
28/05/2021
መረጃ ከሁሉም 20-09-13
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ሮበርት ጎዴክ አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠነቀቁ።
***********************************************
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ሮበርት ጎዴክ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት ተሳታፊዎች አካሔዳቸውን ካልቀየሩ አገራቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ልትወድ እንደምትችል አስጠነቀቁ። ኃላፊው በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ፊት ትናንት ቀርበው በኢትዮጵያ ቀውስ ላይ አገራቸው እየተከተለች ያለችውን የምላሽ አሰጣጥ አስረድተዋል።
ኃላፊው በቅርብ ሳምንታት የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት የጸጥታ ሁኔታ የሰብዓዊ ቀውሱን እንዳባባሰም ተናግረዋል። «የአሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትንተና የቀጠለው ግጭት ወደ ጠኔ የሚጠጋ ሁኔታ መፍጠሩን ያሳያል» ያሉት ጎዴክ በተመጣጠነ ምግብ እጦት እና በረሐብ ሰዎች ለመሞታቸው የተረጋገጠ መረጃ አለ ብለዋል። ውጊያ፣ የፍተሻ ኬላዎች፣ ሥርዓተ አልበኝነት እና በተዋጊ ኃይሎች ወከባ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች እንቅስቃሴ ችግር እንደገጠመው የተናገሩት ሮበርት ጎዴክ ለዚህም የዩስኤይድ አጋር ባልደረባ እና ሌሎች ሰባት የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች መገደላቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።
«ሙሉ የተኩስ አቁም፣ ሙሉ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እንቅስቃሴ፣ የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ጥበቃ እንፈልጋለን» ያሉት ኃላፊው የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ኃይሎች ለቀው ሊወጡ ይገባል ብለዋል። ቀውሱ በፖለቲካዊ መንገድ መፍትሔ እንዲበጅለት በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በደሎች እና የጭካኔ ድርጊቶች ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግ እና ፈጻሚዎች ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዲህ አይነት ውትወታ ሲያቀርቡ የመጀመሪያቸው አይደለም። በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አሜሪካ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በጸጥታ ተቋማት አመራሮች፣ በአማራ ክልል ኃይል እና በህውሓት አባላት ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሏን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። አሜሪካ ከቪዛ ማዕቀብ ተጨማሪ ለኢትዮጵያ የምትሰጣቸውን ዕገዛዎች ከልክላለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ እርምጃ አጥብቃ ተቃውሟል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የአሜሪካ መንግሥት እርምጃውን መለስ ብሎ እንዲያጤን በጠየቁበት መግለጫ «የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በገንዘብ፣ በዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ የሚቀየር» አይደለም ብለዋል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ሮበርት ጎዴክ ግን የትግራይ ግጭት ማቆሚያ ካልተበጀለት አገራቸው ተጨማሪ እርምጃ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ልትወስድ እንደምትችል ተናግረዋል።
DW Amharic