
18/01/2025
የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
አዲሱ የከተራና የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ዝግጅቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
አደባባዩ የዝግጅት ሁኔታ በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተጎብኝቷል።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ሁላችንም ከውኃና ከመንፈስ ዳግም የተወለድንበት የዲያብሎስ ሥራ የፈረሰበት አንድነታችን የታወጀበት መለያየት የተወገደበት ማያት የሚቀደሱበት በአጠቃላይ ምድራችን በቃል ኪዳኑ ታቦታት ኪደተ እግር የምትባረክበት ዕለት ነው።
ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደተባለው ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ከአደባባይ ጽኑስ እስከ ዙፋን ንጉሥ በነቂስ በመውጣት የቤተ ክርስቲያናችንን ታላቅነትና የሀገራችንን ታሪካዊነት የምናሳይበት የሕዝባችንን ፍቅር አንድነት የምንገልጽበት የሰላም የፍቅርና የአንድነት በዓላችን መሆኑን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ በዓላችን ነው።
በመሆኑም ይኽንን ታሪካዊና ዓለም አቀፋዊ የጥምቀት በዓል በነገሥታቱ መናገሻ በዐፄዎቹ መንደር በንጉሡ ቅን ፍርድ ከሰማይ ብርሃን በወረደባት ዘወትርም የክርስቶስ የፍቅር ብርሃን እንደ ፈሳሽ ውኃ በሚፈስባት በዓለ ጥምቀት በአዲስ ታሪካዊ አደባባይ በማክበር ሌላ ታሪክ ሊመዘገብ ጥቂት ሰአታት ቀርተውታል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ታሪካዊ አደባባይ በዓሉን ለማክበር የበቃችሁ ውድ ሕዝበ ክርስቲያን የታሪኩ ተካፋይ በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ።
አቡቀለምሲስ ሚዲያ በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያዊያን በዩቲዩብ ፣ በፌስቡክና በሌሎችም አማራጮች በቀጥታ ስርጭት ወደ እናንተ የሚያደርሳችሁ ይሆናል።