
09/11/2025
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የተላለፈ መልዕክት
*****
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን የመልማት መብት ከማረጋገጥ አኳያ ካለው ትርጉም ባሻገር ሀገራዊ እና አህጉራዊ ደማቅ ምልክት ነው። ግድቡ ከጥንስሱ እስከመቋጫው ያሉ ሂደቶች ራስን የመቻልና የሉአላዊነታችን ምልክት እንዲሁም የኢትዮጵያዊያን የህብረብሄራዊ ትብብር አርማችን በመሆኑ ከፍ ያለ ትርጉም የምንሰጠው የትውልዱ ሜጋ ፖሮጀክት ነው።
በትውልድ ቅበብሎሽ የታነጸ፤ ጽኑዎች ብቻ ሊቋቋሟቸው የሚችሉ የማይቆረጡ ፈተናዎችን አልፈው ኢትዮጵያዊያን እውን ያደረጉት እና ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካዊያን የልማት ምልክት ከመሆኑ አንጻር የዚህ ትውልድ ዳግማዊ አድዋ ተደርጎ የሚወሰድ የታሪክ እጥፋት ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠናቆ ለምርቃት ሲያበቃ ቀጠናዊ ፋይዳ ያላቸው የልማት አውታሮችን የመገንባት እና አለም አቀፍ ሀብቶችን አልምቶ በፍትሀዊነት የመጠቀም እምቅ አቅሙን ለመላው አለም የተግባር ትምህርት እያስተማረ እንደሆነ አብን ይገነዘባል።
በግድቡ የግንባታ ሂደቶች ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶች በገጠሙ ወቅት ገቢራዊ የተደረጉ ስትራቴጂዎች፣ አፍሪካዊና ሰላማዊ የህግና የፖለቲካ ጥበቦችም ከዚሁ ጋር አብረው የሚታዩ ናቸው። ውጤቱም የቀጠናውን የውሀ ፖለቲካ የወደፊት እጣፈንታን የሚወስን ሆኗል።
በዚህ ሂደት ለምርቃት የበቃው የህዳሴ ግድብ አንዱ የዘመናችን አንጸባራቂ ድል ስለሆነ የዚህ ስኬት ባለቤት ለሆነው ትውልድ አብን ምስጋና ያቀርባል።
በመሆኑም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን እና መላ አፍሪካዊያን ዘመኑን የዋጁ ድርብርብ ብሄራዊና አህጉራዊ ድልችን ለማስመዝገብ የተግባርና የሞራል ስንቅ ሆኖ እንደሚያገለግል እንተማመናለን::
አለኝ የሚለውን ሁሉ አዋጥቶ የጋራ አሻራውን ላሳረፈው የጽናት ተምሳሌት ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለዚህ የድል በአል አደረሰህ እያልን የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለምርቃት እንዲበቃ ከኢትዮጵያ ጎን ለተሰለፉ- የአፍሪካ ህብረትን የመሳሰሉ ተቋማት እና ለመላው አለም የዲፖሎማሲ ማህበረሰብ አባለት አክብሮታዊ ምስጋና እናቀርባለን። አባይን ስንገድብ፤ ሀገራዊ የውስጥ ሰላማችንን በማደፍረስ ልማት እንዳናስብና በድህነት እንድንቆይ አልመው ይሰሩ ለነበሩ በተለይ ግብጽን መሰል ውጫዊ ሀይሎች የሽንፈት ጽዋ የተጎነጩበት መሆኑን በማወጅ፤ ለውስጣዊ ሰላማችን መመለስ ደግሞ ሁላችንም በተለይም መንግስት ከመቸውም ግዜ በላይ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል።
እንኳን አደረሰን፤ እንኳን ደስ አለን!
ሰለም ለኢትዮጵያ!
ጳጉሜን 04፥ 2017 ዓ.ም