08/02/2023
ትዕቢት ውደቀትን ትቀድማለች
ሁሉን የሚችል የሚመስለው ሰው አለ። በዙሪያው ባሉት ሰዎች ስለተሞገሰ በሁሉም የሚሞገስ የሚመስለው አለ። አጠገቡ ያሉት ስለተርበደበዱ ዓለም ሁሉ የሚርበደበድለት የሚመስለው ሰው አለ። በሀገራችን እየሆነ ያለው ይህ ነው። የማይነካውን ያስነካቸው ትዕቢት ነው። የማይገባበት ውስጥ ያስገባቸው እብሪት ነው። ልጅነታቸውን ትዕቢታቸው ስለሸፈነው ከአባቶች በላይ እንደሆኑ ተሰማቸው። የነሱ መንገድ ብቻ ስለታያቸው የቀድሞይቱን መንገድ መጠየቅ አቆሙ። የቆሙ ስለመሰላቸው ውድቀታቸው አልታይ አላቸው።
ሁሉን የሚችሉ ስለመሰላቸው ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ተዳፈሩ። በህዝብ እንባ ተሳለቁ ጎርፍ ሆኖ እንደሚወስዳቸው አልታይ አላቸው። በፈጣሪ የታመነውን ህዝብ በሰራዊታቸው ብዛት ታምነው ተዳፈሩት። አንገታቸውን ስላደነደኑ የአባቶችን አንገት አስደፍተው አስለቀሱ።
ትዕቢት በመንገዳቸው ቀደመች። ሞገስ የሆናቸው ፈጣሪ በነውር ስራቸው ተዳፈሩት። ቀናውን መንገድ ትተው ወደ የጥፋት መንገድን መረጡ። የማይነካውን ነኩ ፤ የማይደፈረውን ደፈሩ፤ በማይመጣበት መንገድ መጡ ፤ በነውራቸው አጌጡ።ከፍታችው ለንቀት መመረጣቸውን ለርኩሰት ተጠቀሙበት።
በቀረችው ጥቂት ጊዜ ወደ ልባቸው ካልተመለሱ የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው ይነዳል። ያደነደኑት አንገታቸው በድንገት ይሰበራል አወዳደቃቸውም ታላቅ ይሆናል። ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ ። ለሀጥአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፍል እንደሚባለው የመረጡት የጥፋት መንገድ ሀገራችንንና ህዝባችንን ይዞ ከመጥፋቱ በፊት ወደልባቸው ይመለሱ ዝንድ ጸሎት እና ምኞቴ ነው።
እውነት ሀይሉ