10/12/2025
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዶናይ ብርሃነ ሀ/ሚካኤል የተባለ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለፀ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዶናይ ብርሃነ ሀ/ሚካኤል የተባለ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ቲክቶከር አዶናይ ብርሃነ ሀ/ሚካኤል በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው "ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል እና መልካም ሥነ-ምግባር በተቃራኒ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ አለባበስ ለብሰው በአደባባይ እና በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት የታዩት አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር በዋሉበት የወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ" መሆኑን ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
አዶናይ በቅርቡ በተካሄደው በ3ኛው የጂ- ፓወር ቲክቶክ ክርኤቲቭ አዋርድ ላይ በአራት ዘርፎች ማሸነፉ ይታወቃል።
ፌዴራል ፖሊስ በመግለጫው ዕውቅና እና ገንዘብ ለማግኘት ብቻ በማሰብ ሚዲያዎችን ኃላፊነት በጎደለው አኳሃን እየተጠቀሙ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በመልካም ሥነ ምግባር ተቀርጾ ሀገርን የሚጠቅሙ ተግባራትን እንዳያከናውንና በተቃራኒው በትውልዱ ላይ ርካሽ ባህልን ለመጫ የሚደረገው ተግባር ለመከላከል የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ3ኛው የጂ- ፓወር ቲክቶክ ክርኤቲቭ አዋርድ ላይ "ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህልና ሥነ-ምግባር ባፈነገጠ አኳሃን ሰውነታቸውን የገላለጠ አለባበስ ለብሰው በአደባባይና በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ የታዩ" ተጠርጣሪዎችን ከነግብረ-አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
ግለሰቦቹ ወንጌላዊት ገብረ እንድርያስ በርሄ፣ በርከት ፀጋዬ ጅፋር፣ መቅድም ደረጄ መንግስቱ፣ ግሩም ገዛሀኝ ቀጭኔ እና ዮሃንስ መኮንን ሀ/ማርየም የተባሉ መሆናቸውን ፌዴራል ፖሊስ አመልክቷል።