10/08/2026
የማህበረሰብ ተወካዮች ጥረት አበረታች ምላሽ ያገኘ ሲሆን አፈጻጸሙ እንዲሳካ የሁሉንም አካላት ቁርጠኝነት ይጠበቃል
የጣርማ በር ሰፌድ ሜዳ መንገድ ፕሮጀክት በቆረጣ ምክንያት ከተቆፋፈረ በኋላ ግንባታው በመቋረጡ የመንዝ፣ የግሼ፣ የጣርማ በር እና አካባቢው ማህበረሰብ እያሳለፈ ያለው መከራ ክረምት ታክሎበት እጅግ ለከፋ ለሰው ሰራሽ ስቃይ ተዳርጓል። የኢኮኖሚ ድቀቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለታማሚ ህክምና ለነፍሰጡሮች የጤና አገልግሎት ማስገኘት አዳጋች ከሆነ ሰነባብቷል።
በዛሬው እለት ነሓሴ 4 ቀን ይህን የሚሊዮች መሰረታዊ አጀንዳ ይዘው የመጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ለሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት የህዝቡን ስቃይ በማስዳትና በመፍትሄዎች ምክክር ተደርጓል። የህዝብ ተወካዮቹ እና የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን አመራሮች ባደረጉት ውይይት መደበኛ የግንባታ ስራው እስኪጀመር መንገዱ ጊዜያዊ የጥገና ስራ እንዲከናወንና መግባባት ላይ ተደርሷል። ባለስልጣኑ በሙያተኛ፣ በበጀትና በግንባታ ግብአት ረገድ ዝግጁ መሆኑንና ወደስራ ለመግባት መወሰኑን ገልጾ ከማህበረሰቡና ከሁሉም ባለድርሻዎች ሊደረጉለት የሚጠበቁ እገዛዎችን በዝርዝር አስረድል።
የማህበረሰብ ተወካዮቹም ከዚህ የባሰ አንገብጋቡ አጀንዳ እንደሌለና ሁሉንም አቅማቸው በፈቀደ ህዝባዊ ድጋፍ እንደሚያስተባብሩ ቃል ሰጥተዋል። ከባለስልጣኑ ጋር የተደረገው ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የልኡካኑ አባል የሆኑ አዛውንቶች "ህዝባችን እንዲህ አይነት አበሳ የዛሬ 50 አመት እንኳ እንዳልገጠመው እና ለችግሩ መፍትሄ ካስገኘ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል" መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ ሲቃ እየተናነቃቸው ነበር።
ለረጅም ጊዜ ሲደረጉ የቆዩ እና እየተጠናከሩ የመጡት የህዝብ ንቅናቄዎች በዛሬው የውይይት አቅጣጫ መሰረት ወደተግባር ለመግባት ቁሳዊና ሞራላዊ ግብአቶች ናቸው። በመሆኑም በደብረብርሀንና በሸዋሮቢት ያሉ የመንገዶችና ትራንስፖርት ባለስልጣን አስተባባሪዎችና ሙያተኞች ከማህበረሰብ ተወካዮቹ፣ እና ባለድርሻዎች ጋር በመናበብ በአፋጣኝ ወደ ተግባር ለመግባት የተፈጠረውን መደላድል ተጠቅመው ወደአፈጻጸም መግባች ይጠበቅባቸዋል። ህዝብ ከፊት ቀድሞ እያስተባበረ ባለበት ሁኔታ መሬት ላይ የሚከወኑ የአፈጻጸሞች ስራዎች ቀላል ናቸው።
ሲጠቃለል ለህዝቡ ከዚህ የባሰ የነጻነትና የህልውና ጥያቄ ስለሌለ በምንም አይነት ሰበብ ኮምፕሮማይዝ የሚደረግ ጉዳይ እንዳይደለ የትኛው ባለድርሻ አካል ሊገነዘብ እና ችግሩ እንዲቃለል በተግባር የሚገለጽ አሻራውን ማሳረፍ ይኖርበታል።