27/09/2026
ፍቺ ጠየቀች!
..እወደዋለሁ....እሳሳለታለሁ...ልክ እንደ እናት እቅፌ ውስጥ አስገብቼ ፀጉሩን እየደባበስኩ..
"ዛሬ ቀንህ እንዴት ነበር አባቴ?"
"ባክሽ ብዙ ደስ አይልም ወይ ላንለወጥ ነገር እየደከምን ነው ሌላ አማራጮችን መፈለግ አለብን...መጀመሪያ ቃል እንደገባሁልሽ ቃሌን ማክበር አልቻልኩም...አንደላቅቄ ማኖር አልቻልኩም...ከጓደኞችሽ አሳነስኩሽ...አታይም ፀጉርሽን" ይለኛል የተበጣጠሰ ፀጉሬን ቀና ብሎ በእጁ እየነካካ....
"እኔኮ አፈቅርሀለው ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ አውቃለሁ ባይመጣም አፈቅርሀለው ኪስህን አይቼ አይደለም የወደድኩህ ...አንተ ብቻ በርታልኝ አንተ ብቻ ጠንክርልኝ ቢኖርህ እንዴት እንደምታኖረኝ አውቃለሁ"
"ብቻ ነገ ቀን ይውጣልን የኔ እናት" ብሎ ግንባሬን ስሞኝ ከስሬ ይሸጎጣል...ይለፋል ይሰራል እኔም እሰራለሁ ግን ትዳር እንዳሰብነው አልሆነልንም ነበር ከባድ ጊዜ ነበር ....ከጊዜያት በኋላ ሁሉም ነገር መስመር ያዘልን ...ሱቅ ከፈትን...ሀብት አፈራን...ብዙ ነገሮችን ቀየርን....
"ከጓደኞቼ ጋ ራት ፕሮግራም አለብኝ ካመሸሁ አታስቢ አትጠብቂኝ"
"እሺ ራሳችሁን ጠብቁ"
..ከጊዜያት በኋላ ያመጣው ባህሪ ግራ ያጋባል...ያኔ በባዶ ኪስ የነበረን ፍቅር አሁን ገንዘብ ቀይሮታል...ቤቱ ከሚያድርበት ውጪ የሚያድርበት ጊዜ ይበልጣል...እንደበፊቱ መታቀፍን አይፈልግም ...ከእኔጋ ጊዜ ማሳለፍ አይፈልግም...እንደውም ከእኔጋ መታየትንም አይፈልግም...ብዙ ጊዜ ችግሩ ከእኔ ነው ብዬ ራሴን ለመለወጥ ታገልኩ...ኋላ ላይ የገባኝ ችግሩ የኔ እንዳልሆነ ነው ያኔ ዝምታን መረጥኩ....
"መፋታት አለብን በእርግጥ የተፈራረምነው ነገር የለም እንለያይ.."
አለኝ....ለካ አልተፈራረምንም...ያኔ እንፈራረም ስለው" ከወረቀትኮ ልብ ይበልጣል" ነበር ያለኝ የትም አይሄድም ብዬ ስላሰብኩ ከዛ በኋላ ደግሜ አልጠየቅኩትም.....
"ያሁሉ ጊዜስ? ያ ሁሉ ፍቅራችንስ? የኔስ እድሜ? በቃ? በቀላሉ እንለያይ አልከኝ? "
"አዎ በቃ እኔም ላንቺ ያለኝ ስሜት ቀንሷል...አንቺም በጊዜ ወደሚወድሽ ሂጂ" ..ለካ ነይልኝ ባሉ ማግስት ሂጂም ይባላል...ለእሱ ብዬ ነበር ከቤተሰቦቼ የተለየሁት...አይሆንሽም ሲሉኝ ይወደኛል ይሆነኛል ብዬ ነበር በባዶ ቤቱ የገባሁት....
"አስብበት ግድ የለህም"
"አስቤበታለሁ ውሳኔዬን ነው የነገርኩሽ...ቤተሰቦችሽ ጋ ምትሄጂበትን ቀን ሰአት አሳውቂኝ መኪና እልክልሻለሁ..." ጥሎኝ ወጣ....
ግራ ገባኝ...ከሱጋ ያሳለፍኩት ጊዜ
በሰከንዶች ውስጥ እንደ ትውስታ ታዩኝ...በባዶ ቤት የነበረን ፍቅር ታየኝ...ልቤ ተሰበረ ድምፁ ለእራሴ እስኪሰማኝ ድረስ ከሽ...ከሽ...ይለፍልኝ እንጂ አንቺን እንዴት እንደማኖርሽ አቃለው ብሎኝ አልነበር? ገንዘብ ሲመጣ ፀባይም አብሮ ይቀየራል? ፍቅርም ይጠፋል? ምኔ አስጠልቶት ነው? እንደ እናት ስፍስፍ አልኩበት? የትም እያደረ ሲመጣ ስለማልጠረጥረው ነው? ወይስ ጨቅጫቃ ሚስት መሆን ነበረብኝ? እኔ የችግሩ መወጣጫ ነበርኩ? ብዙ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎች..... አብረን የተነሳነው አንድ ፎቶ እንኳን አልነበረንም....ፍቅር አውሮኝ ነበር....እኔ ከዛ ቤት በወጣሁ ማግስት...የምታምር የምታሳሳ ቆንጅዬ ኮረዳ አስገባ...ቅር አላለኝም ...ውበቴ ደብዝዞበት ነው ካለበት ደረጃ ጋ አልመጥነውም ነበር....ቅር አላለኝም....ማፍቀር የራስ ማድረግ ብቻ አይደለም የሚያፈቅሩትን ሰው ምርጫም ማክበር ፍቅር ነው።