
08/08/2025
በኬንያ ዋና ከተማ አቅራቢያ የህክምና አውሮፕላን ተከስክሶ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ።
በኬኒያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ አቅራቢያ በሚገኝ ህዝብ በሚበዛበት አካባቢ የህክምና ቡድኖችን ያሳፈረ አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሶ የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
የአየር አምቡላንስ አገልግሎት ሰጭ የሆነ አውሮፕላን ከኬንያ ዋና ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ የመኖሪያ መንደር ላይ ሐሙስ እለት መከስከሱን ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
በአደጋው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎች እና ምድር ላይ የነበሩ 2 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን በአካባቢው ኪያምቡ የተሰኘችው ግዛት ኮሚሽነር ሄነሪ ዋፉላ ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላኑ ከዊልሰን አየር ማረፊያ ከተነሳ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን የኬኒያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣናቴ ገልጸዋል።
የኬንያ ቀይ መስቀል የነፍስ አድን ቡድኖቹ ከናይሮቢ ጋር በሚያዋስነው አውራጃ ኪያምቡ ወደሚገኘው የአደጋው ቦታ ማቅናታቸውን ገልጿል።
የአካባቢው ስታር ጋዜጣ የኬንያ መንግስት ባለስልጣናት ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም ሲል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።
በኤልዳና ታደሰ