16/10/2025
"እናቴ ከሀገር አትበልጥም" በዓለምላይ ዋሴ
ለካ የጃውሳው የአጤ ካሣ የአጥንት ፍላጭ የጣልያኑ ጌታ የአባ ኮስትር በላይ የሥጋ ቁራጭ ናት!
ደጃች በላይን በየሻሽወርቅ አጤ ቴዎድሮስን በዓለማየሁ ለማባበል ተሞክሯል።
ቴዎድሮስ ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እና ለራሳቸውም ክብር ብለው ራሳቸውን መሥዋዕት ሊያደርጉ በተዘጋጁ ጊዜ እንዲታቀቡ ተለምነው ነበር። “እባክዎን በሚወድዱት ልጅዎ በልዑል ዓለማየሁ ይኹንብዎ፤ በራስዎ ላይ አይጨክኑ” እያሉ ተማጠኗቸው።
ጃውሳው ካሣ ግን ፡- “ለዓለማየሁ ምንም የማወርሰው ነገር የለም። ሲያድግ ግን አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በዐይኑ እንደዞረች ሞተ በሉት” አሉ።
የደጃች በላይ ክንድ እንደ እሳት የፈጃቸው ፋሺስት ጣልያኖች ልጁን የሻሽወርቅን አፍነው ወስደው መልእክት ላኩበት። እርቅ እናውርድ ልጅህንም ጎጃምንም እንስጥህ አሉት።
አባ ኮስትርም:- "የእናንተ ሀገር ሮም ነው ኢትዮጵያ ደሞ የእኔ። የእኔን ሀገር ከእናንተ አልቀበልም፤ አልወሰዳችኋትም እና። አትወስዷትምም። ልጄ የሻሽወርቅ ከኢትዮጵያ አትበልጥም፤ ለእሷም እግዚአብሔር አላት" በማለት ለምልጃ የመጡትን ባንዳዎች አስተናግዶ ወሬ ነጋሪውን ቱርጁማን መልሶላቸዋል።
በዓለምም ይኽን መሰል ልመና ቀርቦላት ነበር። በቲክ ቶክ ገጿ የተስተናገደ ሲኾን ነገሩ እንዲህ ነው። የኬኳ እናት በሚል ስም አስተያየት ሰጪዋ "እባክሽ ለእናትሽ ኑሪላት" የሚል ማባበያ ታቀርብላታለች። የጀግኖቹ መንፈስ ወራሿ በዓለም ግን መልሷ እንደ አባቶቿ ፈርጣማ እና ቁርጠኛ ነበር። እንዲህ ይላል:- እናቴ "ምንም ቢኾን ከሀገር አትበልጥም።" የሚገርም ጽናት በልጅነት። ባንዳን የሚያረግፍ ታላቅነት ከእውነት አንደበት።
እናቷን ጠልታ እኮ አይደለም። የዓላማ ጽናት ተራራ ላይ ስለወጣች እንጅ። የጸና አይደለልም። ወደኋላ አይመለስም። ሞትን እንደ ውኃ ይጠጣዋል እንጅ ለሞት አይንበረከክም።
ሞት ደመወዙና ክብሩ፣ ሥልጣኑና ክብሩ፣ ታሪኩና ግብሩ ነው።
የ፲፱ ዓመቷ በዓለም ዕድሜዋ ለጋ ቢኾንም ገድሏ ግን የአባቶቿን ያኽላል።
Abayneh Kassie Dn - ዓባይነህ ካሤ - ዲን