚጀምር ራሱን ችሎ ፕሮጀክት የሚሆን ሳይሆን ከወራቤ ቦዦባር አስፓልት ፕሮጀክት /suplimantery / ተጨማሪ ስራ ተደርጎ እንዲሰራ ተወስኖ የተገባበት ልማት ነው። የተፈጠረው መዘግየት የኮሪደር ልማት ሂደት ከመንግስት የግዢ ሂደት ጋር አጣጥሞ ለመሄድ የተደረገዉ ዉይይት ጊዜ መዉሰድ እና የተቋራጩ አቅም ማነስ ነው ።
የስልጤ ዞን አስተዳደርም ሆነ ክልሉ ስራው ወደ ተግባር እንዲገባ በተለየ መልኩ በመከታተል፣ ከሚመለከታቸው የፌዴራል አካላትና ከተቋራጩ ጋር በመነጋገር ሥራዉ እንዲቀጥል እና እንዲጠናቀቅ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ የምደረግ መሆኑን እንገልጻለን።
በሌላ በኩል የወራቤ ከተማ መሠረተ ልማት ችግር እንዲፈታ የስልጤ ዞን መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር በርካታ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል።
በዞኑ ካሉ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ህዝብን በማስተባበር ከ1,000 በላይ በሬዎች ከሞዴል አርሶ አደሮች ድጋፍ በማግኘት እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀብት በማሰባሰብ እንድሁም መንግስት በጀት በመመደብ የወራቤ ከተማ የዉስጥ ለዉስጥ አስፓልት መንገድ እና ኮሪደር ልማት በተሳለጠ ሁኔታ በአጭር ጊዜ እየተጠናቀቀ ይገኛል።
ሌላዉ የዞኑ መንግስት በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የህዝብን ችግር በቀጥታ የሚፈቱ ፕሮጀክቶችን በተለየ ትኩረት እየተከታተለ ይገኛል።
የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማትና ሌሎችም የህዝብን ዘላቂ ችግር የሚፈቱ ፕሮጀክቶች በጥብቅ ክትትልና በተገቢው ድጋፍ እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ሲሆን፣ በርካታዎቹም ለአገልግሎት ክፍት ሆነው ለመመረቅ ዝግጁ ሆነዋል።ይህ አቋም በወራቤ ዋና አስፓልትና ኮሪደር ልማት ላይም ተመሳሳይ ሆኖ ይቀጥላል።
የስልጤ ዞን አስተዳደር በጋራ አመራር / Collective Leadership ሥርዓት ህዝብን በማስተባበር እየመጡ ያሉ ውጤቶችን ማስቀጠል፣ የቆሙ ፕሮጀክቶችን በልዩ ትኩረት መደገፍና መከታተል እንዲሁም ህዝቡ በልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
ሆኖም ዘላቂ ልማት የሚረጋገጠዉ በመንግስት፣ በህዝብ፣ ባለሙያዎችና በባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ክንድ በመሆኑ ሁሉም አካላት የተለመደ ድርሻቸዉን አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የስልጤ ዞን አስተዳደር!!
መስከረም 9/2019 ዓ/ም