
03/08/2025
የደራሲ ዶ/ር ያሬድ ኢሳያስ ኒዩሮ ሳይንስ ለሥራ ፈጠራ ቅጽ ፩ እና የኒዩሮ አመራር ሳይንስ ቅጽ ፪ መጻሕፍት ተመረቁ
በዶ/ር ያሬድ ኢሳያስ የተዘጋጁት ሁለት መጻሕፍት በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ( ገነተ ልዑል ቤተመንግስት ) ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።
በምረቃው ላይ የመጽሐፉን ይዘትና ቅርጽ ከገመገሙት መካከል ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ፣ ዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና ጋዜጠኛ ሱልጣን መሐመድ ኑር መጻሕፍቱ ለኢትዮጵያ የስራ ፈጣሪዎችና አመራሮች ሊኖራቸው የሚችለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ዝርዝር ትንታኔ አቅርበዋል። አያይዘውም በወጣቶች ዘንድ የሥራ ፈጠራ መንፈስን በማነሳሳትና የአመራር ብቃትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
አቶ ዛዲግ አብርሃ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ - ፕሬዝዳንት "ዶ/ር ያሬድ ‟የኒዩሮ አመራር ሳይንስ” በሚል የአመራር ልኅቀትን በኒዩሮ ሳይንስ ማጎልበት አስመልከቶ የጻፈውን ይኼንን መጽሐፍ ሳነብ አሳቡን እንድወደው ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱና ቀዳሚው መጽሐፉ ያተኮረበት ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼውም የሰው ልጅ ራሱን አስመልከቶ ያለውን እውቀት የተሟላ ለማድረግ ሲባል፥ ያደርግ የነበረውን የቆየ ጥረቱን የሚያጠናከር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የመጽሐፉ ዋነኛ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳይ የኒውሮ ሳይንስ አመራር ነውና። ደግሞም ደራሲው ዶ/ር ያሬድ ወጣት፣ የንግድ ሰውና የውጤታማ ካምፓኒዎች መሥራች ባለቤት ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚሰጠው ትርጉም ይበልጥ ግልፅ ይሆናል።
የዶ/ር ያሬድን በተሞክሮና በእውቀት የዳበረ መጽሐፍ የዚህ ዘመን የሀገሬ የቢዝነስ ልሂቃን ልከ እንደ ምዕራቡ ዓለም ሁሉ ታትረው የሚማሩ፣ በሥራቸው ያልተቋረጠ ስኬትን የተጎናጸፉ፣ በገባቸውና በተሞከሮአቸው ልክ መጽሐፍ እየጻፉ እውቀታቸውን ታትረው የሚያጋሩ እየሆኑ መምጣታቸውን እንደ ማብሰሪያ ደወል አድርጌ ነው የምወስደው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ዶ/ር ያሬድን ብዕርህ አይንጠፍ! በርታ! እያልኩኝ የአገራችን የቢዝነስ ልሂቃንም ልከ እንደ ዶ/ር ያሬድ ተሞከሯችሁንና እውቀታችሁን በመጻፍ በየትኛውም ግላዊም ሆነ መንግሥታዊ ተቋም አመራር የሆንን የአሁኑን እና የመጪው ዘመን ትውልድን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ላይ አሻራችሁን ታበረከቱ ዘንድ ላበረታታችሁ እወዳለሁ።"
ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በዝግጅቱ ላይ ነጻ ሐሳብ ቅምሻ ካቀረቡ መካከል ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ እና ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጃዋሬ በመጽሓፍቱ ውስጥ የተዳሰሱትን ሃሳቦችና ከራሳቸው ሙያዊ እውቀት ጋር በማያያዝ ልዩ ትንተና ለታዳሚዎች አቅርበዋል።
ማቴዎስ እንሰርሙ ተባባሪ ፕሮፌሰር
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንደተናገሩት፥ ዶ/ር ያሬድ፣ በኒዮሮሳይንስ - ለሥራ ፈጠራ፣ ለዓመታት ያደረጉት ጥልቅ ምርምር እና የግል ልምዳቸው በሥራ ፈጠራው ውስጥ ስኬታማ አድርጓቸዋል። ለዚህ ነው ፣ ደራሲው ለሥራ ፈጣሪዎች እና ፈታኙን ግን አስደሳች እና ጠቃሚ የንግድ ሥራ ጉዞን የጀመሩትን ለመርዳት መጽሐፍቱን ለምረቃ አብቅተዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ( ገነተ ልዑል ቤተመንግስት ወግ አቅራቢ በኃይሉ ገብረመድህን ጨምሮ
አበበ ባልቻ፣ ሀረገወይን አሰፋ፣ ተፈሪ አለሙ፣ ሙሉዓለም ታደሰ እና አቶ አንዱዓለም ተስፋዬ በመድረክ ወግ እና በንባብ አቅርበዋል።
እነዚህን መጽሓፍት በማንበብ የገዛ አእምሮህን በመጠቀም እንዴት የራስህን የንግድ ሥራ፣ ግንኙነቶችን እና ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት መጀመር እና ማሳደግ እንደምንችል አመላካች ናቸው።
የማንኛውም ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ስኬትም ሆነ ውድቀት ሁሉ ዐቢይ መንሥኤው አእምሮን በአግባቡ የመጠቀም ወይም ያለመጠቀም ወይም ከነጭራሹ ያለመጠቀም ሁኔታ ነው።
የበርካታ ስኬታማ ኩባንያዎች መሥራች፣ ባለቤትና በኬይ ዌስት ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የሆኑት ዶ/ር ያሬድ ኢሳያስ፣ እስካሁን ባደረጓቸው ሰፊ ሳይንሳዊ ጥናቶች እና የራሳቸውን ንግድ ሥራ በመምራት ካካበቱት ተሞከሮዎች ተፈትኖ የተረጋገጠውን እውቀታቸውን ያለስስት በመጻሕፋቸው አስነብበውናል።
ዶ/ር ማዝ ሳርስ፣ የትምህርት ፕሮግራም ዳይሬከተር
ኬይ ዌስት ዩኒቨርሲቲ በመጽሐፉ ላይ አስተያታቸውን አስፍረዋል ፥ "ዶ/ር ያሬድ ኢሳያስ ከኬይ ዌስት ዩኒቨርሲቲ - ፍሎሪዳ በቢዝነስ አስተዳደር ፒኤች.ዲአቸውን የሠሩ ሲሆን፤ በዩንቨርሲቲው ውስጥ የስትራቴጂከ ውሳኔ አሰጣጥ እና ችግር አፈታት፣ እንዲሁም የአስተዳደር ቲዎሪ ኮርስ አስተማሪም ናቸው። ዶ/ር ያሬድ ሥራ ፈጣሪ፣ የካፒታል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት እና የስኬታማ ኩባንያዎች ባለቤትም ናቸው፡፡"
አያይዘዉም ዶ/ር ያሬድ ኢሳያስ፣ የኢንተርዲኖሚኔሽን ቲኦሎጂ ዋና መሥራችና የኮሌጁ ፕሬዝዳንት፣ የሆሊ ቢት ሳውንድ ዎርሽፕ ሚንስትሪ መሥራችና ዳይሬከተር ሲሆኑ፣ ኒዮሮሳይንስ - ለሥራ ፈጠራ የተሰኘውን መጽሐፍ በዓይነቱ ልዩና ጠቃሚ የሆነ ርዕስ ይዘው ብቅ ያሉ መሪም ናቸው ሲሉ ምስክርነታቸውን በመጽሐፉ ላይ ሰጥተዋል።