08/08/2025
ዴቪድ ዴህያ ወደ ኦልትራፎርድ
በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት የራሳቸውን ዐሻራ አሳርፈው ካለፉ እና አሁንም ድረስ በኦልድትራፎርድ ከሚናፈቁ ተጫዋች መካከል አንዱ ነው ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴህያ፡፡
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በ2012/13 የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ አሳክተው ከዩናይትድ ጋር ከተለያዩ በኋላ ቡድኑ ደካማ የውድድር ዓመታትን ሲያሳልፍ እሱ በግሉ ምርጥነቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡
ከፈርጉሰን መልቀቅ በኋላ ወደ ኦልድትራፎርድ የመጡ የተለያዩ አሰልጣኞች ቡድኑን ወደ ክብሩ መመለስ ባይችሉም ዴህያ ብቻውን ጨዋታዎችን አሸንፎ የሚወጣ ግብ ጠባቂ ነበር፡፡ ለዚህም የቀድሞ የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር “ግብ ጠባቂ አንድን ጨዋታ ብቻውን አሸንፎ ከወጣ እሱ ዴቪድ ዴህያ ብቻ ነው” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ከዴቪድ ሞዬስ እስከ ሊዊ ቫንሀል፤ ከጆዜ ሞሪኒሆ እስከ ኦሊጉነር ሶልሸር፤ ከራልፍ ራኚክ እስከ ኤሪክ ቴንሀግ ባሉ አሰልጣኞች ስር ማንቼስተር ዩናይትድ በፊት በሚታወቀው ገናናነቱ መቀጠል ባይችልም እሱ ግን ብቻውን ልዩ ነበር፡፡
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ ለእኔ የአጨዋወት ፍልስፍና ዴህያ አይሆንም በማለት ገፍተው እንዳስወጡት የሚታወስ ሲሆን፤ ዴህያን በማባረር ያመጡት ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና በየጨዋታው ስህተት የሚሰራ እና በርካታ ጎል የሚቆጠርበት ግብ ጠባቂ ሆኖ ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡
ይህንንም የተመለከቱ የማንቼስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች እሱን መናፈቅ እና በድጋሚ በኦልድትራርድ መመልከት የሁል ጊዜ ምኞታቸው ነው፡፡
የቀያይ ሰይጣኖቹ ደጋፊዎች ዴህያን ቢናፍቁ አያስገርምም፤ ቡድናቸው ማንቼስተር ዩናይትድ ፈርጉሰንን ካጣ በኋላ ባለፉት ዓመታት ጨዋታዎችን ለማሸነፍ በሚቸገረው ቡድን ውስጥ የዴህያ አዳኝ እጆች ከጨዋታው ነጥብ እንዲያገኙ ሚናው የሚተካ አልነበረም፡፡
የድንቅ ችሎታ እና ተሰጥኦ ባለቤቱ ዴህያ በሚቸገረው ዩናይትድ ውስጥ በእሱ ልዩነት ፈጣሪነት ክለቡ ጨዋታዎችን አሸንፎ ሲወጣ መመልከት የተለመደ ነበር፡፡
ዩናይትድን ከለቀቀ በኋላ ለአንድ ውድድር ዓመት ያህል ክለብ አልባ ሆኖ ከቆየ በኋላ ወደ ጣሊያን በመጓዝ ፊዮረንቲናን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ፊዮረንቲና በጣሊያን ሴሪ ኤ 6ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ዴቪድ ዴህያ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
እንደተለመደው ሁሉ ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴህያ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያሳይ የነበረውን ድንቅ እንቅስቃሴ በጣሊያን ሴሪኤ በድጋሚ አሳይቷል፡፡
የማንችስተር ዩናይትድ የቀድሞ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴህያ 12 ዓመታትን ካሳለፈበት ክለቡ በፈረንጆቹ 2023 በነፃ መልቀቁ የሚታወስ ሲሆን÷ ነገ ወደ ኦልትራፎርድ በመምጣት የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ ይገጥማል፡፡
ዴቪድ ዴህያ የጨዋታው ቀን ከመድረሱ አስቀድሞ ወደ ኦልትራፎርድ መጥቶ እንደሚጫወት በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ካሰፈረ በኋላ በኦልድትራፎርድ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
ብሩኖ ፈርናንዴዝ እና ዴቪድ ዴህያ ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ በማህበራዊ ትስስር ገፅ በተለዋወጡት መልዕክት፤ ፈርናንዴዝ ጎል እንደማስቆጥርብህ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል ዴህያ በበኩሉ እንገናኛለን የሚል ምላሽ ሰጥቶታል፡፡
ነገ 8 ሰዓት ከ45 ላይ ማንቼስተር ዩናይትድ የጣሊያኑን ክለብ ፊዮረንቲናን በሜዳው ኦልድትራርድ ያስተናግዳል፡፡ ምንም እንኳን በእነሱ በኩል ተሰልፎ ባይጫወትም ዩናይትዶች የናፈቃቸውን ውድ ልጃቸውን ዴቪድ ዴህያን በኦልድትራፎርድ ሲጫወት ይመለከቱታል፡፡