30/05/2023
ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ
ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ ሸገር ሲቲ ተብሎ በተሰየመው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ መስጊዶች ተገቢ ባልሆነ እና በህገወጥ መንገድ መፍረስ መጀመራቸውን ተከትሎ ይህ ህገወጥ የመስጊድ ፈረሳ እስከ አሁንም ድረስ በመቀጠሉ ህዝበ ሙስሊሙን በማስቆጣቱ ዕለተ አርብ ግንቦት 18/2015 በታላቁ አንዋር መስጊድ ህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞ ማሰማቱ ይታወቃል። በዕለቱ በነበረው ተቃውሞ ፖሊስ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በወሰደው የኃይል እርምጃ 2 ሙስሊሞች መስዋእትነት ሲከፍሉ በርካታ ሙስሊሞች ለአካል ጉዳት እና ለእስር ተዳርገዋል። በህዝባችን ላይ በደረሰው ጉዳት ነጃሺ ኢስላማዊ ማህበር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል። መስዋእትነት የከፈሉ ወንድሞቻችን በጀነተል ፊርደውስ ከነብዩ ሙሐመድ ሶለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጉረቤት እንዲያደርጋቸው አላህን እንማፀናለን።
ማህበረሰባችን ለዚህ የከፋ ጉዳት የተጋለጠው ሀቀኛ፣ ብቁ እና ህዝባዊ ተቀባይነት ያለው መሪ ተቋም የሌለው በመሆኑ እንደሆነ ይታወቃል። በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሙስሊሞች በብዙ መስዋእትነት የሰሯቸው መስጊዶች ከአንድ ተራ መኖሪያ ቤት እኩል ህገወጥ ናቸው ተብለው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዲፈርሱ ሲደረግ አሁን ላይ በህገወጥ መንገድ በመፈንቅለ መጅሊስ የሙስሊሙን መሪ ተቋም የተቆጣጠረው ቡድን መስጊዶቹ አንድ ብለው መፍረስ ሲጀምሩ ከማስቆም ይልቅ ዝምታን እና ማድበስበስን በመምረጡ ጉዳዩ ተባብሶ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ መስጊዶች እንዲፈርሱ ትልቁን በር ከፍቷል። ለመስጊዶቹ ጥብቅና በመቆም ህዝብን በማስተባበር ከመፍረስ ሊታደጋቸው ያልቻለው ህገወጡ መጅሊስ ለመስጊዶቹ መፍረስ እና ህዝበ ሙስሊሙ መሪ አልባ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ቅድሚያ ተጠያቂው ነው።
መንግስት የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ሙስሊሙ ማህበረሰብ የእምነት ተቋማቱ ያለ ምክንያት ሲፈርሱበት ተቆጥቶ በሰላማዊ መንገድ ቅሬታውን ሲገልፅ የፀጥታ አካል ያልተገባ የኃይል እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ህይወት መቅጠፍ እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው በፍፁም ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ከመሆኑ ባሻገር መንግስት የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ያለመወጣት ተግባር ነው። በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ህይወትና አካል ከሚቀጥፍ የኃይል ተግባር በመቆጠብ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በእለቱ አድማ በታኞች ወደ አንዋር መስጊድ ቅጥር ጊቢ ለመግባት ያደረጉት ሙከራ ፍፁም የተሳሳተ እና ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከፀጥታ ኃይላት ጋር ወደ ግጭት እንዲገባ ያደረገ ትንኮሳ ነበር። አስለቃሽ ጭስ ወደ መስጊድ ቅጥር ጊቢ መተኮሳቸው እጅግ የተወገዘ ተግባር ነው። የእምነት ተቋማት ሊከበሩ እና ሊታፈሩ፣ በውስጡ የተቀመጡ ምእመናን በሰላም በመስጊዱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የመቆየት እና የአምልኮ ተግባር የመፈፀም ሰብአዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል።
መስጊዶቻችን የህልውናችን መሰረት አላህን በብቸኝነት ለማምለክ የምንጠቀምባቸው ተቋሞቻችን እንደመሆናቸው ያለ ምክንያት ሲፈርሱ መመልከት እጅግ ስሜታዊ ያደርጋል። ሆኖም ግን በማህበረሰባችን ላይ የመጣውን ፈተና እንዴት መሻገር አለብን? ምን ብናደርግ ምን እናገኛለን ምን እናጣለን? በምን አይነት አቅጣጫ ነው መጓዝ ያለብን? ፈተናውን ለመጋፈጥ ያለን አቅም ምን ያህል ነው? … ለሚሉ በርካታ ጥያቄዎች መልስ እየሰጠን መጓዝ ከስሜት እና ከተናጠል አካሄዶች በመቆጠብ እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ ነገን አሻግረን እያየን ፈተናውን መሻገር ግድ ይሆናል። እንደ አለመታደል ሆኖ መሪ ዑለማኦቻችን ከመሰረቱት ተቋም በታጣቂ ኃይል ተገፍተው በመውጣታቸው እና መጅሊሱን የሚሾፍሩት የአንድ ቡድን ስሜት ብቻ የሚያንፀባርቁ ፅንፈኛ እና ህገወጥ ሰዎች በመሆናቸው ከህወገጡ መጅሊስ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚበጅ አቅጣጫ ይኖራል ተብሎ አይታመንም። በኦሮሚያ ክልል መስጊዶች ዛሬም ድረስ እየፈረሱ ቢሆንም ህገወጡ መጅሊስ አፉን ዘግቶ ተለጉሞ ቁጭ በማለቱ ዘላቂ መፍትሄ ከህገወጥ አካል አንጠብቅም።
በመሆኑም በአቅራቢያችን በአካባቢያችን የሚገኙ ዑለማኦቻችን ጋር ምን ይበጀናል? ብሎ በመመካከር
ካልተቀናጀ ከተናጠል እና ከስሜታዊ አካሄድ በመቆጠብ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የነፍስ፣ የደም፣ የአካል እና የንብረት መስዋእትነት ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳይገብር እጅግ የበረታ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በአስተውሎት መራመድ ዛሬ የተፈፀመብን ግፍና መድሎ ነገ በተሻለ ህብረት እና ጥንካሬ እንድንቋቋመው ያስችለናል።
ባለፉት ጊዜያት "ድምፃችን ይሰማ" የተባለው ቡድን በዲን ሽፋን ሙስሊሙን ማህበረሰብ ለድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ሲያታግል እና ተገቢ ያልሆነ መስዋእትነት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ሲያስከፍል እንደነበር የብልፅግና መንግስት መምጣትን ተከትሎ "የለውጡ ሃዋሪያ እኛ ነን፣ ዛሬ ለተገኘው ለውጥ ፈር ቀዳጆቹ ነን" እያሉ በወቅቱ የነበረው እንቅስቃሴ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ እንደተንቀሳቀሰ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል ዛሬም ድረስ በራሳቸው ላይ እየመሰከሩ ይገኛል። በመሆኑም ካለፈው ስህተት በመማር የሙስሊሙን ወቅታዊ ቁስሎች መነሻ በማድረግ ወደማናውቀው አቅጣጫ ይዘውን ለመጓዝ ለሚፈልጉ ለሚታወቁ እና ለማይታወቁ አካላት ተገዢ ባለመሆን ተደራራቢ ጉዳቶችን ማህበረሰባችን እንዳያስተናግድ ጥንቃቄ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ማንነታቸው የማይታወቁ እና ኃላፊነት የማይወስዱ አካላት በሚያስጀምሩት ተቃውሞዎች ተሳታፊ ባለመሆን ማህበረሰባችንን ከጉዳት እንጠብቅ።
ዕለተ አርብ ግንቦት 18/2015 በአንዋር መስጊድ እና በመርካቶ ዙሪያ ለተገደሉ፣ ቆስለው የአካል ጉዳት ለገጠማቸው እና ለታሰሩ ሰዎች ከጎናቸው በመቆም አስፈላጊውን እገዛ እናድርግላቸው። ብዙ ወጣቶች ቆስለው በህክምና ላይ ናቸው። በርካታ ወጣቶች በጅምላ ታፍሰው ዛሬም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ። በህመም እና በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛ እገዛ ያስፈልጋቸዋልና ጉዳዩ የጋራችን በመሆኑ እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ ኃላፊነታችንን እንወጣ። በዚህ አጋጣሚ ከሙስሊም ወንድሞቻቸው ጎን በመቆም አብሮነታቸውን መስዋእትነት በመክፈል ጭምር በጎነታቸውን ላሳዩን ክርስቲያን ወገኖቻችን እጅግ የላቀ ምስጋና እያቀረብን ሙስሊሙ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ ከጎናቸው እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆመው፣ የሙስሊሙ ንብረት የእምነት ተቋማት እና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አጥብቀን እንጠይቃለን።
የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ማሕበር