13/01/2026
ወንዝና ከተማ!
የአካባቢያችሁን ወንዞች አስቧቸው አሁን ምን ላይ ናቸው?
አዲስ አበባ ወንዟ ዳር የከተማ ሳፋሪ ዕውን አድርጋለች።
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም - ለድሬ ቲዩብ)
የት ነበር ዋኝታችሁ ያደጋችሁት? ቀበና ወይስ በሰቃ? ቦርከናዎች ናችሁ ባሮዎች? ወይስ ቀሃ የዋኛችሁ? ኩልፎ ነው ትዝታችሁ? አዌቱ? ቡልቡላ ነን የምትሉት ወይስ ደግሞ ጪጩ?
ለንደን በቴምዝ፣ ፓሪስ በሴይን፣ ካይሮ በናይል ላይ እንደ ደመቁት በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ ከተሞች እና አብዛኛዎቹ ዋና ከተሞች በወንዞች ዳርቻ ያደጉ ናቸው። የእኛስ የወንዝ ዳርቻዎች ብንል እነሱም ከተማ አፍርሰዋል ከተማውም ወንዞቹን አንጥፏል።
ያም ሆኖ ባለ ወንዝ ነን። ከተሞቻችን ከወንዝ አልራቁም። ዋኝተናል፣ አዋሽ እንኳን የስንት ከተሞቻችን ጌጥ ነው። የጎርጎ ልጆችን ያዝናና እስከ አቦ ምሳ ያጌጥንበት፣ የወረር መልክ፣ የሰዲ ገፅ፣ ከዱብቲና አሳይታ የማይነጠል።
እሺ ይርጋለም ያለ ወይማ ምንድን ነው? ማርቆስስ ያለ ውትርን? ኮሶኮል የሚዛን ወዝ አይደለምን? እኮ የት ነበር ወንዛችሁ? የትስ ዋኛችሁ? ላህ ለፍኖተ ሰላም መልኳ ነው። አምቦ በሁሉቃ ጥሟን ጭምር ቆርጣለች።
እኔ አንጅሶና አቃቂ እስከ ጀሞ የዋኘሁ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ። የወንዝ ውበትም የወንዝ ግማትም ጣጣው ምን እንደሁ አውቃለሁ። አሜሪካዊው ፕሮዲዩሰር Ted Turne "Rivers are places that renew our spirit, connect us with our past, and link us directly with the flow and rhythm of the natural world" የሚል አባባል አለው።
እርግጥ ነው ያ ልጅነታችን መንፈሱ በወንዞቻችን ይታደስ ነበር። ካለፈው ታሪካችን ጋር የሚያገናኙን እንደሆኑ ለመረዳት መለስ ብሎ ማጤን ነው። ልጅነታችን በቀጥታ ከተፈጥሯዊው ዓለም ፍሰት ጋር የተገናኘባቸው አንድ ስፍራ የአካባቢያችን ወንዞች ነበሩ።
ወንዞችና ከተሞች ጥልቅ፣ ታሪካዊ ትስስር አላቸው፣ ብዙውን ጊዜ በውሃ አማካኝነት ለምግብ፣ ንግድ፣ ትራንስፖርት ዓላማ የሚፈጠሩ ሰፈሮች፣ የከተማ እድገትን፣ ባህልን እና ኢኮኖሚን የሚቀርጹ ናቸው። ለእርሻ ልማት በሚል አዋሽ ወንዝ ዳርቻ የተፈጠሩ ከተሞች ዛሬ የዚህ ማሳያ ናቸው።
በሌላ በኩል የከተማ መስፋፋት ለወንዞች ብክለት ጦስ ነው። እኔ የዋኘሁበት የዘነበወርቁ አንጅሶ መጀመሪያ ተበከለ ቀጥሎ ደረቀ አሁን ተረት ሆነ።
ከተማና ቱሪዝም ፅንሰ ሐሳብ ነው። ከተማን ለመጠበቅ ወንዞችን መጠበቅ የሚለው ገኗል። አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻዋን ከጥፋት ጭቆና ነፃ አውጥታለች። እንደ አራዳ ፓርክ ያሉ ቦታዎች ቀድሞ ምን እንደነበሩ ለሚያውቅ አሁን ሲመለከታቸው ይደንቃል።
ከአምባሳደር ጀርባ የነበረውን አስታውሼ ዛሬ ቆም ብዬ እስከ ግዮን ስመለከት ወንዞችን አጥፍቶ ከመጥፋት ልማዳችን ያመለጥንበት አዲስ አብዮት ይደንቀኛል።
አዲስ አበባ የከተማ ሳፋሪ ልዩ ስፍራ ባለቤት ሆናለች። ሰሞኑን አዲስ አበባ ከምታስተዋውቀው ልማት አንዱ በወንዞች ዳርቻ የገነባችውን የከተማ ሳፋሪ ነው። አንዳንድ ሚዲያዎች የዱር ሳፋሪ ሲሉ ሰምቻለሁ። wilidlife safari "የዱር ሳፋሪ" ማለት እንስሳትን በተፈጥሮ ወይም ከፊል ተፈጥሯዊ መኖሪያዎቻቸው ውስጥ ለመመልከት የሚደረግ ጉዞ እና ዘመናዊ ኢኮ-ቱሪዝም ሀሳብ ነው። ለምሳሌ እንደ አምስቱ ትልቆች የምንላቸው የአፍሪካ ዱር እንስሳት መዳረሻዎች ዓይነት።
አዲስ አበባ ግን የከተማ ሳፋሪ city safari ወይም በሌላ መጠሪያው Urban Safari ነው የገነባችው። ሁለቱ በሳይንስም፣ በብያኔም፣ በይዘትም፣ በጠባይም ይለያያሉ። በጥቅሉ በቱሪዝም ቋንቋም ሆነ በሳፋሪ ብያኔ የዱር ሳፋሪ በተፈጥሮ፣ ሰፊ መኖሪያ (እንደ አፍሪካ ብሔራዊ ፓርኮች) እንስሳትን ለማየት የሚደረግ ጉዞ ነው።
የከተማ ሳፋሪ በአካባቢ ላይ የተመሰረተ ተጨማሪ የእንቅስቃሴ ተግባራት ምቹ ሁኔታዎች ያሉት ሁሉን አቀፍ መዝናኛ ነው። ለእንቅስቃሴ ምቹ ነው። ለምሳሌ የአዲስ አበባከው በእግርም በብስከሌትም በዊልቼርም ይጎበኛል።
በሌላ በኩል የከተማ ሳፋሪ እንደ ዱር ሳፋሪ አይደለም። ዱር እንስሳቱ በሰፋፊ ሜዳ ላይ እንደልብ የሚፈነጩ ባለመሆናቸው በቀላሉ የማየት ዋስትናው መቶ ፐርሰንት ነው።
የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ምቹ፣ ተደራሽ፣ ለቤተሰቦች በጣም ጥሩ፣ ወጪ ቆጣቢና ለመድረስ በጣም ቀላል ሲል የከተማ ሳፋሪን ይገልፀዋል። አዲስ አበባ ሌላ መልክ ይዛለች። ሌላ።