
26/09/2025
🇪🇹" ሀገራዊ ስሜት የለም ፤ አትሌቶች ሀገራዊ ስሜት የላቸውም " - አትሌት ስለሺ ስህን
➡️ " ለጠፋው ውጤት ይቅርታ አይደለም መታሰርም ሲያንሰን ነው " - አትሌት የማነ ፀጋይ
በቅርቡ በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ስሟ በገነነበት የአትሌቲክስ ውድድር ቶኪዮ ላይ የተመዘገበው ውጤት አንገት የሚያስደፋ ፤ የስፖርቱን ቤተሰብ ፣ መላ ዜጎችን ያሳዘነ ሆኖ አልፏል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስለሺ ስህን በተገኘው ውጤት ፌዴሬሽኑና ልዑካን ቡድኑ ማዘናቸውን ገልጸው የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያን የማይገልፅ መሆኑን ተናግረዋል።
" ህዝቡን ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን " ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ " አብሮ ለመስራት ፍላጎት አልነበረም ፤ አትሌቶች አብራችሁ ልምምድ ስሩ በቡድን ስሩ ሲባሉ በአፍ ' እሺ እሺ ' ብለው ነገርግን አይተገብሩትም ፍላጎት የላቸውም " ሲሉ ገልጸዋል።
" ሀገራዊ ስሜት የለም ፤ አትሌቶች ሀገራዊ ስሜት የላቸውም ይህ ለውጤቱ ተፅዕኖ አሳድሯል ወደፊት በስፋት ይሰራበታል " ብለዋል።
የአትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አትሌት የማነ ፀጋይ " ለጠፋው ውጤት ይቅርታ አይደለም መታሰርም ሲያንሰን ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
" የተመዘገበው ውጤት የማይገባ ነው ፤ ይቅርታ አይደለም አለመታሰራችንም አንድ ነገር ነው " ሲሉ ገልጸዋል።
" እኔ በበኩሌ በርካታ አትሌቶች ማጣሪያውን እንደማያልፉ እርግጠኛ ነበርኩኝ " ብለዋል።
" እኛ አንጋፋዎቹም መከባበር፣ በቀራረብ፣ ማውራትና መነጋገር አለብን። የዚህ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለሪከርዶች ጥሩዬና ቀነኒሳ የት ናቸው ? ከምንገፋቸው ለምን አናቀርባቸውም ? " ሲሉ ጠይቀዋል።
" መወሻሸት አያስፈልግም አሁን ባሉት አትሌቶች መካከል የሀገር ፍቅር ከጠፋ ቆይቷል አብረው መዋል ፤ መመገብ እና መስራት አለባቸው ነገርግን አላደረጉም። " ብለዋል።
ምንጭ:-ቲክቫህ ስፖርት