
19/07/2025
ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ “በጋዛ የዘር ፍጅት ወንጀል ተባባሪ” ነው የሚል ክስ ቀረበበት
የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፤ “በጋዛ የዘር ፍጅት ወንጀል ተባባሪ” ነው የሚል ክስ የቀረበበት በጸሐፊያን ጥምረት ነው። ጥምረቱ ይህን ክስ ያቀረበው የጋዜጣው ዘገባዎች ላይ ምርመራ በማድረግ ለሕዝብ ባሠራጨው ዶሴ አማካኝነት ነው።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሚሠሩ ጸሐፊያን ጥምረት ረቡዕ ዕለት ይፋ ባደረገው ሠነድ እንደሠፈረው፣ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሥልታዊ በሆነ መልኩ እስራኤልን የሚደግፍ እና ፍልስጤማውያንን የሚቃወሙ አድልዎአዊ መረጃዎችን ሲያሠራጭ ቆይቷል። ከባልደረቦቹ መካከል ጋዜጠኞች፣ አዘጋጆች እና ሥራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ ከሃያ በላይ ግለሰቦች ከእስራኤል ደጋፊ የሎቢ ቡድኖች ጋር ትስስር አላቸው።
የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባዎች በበርካታ የአሁን እና የቀድሞ የጋዜጣው ባልደረቦችና በእስራኤል ባለሥልጣናት አልያም በሠራዊቱ መካከል ባለው ሠፊ ቁሳዊ፣ የገንዘብ እና ርዕዮተ ዓለማዊ ትስስር ሊብራራ እንደሚችል ማሳያዎች የቀረቡበት መሆኑን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል።
በዚህም የጋዜጣው አርታዒዎች እንደ “ዘር ማጥፋት” እና “በወረራ የተያዙ ግዛቶች” የመሳሰሉ አገላለጾችን እንዲያስወግዱ እንዲሁም “ፍልስጤም” ብለው ከመጥራት እንዲታቀቡ ለሪፖርተሮች ነግረዋቸዋል።
በዚህ ተግባር ላይ የሚሣተፉ ሠራተኞች ለወንጀል ፈጻሚዎች ለሚሰጡት ሽፋን በግለሰብም ሆነ በመዋቅራዊ አሠራር ደረጃ ከአለቆቻቸው ድርጎ እንደሚሠፈርላቸው ተጋልጧል። ኒውዮርክ ታይምስ ለፈፀመው የሞያ ሥነ ምግባር ጥሰት ተጠያቂ መደረግ አለበት ያለው ጥምረቱ፣ የጋዜጣው አንባቢዎችም የዚህ ወንጀል ተባባሪ ላለመሆን ደንበኝነታቸውን እንዲያቋርጡ ጥሪ አቅርቧል።
ጥምረቱ አክሎም እንደ በርካታ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ሁሉ ኒውዮርክ ታይምስ በጋዛ ላይ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ባቀረበው ዘገባ ላይ ከፍተኛ ክትትል ማድረጉን በመግለፅ፣ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ታዛቢዎች በተመሣሣይ ጋዜጣው ለእስራኤል የጦር ወንጀሎች ሽፋን ይሰጣል ማለታቸውን አስታውሷል። (ሚንበር ቲቪ)
በድረ ገጽ ያንብቡ፦ https://minbertv.com/?p=10581
★ ★ ★
Minber TV | Ethio Sat | 11545 | H | 45000
!