Multi Ethnic Shoa

Multi Ethnic Shoa ሸዋ የትልቋ ኢትዮጲያ ማዕከልነቱን እንዳስጠበቀ ኅብረ ብሄራዊ ክልላዊ አስተዳደር ይዋቀራል፡፡

ቡልጋድንቅ ምድር!ስለ ቡልጋ ምን ያውቃሉ? ቡልጋ ሲባል ወደ አዕምሮዎ ምን ይመጣል? ሀሳብዎትን ያካፍሉ።📷 Hilena Tafesse
12/07/2025

ቡልጋ

ድንቅ ምድር!

ስለ ቡልጋ ምን ያውቃሉ? ቡልጋ ሲባል ወደ አዕምሮዎ ምን ይመጣል? ሀሳብዎትን ያካፍሉ።

📷 Hilena Tafesse

የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማው ጮቄ ተራራ‼️ ~~~~~👉መገኛዉ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ነው፡፡ 4100 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ 👉በዋናነት ስናን፣ ደባይ ጥላት ግን፣ ሰዴ፣ ቢቡኝና ማቻከል ወረዳዎችን...
08/07/2025

የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማው ጮቄ ተራራ‼️
~~~~~
👉መገኛዉ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ነው፡፡ 4100 ሜትር ከፍታ አለው፡፡

👉በዋናነት ስናን፣ ደባይ ጥላት ግን፣ ሰዴ፣ ቢቡኝና ማቻከል ወረዳዎችን ያካልላል፡፡

👉ኢትዮጵያን የውኃ ማማ ከሚያስብሏት መካከል ጮቄ ተራራ ግንባር ቀደም ነው፡፡
👉 23 ትላልቅ ወንዞችና 273 ትናንሽ የዓባይ ገባሮች ከስሩ የሚፈልቁበት የውኃ ጋን ነው፡፡

👉ከፍተኛ ቅዝቃዜ አለው፤ በተለይም በክረምት ወራት ለተወሰኑ ሳምንታት በበረዶ ተሸፍኖ የሚቆይ ተራራ ነው፡፡

👉በበጋ ወቅትም ቢኾን በተለይ በታህሳስ ጧት ላይ በረዶ አይጠፋውም፡፡

👉ጮቄ በተፈጥሯዊ ገጽታው ውበትን የተቸረ፤ ሲያዩት መንፈስን የሚያረካ የተፈጥሮ ገፀ-በረከት ነው፡፡

👉አካባቢው በብዝሐ ህይወትም የታደለ ነው፡፡

👉ጮቄ ከ85 በላይ የሚኾኑ የዕፅዋት ዝርያዎችን የያዘ የተፈጥሮ አካባቢ ነው፡፡

👉ከነዚህም መካከል አስታ፣ አምጃ፣ አሸንግድዬ፣ ጅባራ፣ አይዳኝ፣ ግምይ፣ ጽድ፣ ኮሶና ኮሸሽሌ የመሳሰሉት ሲገኙ ከእንስሳት ዝርያዎች ደግሞ ነብርና ሌሎች የዱር እንስሳት ይጠቀሳሉ፡፡

👉የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራው ከ16 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት እና ከ41 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች እንዳሉት በጥናት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

👉በርካታ የወፍ ዝርያዎችም ይገኙበታል፤ ቅልጥም ሰባሪ የሚል ስያሜ ያለው የወፍ ዝርያ በዚሁ ተራራ የሚገኝ ነው፡፡

👉ብርቅዬዋ የቀይ ቀበሮ ታሪካዊ የመኖሪያ አካባቢ እንደነበረም ይነገርለታል፡፡

👉ጠቅላላ ስፋቱም ወደ 53 ሺህ 558 ሄክታር እንደሚደርስ በአካባቢው የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

👉የጮቄ አካባቢ የመሬት አቀማመጥ 86 ከመቶ ተራራማ፣ 1 ነጥብ 5 ከመቶ ሸለቆና 12 ነጥብ 5 ከመቶ ሜዳማ እንደኾነ በአካባቢው የተደረጉ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

👉ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ 61 ኪሎ ሜትር፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር 325 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

👉ከደብረ ማርቆስ ድጓ-ጽዮን ሞጣ የሚሄደው አንደኛ ደረጃ የጠጠር መኪና መንገድ እና ከድጓ-ጽዮን ፈረስ ቤት፣ ከደብረማርቆስ ቁይ፣ ቢቸና የሚያገናኙ አውራ መንገዶች ጮቄ ተራራን ለመጎብኘት የሚያስችሉ መንገዶች ናቸው፡፡

👉 የሚመቸዎትን መንገድ መርጠው ይጠቀሙ፤ ይህን ድንቅ የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ የተፈጥሮ በረከት ይጎብኙ፡፡

Visit Amhara

Amhara Culture & Tourism Bureau

አልዩአምባ፦ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የጉምሩክ ከተማ    የአንኮበር ታሪክ ሲዘከር የስምጥ ሸለቆ አካል የሆነችው እና የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የንግድ ማዕከል የነበረችው አልዩ አምባ የምትገኘው...
03/07/2025

አልዩአምባ፦ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የጉምሩክ ከተማ

የአንኮበር ታሪክ ሲዘከር የስምጥ ሸለቆ አካል የሆነችው እና የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የንግድ ማዕከል የነበረችው አልዩ አምባ የምትገኘው በአንኮበር ወረዳ ነው፤ የተመሠረተችው ደግሞ በ1266 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል፡፡ አልዩ አምባ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው ‹‹አልየ›› ከተባለ የአካባቢው ነጋዴ ሥም በመነሳት እንደሆነ ከአካባቢው የዕድሜ ባለፀጋ አባቶች እና ከወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህች ታሪካዊ ከተማ ከአዲስ አበባ 187 ኪ.ሜ፣ ከደብረ ብርሀን 57 ኪ.ሜ እንዲሁም ከአንኮበር ወረዳ ዋና ከተማ ጎረቤላ 15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

አልዩ አምባ ሞቃታማና ተስማሚ የአየር ንብረት የታደለች ከመሆኗም በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት ይገኙባታል፡፡ ቀደም ባለዉ ጊዜ ለሲራራ ንግድ ምቹ በመሆኗ በወቅቱ እስከ ዘይላ ወደብ ድረስ ተዘርግቶ የነበረው የሲራራ ንግድ ማዕከል ነበረች፡፡ በ1834 እና 1835 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የቀረጥ ውል የተፈረመው በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ነው። በአጼ ምኒሊክ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረጥ መሥሪያ ቤት ሲከፈት በአልዩ አምባ የጉምሩክ ጽሕፈት ቤት ሥራውን እንዲጀምር ተደርጎ ነበር።

በዚህም መሠረት በዘይላ ወደብ የንግድ መስመር በኩል ወደ ሀገራችን በሚገቡ የንግድ ዕቃዎች ላይ የቀረጥ ክፍያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረባትና የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የጉሙሩክ ከተማ አልዩ አምባ ሆነች፡፡ ከ1500 እስከ 1700 የሚጠጉ ግመሎች የአገር ውስጥ ሸቀጦችን ወደ ውጭ ያጓጉዙባት እንደነበርም ይነገራል።

በተጨማሪ በወቅቱ የነበረው የባሪያ ንግድ ቀረጥ መቅረጫ ነበረች፡፡ ለዚህም ማሳያው የባሪያ ንግድ ሲካሄድበት የነበረው አብዱል ረሱል በአልዩ አምባ ከተማ በቅርብ ርቀት መገኘቱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአልዩ አምባ ከተማ የአማራ፣ የአፋርና የአርጎባ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በፍቅር እና በአንድነት ይኖሩባታል፡፡ በመሆኑም አልዩ አምባ ትንሿ ሐረር በመባል ትታወቃለች፡፡ ከተማዋ በ19ኛው ከፍለ ዘመን በሲራራ ንግድ ማዕከል በነበረችበት ወቅት አራት በሮች ነበሯት፡፡ ሁለቱ በሮች መግቢያ ናቸው፤ አዋሽ በርና ጨኖ በር ይበላሉ፡፡

በሮቹ እንደ ጨው፣ ሻይ እና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ከዘይላ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡባቸው ነበሩ፡፡ ሁለቱ በሮች ደግሞ መውጫ በሮች ናቸው፡፡ በሮቹ አንኮበርና ምንጃር በር በመባል ይታወቃሉ፡፡ በአንኮበር በር ከመሀል አገር እስከ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል የንግድ ዕቃዎች የሚላኩበት ነበር፡፡ ምንጃር በር ደግሞ ወደ ደቡቡ የአገራችን ክፍል ሸቀጦች የሚላኩበትነው፡፡ ይህም የሆነው በወቅቱ ከተማዋ የጉሙሩክ ማዕከል በመሆኗና ዕቃዎች ከዚሁ አካባቢ ተቀርጠው ወደ ተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ስለሚሄዱ ነበር፡፡ በከተማዋ ከፐርሽያ፣ ከህንድና ከአረብ አገሮች የሚመጡ በርካታ የውጭ ዜጎች ይኖሩባት እንደነበርም ጎብኝዎች ጽፈውላታል። ስልክ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ከእንጦጦ እስከ አልዩ አምባ ድረስ መስመር ተዘርግቶለት ነበር፡፡ በከተማዋ እስካሁን ድረስ ‹‹ስልክ አምባ›› የሚባል መጠሪያ ያለው ሰፈር አለ፡፡ ይህም ስልክ ተተክሎበት የነበረበት ነው።

ይህን ታሪክ በማስታወስ ወደ ዘመናዊቷ አልዩ አምባ ደብረ ብርሃን እናቀናለን።

ደብረ ብርሃን ማለት ባንድ በኩል የብርሃን ተራራ ማለት ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ አፄ ዘርዐ ያቆብ የቅድስት ስላሴን ቤተ ክርስቲያን ያሰሩበትና በቤተ መቅደሱ ብርሃን ስለወረደበት ደብረ ብርሃን የሚለዉን ስም እንደያዘች ይነገራል። ከአልዩ አምባ በ57ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ።

ዘመናዊቷ የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከሏ፦ ደብረ ብርሃን የተቆረቆረችዉ 1449ዓም ገደማ በ15ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበር ሲሆን ዛሬ የአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ከተማ ናት። ቀደም ባለዉ ጊዜ የሽዋ ክፍለ ሃገር የጅሩ ሽዋ ሜዳ፣ የተጉለትና ቡልጋ አዉራጃ ዋና ከተማ ነበረች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢንቨስትመንት መናህሪያ የባለሃብቶች መርመስመሻ የሆነችዉ ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ በ132 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ደብረብርሃን ዉስጥ የሌለ ኢንቨስትመንት፣ የሌለ የንግድ አይነት የለም።

ብዙ ፋብሪካዎች፣ የሪልስቴት ግንባታዎች፣ የጠርሙስ ፋብሪካዎች፣ የእንሰሳት መኖ ማቀነባበሪያ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች፣ የወተት ልማት ማቀነባበሪያ ድርጅቶች፣ የፕላስቲክ ፋብሪካዎች እና ሌሎችም በርካታ ግዙፍ ፋብሪካዎች ይገኙባታል።

አዲሱ የአቶ በላይነህ ክንዴ የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ የሚገኘዉም እዚሁ ደብረ ብርሃን ነዉ። የኢትዮጵያ የኢዱስትሪና ልማት ማዕከል ነች።

ከተማ በለማ ቁጥር ወጣቱ ስራ ያገኛል። ስራ ያለዉ ገቢ ይኖረዋል። ቋሚ ገቢ ያለዉ የተመጣጠነ ምግብ ይበላል። ጥሩ የበላ ጥሩ ያስባል። ጥሩ የበላ ሀገርን ከፈተና የሚያድን አስተሳሰብ ያጎለብታል።

ሰላምና ልማት ለሀገራችን፣
ሰላምና እድገት ለህዝባችን

- ኢትዮጵያ

03/07/2025

#ምንጃሬ #ሸዋ

31/05/2025

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እነዋሪ ከተማ የሚኖረው ባለ ተሰጥኦው ዳዊት አድማሱ በሰራው " Walking Tractor" እርሻ በማረስ ላይ

ትግሬ ወያኔ የሸዋ ገዥ መደብ እያለ የጥላቻ  ዜማ ሲያወርድ ፣ሲገልና ሲያፈናቅል  በእጅና  በእግሩ እያጨበጨበ ይደግፍ  የነበረው  ጎጠኛ አካል አሁን ላይ በይፋ ሸዋን እዋጋለሁ  በሚል እብሪ...
06/05/2025

ትግሬ ወያኔ የሸዋ ገዥ መደብ እያለ የጥላቻ ዜማ ሲያወርድ ፣ሲገልና ሲያፈናቅል በእጅና በእግሩ እያጨበጨበ ይደግፍ የነበረው ጎጠኛ አካል አሁን ላይ በይፋ ሸዋን እዋጋለሁ በሚል እብሪት ሲያቅራራ ሪከርዶቹ ይፋ ሆነዋል። ይህ የሸዋ ልጆች አንድ እንዳይሆኑ ሌት ከቀን የሚደክመው አካል አካሄዱ ለአማራ ትግል ክፉ እንቅፋት ስለሆነ እውነተኛ አማራ ሊያወግዘው ይገባል ከዚህ ውጭ ግን ሸዋን አስገብራለሁ የሚለው ተራ ጉራ ዳር እንደማይደርስ ይታወቅ።

አቡነ ጴጥሮስ በኢጣልያኖች በአደባባይ ሲገደሉ ሂደቱ እና በዕለቱ የታዩት ክስተቶች ምን ይመስሉ ነበር?የጣልያንን ወረራ ለመከላከል በ1928 አዋጅ በታወጀ ጊዜ በወቅቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ...
05/05/2025

አቡነ ጴጥሮስ በኢጣልያኖች በአደባባይ ሲገደሉ ሂደቱ እና በዕለቱ የታዩት ክስተቶች ምን ይመስሉ ነበር?

የጣልያንን ወረራ ለመከላከል በ1928 አዋጅ በታወጀ ጊዜ በወቅቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጴጥሮሥ ንጉሠነገሥቱን ተከትለው ወደማይጨው ዘመቱ። በ1928 ሐምሌ 21 ቀን የተባበሩት የአርበኞች ግምባር አዲስ አበባ ላይ የሠፈረውን የጠላት ጦር ለመዋጋት በአደረገው ቀጠሮ መሠረት አቡነ ጴጥሮሥ በነደጃዝማች አበራ ካሣ ይመራ ከነበረው የሠላሌ ጦር አብረው ወደ አዲስ አበባ ገቡ።

ይህ ጦር ግን የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱን በመገንዘብ ወደመጣበት ሢያፈገፍግ አቡነ ጴጥሮሥ የአዲስ አበባን ህዝብ ሠብከው በጠላት ላይ ለማሥነሣት በማሠብ ከጦሩ ተለይተው አዲስ አበባ ቀሩ።ብዙም ሣይቆዩ አንድ ቀን ብቻ እንደቆዩ የጦር አለቆች ፊት ቀረቡ።

ብፁእነታቸው ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት 'ኮርየር ዴላሴራ' (corriere della sera) የተባለው ጋዤጣ ወኪል እና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው 'ፖጃሌ' የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓም አዲስ አበባ በነበረ ጊዜ ሂደቱን ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ፅፎ ነበር፦

"ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ ያለና መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡

ለፍርድም የተሠየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል 'ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም አንዲያምፁ አድርገዋል' የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም 'ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቂርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ አርስዎ ለምን ዐመፁ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?' ሲል ጠየቃቸው ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ''፡፡

'አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ለፈጣረዬ ብቻ የምናገረውን አናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ' አሉ፡፡ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእከት አስተላለፉ፦

''አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡ እንጂ በጎ ለመሥራት፣ እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ ። ነፃነታችሁን ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን።''

እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣሊያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጎም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጎመም፡፡ እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበበ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ሐላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቤ ተቀምጦ ስለ ነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለ ገለጠልኝ ነው፡፡ እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተስበስቡት ጣሊያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበበ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰማ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር"።ሆኖም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረበቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ ቀረ።

ቀጥሎም ብፁእነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ ርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ።ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣልያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሣ ታዘዘ።በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ስዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር።

ይሙት በቃ የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሞአቸው ስለ ነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው፡፡በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኩዋቸው። ብፁዕነታቸው እስከ መቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ የሆነ ፍጹም ቆራጥነት ይታይባቸው ነበር፡፡

የሀገራቸው በጠላት መወረር የሕዝባቸው መገደልና መታስር የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ ለመገደል ሊወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ስው እንዳይጎዳ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሔድ ከመካነ ፍትሑ 10 ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ። ከገዳዮቹም አንዱ 'ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉ?' ሲል ጠየቃቸው፡፡ 'ይህ የአንተ ሥራ ነው' ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ'፡፡ከመግደያውም ቦታ እንደ ደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ እድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ።

ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ ርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ 'ተኩስ' በማለት ትእዛዝ ሲስጥ ስምንቱም ተኩስው መቱዋቸው።ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡ የብፁዕነታቸው አስክሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በሚሥጢር አንዲቀበር ተደረገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ"

በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ "አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ" ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቆአቸው እርሳቸውም የሚከተለውን ተናግረዋል፦

"አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በሩምታ ተኩስው ገደሉዋቸው። ይህ እንደሆነ አስገድዶ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ። ማታ ከአስገዳዩ ኮለኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት 'በዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል' እለኝ 'እንዴት?' ብለው 'አላየህም ሲያጨበጭብ' አለኝ። እኔም 'ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል' አልኩት። 'እንዴት?' ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት።
እሱም አሳየኝ። ከዚህ በኋላ " የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቼአለሁ" ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ስዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተሰንጥቋል። መስቀሉም ልክ በመሐከሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል። የኪስ ስዓታቸውንም እንዳየሁት፡ እንደዚሁ ጥይት በስቶታል"

◆ምንጭ:-

1) ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን (ዲ/ን መርሻ አለሀኝ)
2) ታሪካዊ መዝገበ ሠብ (ፋንታሁን እንግዳ)!

ጓሳ ብቅ ሲሉ ይታያል ኤጎራ ጫማ ብገዛላት ሁለቱም የግራ ።በመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ የአልፋ ምድር ቀበሌ ስር የምትዳደረዋና በመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ረግረግ ከተባለው ቦታ ከነባሩ ...
04/05/2025

ጓሳ ብቅ ሲሉ ይታያል ኤጎራ
ጫማ ብገዛላት ሁለቱም የግራ ።
በመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ የአልፋ ምድር ቀበሌ ስር የምትዳደረዋና በመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ረግረግ ከተባለው ቦታ ከነባሩ ሎጅ በስተምስራቅ አቅጣጫ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው። በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር ጎብኝዎች የምትመረጠው የየጎራ አሰላቶና የፈረስ ላይ ውብ መንደሮችና የአካባቢያቸው መልከዓ-ምድር።

የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና መምህር ናቸው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሲታወሱ!የመጀመርያው የኢትዮጵያ የቀዶ ጥገና ሀኪም ናቸው፣በሀገራችን ከፍተኛ የህክምና ግልጋሎት የሚሰጥ...
04/05/2025

የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና መምህር ናቸው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሲታወሱ!

የመጀመርያው የኢትዮጵያ የቀዶ ጥገና ሀኪም ናቸው፣በሀገራችን ከፍተኛ የህክምና ግልጋሎት የሚሰጥበትን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን አቋቁመዋል፣ ፈረንጆች ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እርሳቸው ጋር ይታከሙ እንደነበር ይገለፃል፣ በሀገሬው ሰውማ በታዋቂ ቀዶ ጥገና ሀኪምነታቸው ምክንያት እስከ መመለክም ደርሰው ነበር ይላሉ አንዳንድ ፀሀፍያን፣ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ፣ የእንግሊዝ እና የዓለም ሀኪሞች ማህበር አባል እና መሪም ነበሩ፣ በቀዶ ጥገናው ዘርፍ ላበረከቱት በጐ አስተዋፅኦ አምስት ኒሻኖችን ተሸልመዋል፣ በ1983 ዓ.ም ከራሳቸው አንደበት እንደተደመጠው ቀዶ ጠጋኝ ሀኪምና መምህር ብቻ ሳይሆኑ አውሮፕላን አብራሪም ነበሩ፣ በዲያቆንነታቸውም ቤተክርስትያን አገልግለዋል፣ እረ ስፖርቱንም ችላ አላሉት ግብፅ ለትምህርት በነበሩበት ወቅት የራግቢ ተጨዋችም ነበሩ፡፡

የዚህና የሌሎች በርካታ አንቱ የሚያስብሉ መልካም ስራዎች ባለቤት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን አንቱ ብለን በክብር ታሪካቸውንና አስተዋፅኦዋቸውን እናነሳለን፡፡

ከ1933 ዓ.ም በኋላ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቀዶ ጥገና ሀኪም የሆኑት ፕሮፊሰር አስራት ወልደየስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታየ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍ ይዋሉ ፅጌ ሰኔ12 ቀን 192ዐ ዓ.ም ነበር በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡

ትውልዳቸው አዲስ አበባ ቢሆንም ያደጉት ድሬድዋ ነው፡፡ በድሬድዋ የህፃንነት ቆይታቸው የአብነት ትምህርት በመማር ዳዊት ደግመዋል፡፡ የድሬድዋ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ዲያቆን በመሆንም አገልግለዋል፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ማርሻል ግራዝያኒ ብዙ ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በግፍ ሲጨፈጭፍና፤ሲያስር ሰላባ ሆነው ህይወታቸውን ካጡት መካከል የያኔው የ 8 ህፃን ፕሮፌሰር አስራት አባት አቶ ወልደየስ አልታየ ይገኙበታል፣ አያታቸው ቀኝ አዝማች ፅጌ ወረደም ወደ ጣሊያን ሀገር በግዞት ተወስደው ታስረዋል፡፡

እናታቸው ወይዘሮ በሰልፍ ይዋሉ ፅጌም በምድር ላይ ብዙም አልቆዩም ነበርና የፕሮፌሰር አሥራት የልጅነት ጊዜ በሀሴት የተሞላ አልነበረም፡፡

በድሬድዋ ከአጐታቸው ጋር ከቆዩ በኋላ በ1934 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በ1934 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ቀጥለው በ1935 ዓ.ም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ፕሮፌሰር አሥራት በትምህርታቸው ያስመዘግቡ የነበረው የላቀ ውጤት ወደ ግብፅ ሄደው በቪክቶሪያ ኮሌጅ እንዲማሩ አስቻላቸው፡፡ ከዚያም ወደ እንግሊዝ በማቅናት የህክምና ትምህርታቸውን ኤዴንበርግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል፡፡ በእንግሊዙ ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ሰርጀን ቀዶ ጥገናን ለይተው /ሰፔሻላይዝ አድርገው/ በሙያው ተክነው ነበር ወደ ሀገራቸው የተመለሱት፡፡

በ1947 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በልዕልት ፅሀይ ሆስፒታል /በአሁኑ ጦር ሀይሎች/ መስራት ጀመሩ፡፡ ፈረንጆች ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በፕሮፌሰር አስራት ይታከሙ እንደነበር ይገለፃል፡፡ በታዋቂ ቀዶ ጥገና ሀኪምነታቸው በሀገሬው ሰው እስከ መመለክም ደርሰው ነበር፡፡

የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና መምህርም ሆኑ፡፡ ከመምህርነታቸው ባሻገር በሀገራችን ከፍተኛ የህክምና ግልጋሎት የሚሰጥበትን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን አቋቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ፣ የእንግሊዝ እና የዓለም ሀኪሞች ማህበር አባል እና መሪ የነበሩት ፕሮፌሰር አስራት፤ በቀዶ ጥገናው ዘርፍ ላበረከቱት በጐ አስተዋፅኦ አምስት ኒሻኖችን ተሸልመዋል፡፡

በ1950ዎቹ የጤና ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ቢጠየቁም የነፍስ ጥሪዬ የህክምና ሙያ ነው በማለት ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡

በደርግ ጊዜ ፕሮፌሰር አስራት የሶሻሊዝም ሰባኪ እንዲሆኑ ተፈልጐ እንደበርና እሳቸው ግን ፍላጎቱን ባለማሳየታቸው ከደርግ ጋር የተፈጠረው ቅሬታ ንጉሰ ነገስት ሀ/ስላሴ እንዴት እንደሞቱ ላላወቀው ህዝብ “በልብ በሽታ እንደሞቱ ተናገር” ፕሮፌሰር አስራት ሲባሉ አሻፈረኝ በማለታቸው ከደርጎች ጋር የለየለት ቅዋሜ ውስጥ ገቡ፡፡

የህይወት ታሪካቸውን አንፀባራቂው ኮከብ በሚል ርዕሰ የከተበው አቶ ጋሻው መርሻ እንደሚለው ፕሮፌሰሩ “ለደርግ ትዕዛዝ አሻፈረኝ በማለታቸው ወደ ሰሜን ግንባር ምፅዋ ተልከው እንዲገደሉ ተፈልጐ ነበር፡፡

ወታደሩን ለማከም ወደ ምፅዋ የሄዱት ፕሮፌሰር አስራት ለልብ ድካም ቢዳረጉም በጥይት ሳይመቱ ተመልሰዋል፡፡ “በህክምና ሳይንስ ጠላት የለም፡፡ ጃንሆይንም፤ የደርግ ባለስልጣናትንም ያለምንም ልዩነት አክማለሁ፡፡ ህክምና የሰውነት ስራ ነው” ይላሉ፡፡

ጃንሆይን ማከማቸው በደርግ እንደተጠላው ሁሉ፤ የደርግ ባለስልጣናትን ማከማቸው ደግሞ በነ ህዋኃት እና መሠል ድርጅቶች አልተወደደላቸውም፡፡ ደርግ ፊውዳላዊ አድርጐ ሲያሳድዳቸው፣ ኢህአዴግ ደግሞ ደርግ አድርጐ ቆጥሯቸዋል፡፡

ግንቦት 2ዐ ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ኢህአዴግ ሲቆጣጠር በሽግግር መንግስቱ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ከእነ አቶ መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም የብሄር ፌዴራሊዝም አስቸጋሪነቱን የኤርትራ መገንጠልም ለዘላቂ ሰላም እንደማይበጅ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ “ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚቅበዘበዙ ሁሉ እነሱ ቀድመው ይጠፋሉ፡፡” በሚለው ዝነኛ ንግግራቸውም ይታወቁ ነበር፡፡

አማራውን በጨቋኝነት ፈርጆ፣ ኢትዮጵያዊነትንም ጠልቶ የተጠነሰሰው የዘውግ ፖለቲካ ፕሮፌሰር ፈስራት ነሳኝ አሉ፡፡

አማራ ባለመደራጀቱ እረኛ እንደሌለው ከብት ተበትኖ የሀገር ውስጥ ስደተኛ ሆነ፣ ተፈናቀለ በማለት የህክምና ጋውናቸውን አውልቀው፣ ይጠሉት ወደነበረ የብሄር ፖለቲካ ገቡ፡፡
ጥር 1984 የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትን መሰረቱ፡፡ ፖለቲካውን ከተቀላቀሉ በኋላ በፕሮፊሰር አስራት ላይ ተደጋጋሚ ወከባ ይደርስባቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ በ1985 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩት 42 መምህራን መካከል ፕሮፌሰሩ ቀዳሚው ነበሩ፡፡

በዚህ ብቻ አላባራም በደብረ ብርሃን ከተማ ቀስቃሽ ንግግር በማድረግ እና ከጐጃም ገበሬዎች ጋር ለመፈንቅለ መንግስት አሲረዋል በሚል አምስት ዓመት ከ ስድስት ወር ተፈረደባቸው፡፡ በማረሚያ ቤት እያሉ ግፍና መከራን ተቀበሉ፡፡ ህክምናም ተከልክለዋል፡፡

የመሰረቱት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲያገለግላቸው እንዳልተፈቀደ አንፀባራቂው ኮከብ በሚለው መፅሀፉ የሚናገረው አቶ ጋሻው መርሻ ፕሮፌሰር አስራት 150 ጊዜ ፍርድቤት እንደቀረቡ ፅፏል፡፡ በመጨረሻ ከደከሙ በኋላ በመአህድ እና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥረት በ1991 ዓ.ም ለህክምና ወደ አሜሪካ ቢሄዱም ሊተርፉ አልቻሉም፡፡

አሜሪካ አርፈው አዲስ አበባ ባለወልድ ቤተክርሲቲያን ስርአተ ቀብራቸው በ1991 ዓም ተፈፅሟል፡፡

በመአህድ አማካኝነትም ለበጐ አድራጐት የሚተጋ የፕሮፌሰር አስራት ፋውንዴሽን ተቋቁሟል፡፡

“ፕሮፌሰር አስራት በህክምና፣ ሀገርን በመውደድ እና ራስን አሳልፎ ለህዝብ በመስጠት አርአያ ሰው ናቸውና ፋውንዴሽኑ ተገቢ ነው” ይላል የህይወት ታሪክ ከታቢያቸው አቶ ጋሻው መርሻ፡፡

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን በቅርብ የሚያውቋቸው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ
ፕሮፌሰር አስራት ኢትዮጵያን በተለየ መንገድ ይወዷታል፡፡ ስለሚወዷት ጎሰኝነትን አጥብቀው ይቃወሙ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ደፋር ነበሩ፡፡

የሚገርምህ ጃንሆይን በእስር እንዳሉ መርምረዋቸው ነበር፡፡ጤነኛ ሆነው አገኟቸው፡፡ወዲያው ግን ደርግ ገሎ ታመው እንደሞቱ መስክር አላቸው፡፡ደህና ነበሩ፡፡ ውሸት አልናገርም ብለው ደርግን ሞግተው ጃንሆይን ደርግ እንደገደላቸው ታወቀ፡፡

ያን ባያደርጉ ይሄኔ የደርግ ገዳይነት ተሸፍኖ ህዝቡ ጃንሆይ ታመው ሞቱ የሚለውን ያምን ነበር ሲሉ መስክረውላቸዋል፡፡

ስለ አበርክቶዎትና ስለመስዋዕትነትዎት ፕሮፌሰር አሥራት አንቱ ስንል እናከብርዎታለን!

A Man of his wordአቶ ግርማ የሽጥላ ደፋርና የመርህ ሰው ነበሩ፣ በውሳኔያቸው የሚፀኑ ትንታግ፣  ላመኑበት ሁሉ ግንባራቸውን የሚሰጡ ደፋር መሪ፣ ማዕበል የማያናውጣቸው የብረት አጥር፣...
29/04/2025

A Man of his word

አቶ ግርማ የሽጥላ ደፋርና የመርህ ሰው ነበሩ፣ በውሳኔያቸው የሚፀኑ ትንታግ፣ ላመኑበት ሁሉ ግንባራቸውን የሚሰጡ ደፋር መሪ፣ ማዕበል የማያናውጣቸው የብረት አጥር፣ የአባቶቻችንን ጥበበኛነት የወረሱ ዕውነተኛ የአባቶቻቸው ልጅ፣ የሚናገሩትን የሚተገብሩና በቃላቸው የሚገኙ መሪ በመሆናቸው አንዳንዶቹ A Man of his word ይሏቸዋል።

አቶ ግርማ የሽጥላ ውሳኔን ከጥሩ ድፍረት ጋር አጣምረው ሲወስኑ መባልን የማይፈሩ ተወዳጅ መሪ ናቸው። አቶ ግርማ እኛ ጥረት ካደረግን የማንለውጠው ነገር አይኖርምና ከልባችን ሰርተን ወደ ከፍታው እንውጣ በሚል መርህ ህዝብን ለማበልፀግ የሚሰሩ መሪም ነበሩ።

አቶ ግርማ ነገን የተሻለ በማድረግና የህዝብን ከፍታ ለማብሰር የሚተጉ ስክነትን የተላበሱና በቁርጠኝነት እየሰሩ ከሚገኙ የአማራ መሪዎች አንዱ መሆናቸው ለጠላት ተላላኪዎች የተመቸ ባለመሆናቸው በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የፅንፈኛ ቡድኖች ከተሰዋ ሁለት አመት ሞላው።

#ጀግናው

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ፤*****የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)  ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ክልላዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ሰ...
27/04/2025

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ፤
*****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ክልላዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅርቡ ባካሄደው 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተዋቀረው የብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ክልላዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አቋም የወሰደ ሲሆን ጉባኤውን ተከትሎም እንደ አዲስ መታገል ያለበትን የትግል ነጥቦች ነቅሶ ተነጋግሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን የተራዘመ ግጭት የገመገመ ሲሆን የአማራን ህዝብ ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ለመክተት ግጭት እየጠመቁ ያሉ እና የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲዘነጉ የሚያደርጉ ኃይሎች ን አሰላለፍ በመለየት አቋም ላይ ደርሷል።

ሁለት አመት ያስቆጠረው የአማራ ክልል የጸጥታ መታወክ ያስከተለው መጠነ ሰፊ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ፤ የህዝባችን መሰረታዊ ጠላቶች የሆኑ ውጫዊ ሀይሎች ጭምር ግጭቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተዋናይ እየሆኑ መምጣታቸው አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ በክልሉ በቀጠለው ግጭት በተኩስ ልውውጥ አያሌ ንጹሀኖች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ቆስለዋል፣ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ ፖለቲካ ውስጥ የሌሉ መምህራኖችና ተማሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተረሽነዋል፣ የባለሀብቶችና የታዋቂ ሰዎች ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል፣ ህዝቡ በተራዘመ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የአማራ ህዝብ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገም የነቃ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖረው እና ከአሁኑ የማህበረ-ኢኮኖሚ ፈተና ይልቅ የነገው እየከፋ አንዲመጣ በጠላቶቹና ተላላኪዎቹ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል። በዋናነት የአማራ ልጆች በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ምግባር ታንጸው ተወዳዳሪ እና ሐገር ተረካቢ እንዳይሆኑ እየተደረገም ይገኛል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው የተነሳ ህጻናት ልጆች ያለ እድሜ ጋብቻ ውስጥ እየገቡ እንደሆነ እና የህጻናት መደፈር ስለመበራከቱ መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ፡፡ ግጭቱ የጤና መሰረተ ልማቶችና በጤና አገልግሎት ላይ ሰፊ አደጋ በመጋረጡ በህክምና እጦት ህዝብችን ለሞትና ለማይድን ህመም እየተዳረገ ይገኛል፣ ወዘተ። በኢኮኖሚው ረገድ ሲታይ አቅም ያላቸው የክልሉ ባለሀብቶች ተሰደዋል፣ የሸቀጥ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ በመስተጓጎሉ የኑሮ ውድነት ተባብሷል፣ በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ የአማራ ክልልን ኢንቨስትመንት የመሳብ እምቅ አቅም እና የቱሪዝም ኢኮኖሚውን በመጎተቱ የህዝቡ የመልማት እድል እየተነጠቀ ይገኛልም፡፡ ይህም የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሚደረገውን ትግል አንዲደበዝዝ እያደረገ ሲገኝ ህዝባችንም ለአጠቃላይ የጸጥታ ስጋት ተዳርጎ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ይህንን ለመጭው ዘመን ጭምር የሚተርፍ ዳፋ ያለው ተግባር በማያሻማ ሁኔታ እያወገዝን ሁሉም የሚመለከተው አካል ይህ አይነትና መሰል ድርጊቶች በአፋጣኝ እንዲታረሙ እንዲታገል እና ህዝባችንን ለመታደግ እንደ አዲስ ለጀመርነው እንቅስቃሴ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ እናሳስባለን። እንዲሁም በውጊያ ቀጠና እና በከበባ (Hostage) ውስጥ የሚገኘው ህዝባችን ለከፍተኛ ሁለንተናዊ ጉዳት የተዳረገ ሲሆን ሁሉም ኃይሎች የንጹሀንን ከለላ በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ በጥብቅ እያሳሰብን ችግሩ በውይይትና የሰላምን አማራጭ በማስቀደም እንዲፈታ አበክረን እንመክራለን።

አብን የሀገራዊ ምክክሩ ስትራቴጂካዊ መፍትሄ የምናፈልቀበት አንዲሆን ይመኛል፡፡ በመሆኑም የብሄራዊ ምክክር ጉዳይ በብዙ ውትወታ እና የፖለቲካ ትግል የተገኘ ሀገራዊ መድረክ መሆኑ ታውቆ ህዝባችንን እንወክላለን የሚሉ ኃይሎች ሁሉ በሂደቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አደራ እያልን ይህንኑም በንቃት የምንከታተል መሆኑን አያይዘን እንገልጻለን።

በሌላ በኩል የአብን ስራ እሰፈጻሚ ኮሚቴ የአማራ ክልልን የወያኔ የጥፋት ድግስ የጨዋታ ሜዳ ለማድረግ ከዚህም ከዛም የተጣቀሱ ያልተቀደሱ ጋብቻዎች መፈጸማቸውንና የሚደረጉ የጦርነት ቅስቃሳና ፕሮፓጋንዳወችን በተመለከተ ጥልቅ ግምገማ አድርጓል፡፡ ወያኔ የፖለቲካ ትርክት፣ አደረጃጀት እና የህግ ማዕቀፍ ዘርግቶ፣ ተቋማት አቋቁሞ በአማራ ህዝብ ላይ ስርዓታዊ ግፍ ሲፈጽም የኖረ ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ የቅርብ ዘመን ታሪካዊ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ የአማራ ህዝብ ጠላት በ2017 ዓ.ም. ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁምራን አስመልከቶ ያንጸባረቀው የወራራ አቋም የህዝባችንን አንጻራዊ ነጻነት በኃይል የመንጠቅ እኩይ አላማን ያነገበ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በመሆኑም በተጠቀሰው አካባቢ ባለው የአማራ ህዝብ ላይ ዳግም ሊፈጽም ያለመውን የዘር ማጽዳት፣ የዘር ማጥፋትና በ2014 ዓ.ም ማይካድራ ላይ የተፈጸመን የጦር ወንጀል ዳግም የማስቀጠል አላማ እንዲያቆም አበክረን እንገልፃለን:። ወልቃይትን አስመልክቶ የወያኔ ትንኮሳና የጦርነት ቅስቀሳ ከሰብአዊነት ጉዳይና ከሀገራዊ ሰላምና ጸጥታ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ የሚከተለውን ጥሪ ለሚመለከታቸው አካላት አናቀርባለን፡፡

1. የፌደራሉ መንግስት እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ህዝብ ያገኘው አንጻራዊ ነጻነት፣ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት እንዲጸና እና አካባቢው የህወሃት የጦርነት አጀንዳ ሰለባ አንዳይሆን ከሰላም ወዳዱ ከወልቃይት ህዝብ ጎን አንዲሆን አበክረን አንጠይቃለን፡፡

2. በራያ አካባቢወች በህዝብ ትግል የተገኘውን ድል ማጽናት ያልቻለው መንግስት በፈጠረው ክፍተት የወያኔ ሀይሎች ዛሬም ድረስ ህዝባችንን በተራዘመ መከራ ውስጥ ያስገቡት ቢሆንም ህዝባችን ዕለት በዕለት መስዋዕትነት እየከፈለ ለነጻነቱ የሚያደርገውን መዋደቅ መንግስት እውቅና እንዲሰጠውና ለወያኔ የተጋለጠውን ህዝባችንን ህልውና እንዲያስጠብቅ እናሳስባለን።

3. የአማራና የትግራይ ህዝቦች የረጂም ዘመን ታሪካዊና ባህላዊ ቁርኝት ያላቸው መሆናቸው የማይሻር ሀቅ ሲሆን፤ በወያኔ ሃይል የተሳሳተ ትርክት ምክንያት የተፈጠረውን ነውረኛ ማህበራዊ አጥር (wall of shame) ማፍረስ እጅጉን ያስፈልጋል። እስካሁን የተፈጠሩ ቅራኔዎች በሰላማዊ መንገድ በሀቀኛ ውይይትና ድርድር እልባት እንዲያገኙ፤ የትግራይ ህዝብ ከወያኔ የ50 ዓመታት የነጣይ ትርክትና የአፈና ቀንበር መንጭቆ ነጻነቱን ለማወጅና አዲስ መስመር ለማስቀመጥ የሚያደርገውን የከበረ የትግል ጅማሮ እውቅና እየሰጠን ይገደናል ከሚሉ ሰላማዊ የትግራይ ሀይሎች ጋር ተቀራርበን የምንሰራ መሆኑን እንገልጻለን።

አብን ከአማራ ህዝብና ከቀጣናዊ የሰላም መረጋገጥ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም አንጻር በሻዕቢያ አሁናዊና የትላንትና ዘመን ሁኔታ ላይ ሰፊ ግምገማ አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ሻዕቢያ ከፍጥረቱ ጀምሮ ከአማራ ህዝብ ብሎም ከኢትዮጵያን የፖለቲካ ማህበረሰብ ህልውና አንጻር በበጎ ሊመዘገብለት የሚያስችል ታሪክ የሌለው ኃይል መሆኑ ይታወቃል። አሁን ላይም በአማራ ክልል እንዲሁም በኦሮምያ ክልል አንዳንድ አካባቢወች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ለማባባስ ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር የአጋርነት ዝንባሌ እንዳለው መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተቀጽላ በመሆን በሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ላይ ያለመታከት የሚሰራ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አጥብቆ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል:።

ትላንት ኢትዮጵያ በተዳከመችበት ዘመን ሻዕቢያና ወያኔ መሩ የጣምራ ሀይሎች የፖለቲካ መድረኩን በተቆጣጠሩበት ዘመን በተናጥል ስምምነት እና በሁለትዮሽ በመመሳጠር በሽግግር መንግስት ወቅት የተገንጣይነት አጀንዳውን የኢትዮጵያ ህዝብ ባልተሳተፈበት በቀላሉ እንዲያሳካ ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ፓርቲያችን አብን ኤርትራ የሚባለው ሐገር የተመሰረተበት ታሪካዊ ሂደት ቅቡልነት ላይ ጥያቄ ያለው ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ሐገራችን ታሪካዊ ይዞታዋ ከሆነው የባህር በር የተገፋችበት የሸፍጥ አካሄድ እንደገና ይፋና ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲያዝ ይጠይቃል።

በአጠቃላይ ግምገማም ሻዕቢያ የኢትዮጵያ እና የቀጠናው መልክዓ-ፖለቲካ (geopolitics) ጉዳዮች ከሰላማዊ ውይይትና ድርድር ይልቅ በግጭትና በጦርነት ብቻ መፈታት አለባቸው የሚል ሃላፊነት የጎደለውና አውዳሚ የሆነ ባህል እንዲንሰራፋ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት መቆየቱ፣ ኤርትራም ሀገር ከሆነች በኋላም ቢሆን ይሄን አመለካከት በፊታውራሪነት የሚያራምድ ሀይል መሆኑ፣ ባጠቃላይም በህዝቦችና በሀገራቱ መካከል ከፍትሃዊ አማካኝና ከትብብር ይልቅ ተናጥላዊ ጥቅምን በሴራ እና በሃይል የማስፈፀም እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ በዛው የቀረ ሃይል መሆኑ አለም ያወቀው ሀቅ ሆኗል።

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ግጭት በተመለከተ አሁይም አጽንኦት ልንሰጠው የምንወደው ጉዳይ ከታሪክ፣ ከፖለቲካና ከሞራል ፍልስፍና አኳያ፣ እንዲሁም አሁን ካለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር፣ "ጦርነት የችግሮች መፍቻ ብቸኛው መንገድ ነው" የሚለው ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑይ አስምረን እንገልጻለን። ይህንንም ከታሪካዊ እውነታዎች አንጻር ከተመለከትን ኤርትራ ከ1963 - 1983 ዓ.ም ለ 30 ዓመት ያካሄደው ጦርነት ለኤርትራ ህዝብ አምጥቶታል የሚባለው ነጻነት በተጨባጭ ሚዛን ሲለካ ህዝቡ ለሰፊ አፈና ከመዳረጉ በቀር ዛሬም ለነጻነቱ የሚታገል መሆኑ ግልጽ ነው። "ነጻነት" ተብሎ ከበሮ የሚደለቅለትም ታሪካዊ ክስተት የሻዕቢያን የጥቂት ግለሰቦችና የነሱን አምባገነናዊ አገዛዝ ከማፅናት ባለፈ ቅንጣት አዎንታዊ ፋይዳ እንዳሌለው፣ ይባስ ብሎም ተጨማሪ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና የሰዎችን ፍልሰት ያስከተለ መሆኑ የሚታወቅ ሀቅ ነው። ሌላው ታሪካዊ እውነታ በደቡብ ሱዳን የምናየው ሲሆን እንደዛው በጦርነት የተገኘው ነፃነት ከ10 አመት በላይ የዘለቀ የእርስበርስ ውጊያ ማስከተሉ እና ከ400,000 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።

አብን ኢትዮጵያ ከጦርነት አዙሪት ወደ ሰላም ማድረግ ስለሚገባት ሽግግር ላይ መክሯል፡፡ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ታሪኮች እንደሚስረዱት የብሄር ይዘት ያላቸው ግጭቶችና ጦርነቶች በማህበረሰቦች ግንኙነት ላይ አሉታዊ ጠባሳ ጥሎ ስለሚያልፍ በቀጣይ አብሮነት ላይ ተግዳሮችን የሚፈጥር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በህወሀትና ኦነግ ጥምረት በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጂም ዘመን የተገባበት የግጭት አዙሪት አስተማሪ ተሞክሮ የሚሆን ነው፡፡ በሚሊዬን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ከመሆኑም በላይ ባጠቃላይ የነበረው ዑደት የሚያስገነዝበው የግጭትና የጦርነት አማራጭ መቋጫ እንደማይኖረው አብን ይገነዘባል፡፡

በተለይ የብሄር ይዘት ያለው ግጭትና ጦርነት በማህበረሰቦች ግንኙነት ላይ አሉታዊ ጠባሳ ጥሎ ስለሚያልፍ በቀጣይ አብሮነት ላይ ተግዳሮት የሚፈጥር ነው። በዚህም ረገድ በህወሀትና ኦነግ ጥምረት በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጂም ዘመን የተገባበት የግጭት አዙሪት አስተማሪ ተሞክሮ እነንደሚሆን፣ በሚሊዬን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ከመሆኑም በላይ ባጠቃላይ የነበረው ዑደት የሚያስገነዝበው የግጭትና የጦርነት አማራጭ መቋጫ እንደማይኖረው ሲሆን መንግስትን ጨምሮ ሁሉም አካል ይህንን በማጤን ሀገራችንና ህዝባችን በዘላቂ እፎይታ ውስጥ እንዲገባ የልተሄደበትን መንገድ ሁሉ አሟጦ መጓዝ ያስፈልገናል።

እንደሚታወቀው በተለይ የርስበርስ ጦርነት አሸናፊም ተሸናፊ የሌለውና አጠቃላይ ድል ሊያጸና ማይችል፤ ይልቁንም ተጨማሪ ሞት እና ውድመት ከማስከተሉም በላይ ዘላቂ ቅራኔ የሚፈጥር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም ረገድ የቅርቡን ህወሀት መር ሁለት ዙር ጦርነት በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልል ህዝቦች ያስከተለው ሰብአዊ፣ ስልቦናዊና ቁሳዊ ቀውስ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡ "የሰላማዊ ትግል አይሰራም" በሚል አንዳንዶች የሚያራምዱት ሃሳብ ትክክል እንዳልሆነ በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህዝቦች የተደረገው ሰላማዊ ትግል የስርዓት ለውጥ ማምጣቱ በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን ሂደቱም በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የተሻለ መቀራረብንና የአንድነት መንፈስን የፈጠረ ነበር፡፡ ስለሆነም ከግጭትና ከጦርነት አዙሪት ለመውጣትና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሀገራዊ ውይይት ሂደቶች ጤናማነት፣ የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ማህበረሰባዊ የጋራ እሴቶችን ማጎልበት መጠቀም፣ እና የኢኮኖሚ እድሎችና መፍጠርና ማስፋት አንደሚያስፈልግ አብን ያምናል፡፡

የጦርነት አማራጮች በሂደትም ይሁን በመጨረሻ የግለሰቦችና የጠባብ ቡድኖች ጥቅም ማስፈፀሚያ የመሆን እድሉ ሰፊ ሲሆን ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የስልጣን ሽኩቻ መድረክ መሆኑ አንደማይቀር፣ ይሄን እውነታ በኤርትራ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩትና አሁንም ካሉት ሁኔታዎች በቀላሉ መገንዘብ እንደሚቻል አብን ሁሉይም ወገን እያስታወሰ "ጦርነት ክብር ይሰጣል" ለሚሉ አካላትም መልሱ "ጦርነት ክብር አይሰጥም፣ ጦርነት የሚያስከትለው ተጨማሪ ሞት እና ውድመት ብቻ መሆኑ"፣ በዚህም ረገድ ህወሀት መራሽ የሆኑት ሁለት ዙር የትግራይ ጦርነቶች ውድመት እንጂ ሰላም፣ አንድነት እና ክብር አላመጡም። ስለሆነም ሁልጊዜም ቢሆን የሰላም አማራጮችን በመከተል የግጭትና ጦርነት አዙሪትን መስበር እንደሚገባ አብን ሁሉይም ሀይሎች በአጽንኦት ማሳሰብ ይወዳል።

በተለይ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ከሌሎች የማህበረ-ኢኮኖሚ መስኮች ጋር አመጋግቦ በመስራት የሁላችንም አጀንዳ የሆነውን የህዝብን ሰላም መመለስ የሚቻልበት እድል አለ ብለን እናምናለን፡፡ የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ የህግ የበይነትን የማስፈን ስምሪቶች በህዝብን አመኔታና ተሳትፎ የታጀቡ በማድረግ፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራዎችን በሰላማዊ ኮሚዩኒኬሽን ማገዝና እና ይህን ክንውን ከማህበረ-ኢኮኖሚ መርሃግብሮች ጋር ማስተሳስር አንዱና ዋናው የሰላም መንገድ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በማህበረ-ኢኮኖሚው ዘርፍ የኢትዮጵያዊንን የጋራ ታሪኮችና የጋራ እሴቶች ለሰምና ለሀገራዊ አንድነት መጠቀም እና በግጭት ወይም በጦርነት ተሳታፊ አካላትን መቀነስ የሚያስችል የኢኮኖሚ አማራጮችን ማስፋት ብሎም የስራ እድሎችን መፍጠርን የሚመለከት ሲሆን መንግስት እና መሰል አካላት በነዚህ ቁልፍ ተግባራት ላይ አበክረው አንዲሰሩ አብን ጥሪ ያቀርባል፡፡

በመጨረሻም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ብሄራዊ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፓርቲው በቅርቡ ያካሄደው ደማቅ ጉባኤ የተመራበትን አካሄድና ዲሲፕሊን፣ የፈጠረውን ሰላማዊ መድረክ እና የተሰጠውን አመራር ያደነቀ ሲሆን ፓርቲው ራሱን ከውስጥ የትግል ጎታቾችና የሌላ አጀንዳ ተሸካሚወች ያጸዳበትን ሂደት "ታሪካዊና ቆራጥ" እርምጃ ሲል አውስቶታል። ጉባኤው በአባላትና ደጋፊወቻችን ዘንድ የፈጠረውን የታደሰ ተስፋና የትግል ቁርጠኝነት ስራ አስፈፃሚው ያደነቀ ሲሆን ይህም ለቁርጠኛ ትግል ስንቅ እንደሚሆነው ገምግሟል።

ብሄራዊ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ከወቅታዊ ጉዳዮች በተጨማሪም የፖርቲውን መዋቅሮች እና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተቀራርቦ ለመወያየት፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል በቀረበው እቅድ ዙሪያ በሰፊው ተወያይቶ አጽድቋል። በመጨረሻም ጠንካራ ሀገር እንዲገነባ፤ የአማራ ህዝብም ከገባበት ውስብስብ ችግር እንዲወጣ ራሱን መልሶ የማይናወጥ የልማትና የሰላም አለኝታ እንዲሆን ለማስቻል በምናደርገው የትግል ሂደት ይገደናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ ድጋፋቸውን እንዲሰጡን፣ በተለይ የፌዴራል መንግስት ትልቅ ሀላፊነት ያለበት እንደመሆኑ ሰላም እንዲሰፍን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የሰላም እድሎችን ሁሉ አሟጦ እንዲጠቀም ጥሪ እናቀርባለን።

ሚያዝያ 19/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ሽዋ ከተማ መራጭ ና አናጭ ፣ አዋጅ አስነጋሪ እና ዘማች። ሀገር እና ትዳርን ያቀናው ድንበር የለሹ ሸዋ ያስደንቃል። ሸዋ ከፍታው እና ዝቅታውን ኢትዮጲያ በምትባል ውብ ልኬት የሚለካ መሀሉ የ...
17/04/2025

ሽዋ ከተማ መራጭ ና አናጭ ፣ አዋጅ አስነጋሪ እና ዘማች። ሀገር እና ትዳርን ያቀናው ድንበር የለሹ ሸዋ ያስደንቃል።

ሸዋ ከፍታው እና ዝቅታውን ኢትዮጲያ በምትባል ውብ ልኬት የሚለካ መሀሉ የማይመረመር ህዝብ ነው።

ሸዋ አራሽ፣ አርብቶ አደር፣ ነጋዴ፣ አማኝ እና ጦረኛ ህዝብ ነው። ሸዋ እግረኛ፣ ተራማጅ እና አሻጋሪ ህዝብ ነው። ድልን እና ምርኮን፣ ንግስናን እና ስርዓተመንግስትን የሚያውቅ የመሀል እና የዳር ሀገር ህዝቦች ህብረት ስሪት።

ሸዋ የሀገር እና የአለም ኩራት! ሸዋ~ ሰብሳቢ ማንነት ነው።

ሸዋ ከአምስቱ ዋና ክፍለ ሃገራት ማለትም የሃበሻ ምድር ውስጥ አንዱ ነው። የግዛቱ ተራራማነት የተፈጥሮ መከላከያ በመሆን ከውጭ ወረራ ለመላ አገሪቱ ደጀን የነበረና በፍትህ የአስተዳደር ዝናውም ለሌላ የኢትዮጵያ ዜጋዎች መጠጊያና መሸሸጊያም ነበር።

#የዛሬን አያድርገውና የሽዋ ክፍል በትንሹ እነዚህን አውራጃዎች ያቀፈ ሰፊ ግዛት ነበር ።
ማለትም

ተጉለት እና ቡልጋ = ደብረብርሃን
ይፋትና ጥሙጋ = ኤፌሶን
ጨቦና ጉራጌ =ወሊሶ
ከምባታና ሃድያ =ሆሳዕና
ሀይቆችና ቡታጅራ =ዝዋይ
የረርና ከረዩ = ናዝሬት
መናገሻ =አዲስ አበባ
መንዝ እና ግሼ =መሃል ሜዳ
መርሐቤቴ =አለም ከተማ
ሰላሌ =ፍቼ
ጅባትና ሜጫ = አምቦ

#ይሁን እንጅ በአሁኑ የግዛት አስተዳደር በአማራ ክልል ስላለው ሽዋ ስናወራ ...20 ወረዳዎችና አራት ከተማ አስተዳደሮች ያሉት ዞን ነው ።እነዚህም

1.ደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር……….ደብረብርሃን
2.ባሶናወረና………………………………..ደብረብርሃን
3.አንጎለላና ጣራ………………………………..ጫጫ
4.አሳግርት ………………………………………..ጊናአገር
5.አንኮበር……………………...............…………ጎረቤላ
6.ሃገረማሪያም ከሰም……………………………ሾላገበያ
7.በረኸት……………………………………..መጥተህብላ
8.ኤፍራታግድም……………………………………አጣዬ
9.አንፆኪያ ገምዛ………………………………..መኮይ
10.መንዝጌራምድር…………………………….መሃልሜዳ
11.ግሼ………………………………………ራቤል
12.መረሃቤቴ………………………………አለምከተማ
13.ቀወት………………………………..ሸዋሮቢት
14.መንዝማማ ምድር……………………..ሞላሌ
15.ሞረትና ጅሩ……………………………..እነዋሪ
16.ምንጃር ሸንኮራ………………………….አረርቲ
17.ሚዳወረሞ……………………………..መራኛ
18.መሃልሜዳ ከተማ አስተዳደር………መሃልሜዳ
19.ጣርማበር…………………………………..ደብረሲና
20.ሞጃና ወደራ…………………………..ሰላድንጋይ
21.እንሳሮ………………………………………..ለሚ
22.አጣዬ ከተማ አስተዳደር………………….አጣዬ
23.ሲያደብርናዋዩ………………………………………..ደነባ
24.ዓለም ከተማ አስተዳደር……………….አለምከተማ
ከ17 ኛዋ መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ ሽዋን ያስተዳደሩ ነገስታት
አቤቶ ነጋሲ ክርስቶስ (1682- 1703 )
✡ መርዕድ አዝማች ሰባስትያኖስ (1703-1718)
✡ መርዕድ አዝማች ኪዳነ ቃል (አቡየ) (1718-1744 )
✡ መርዕድ አዝማች አምሃ እየሱስ (አምሃየስ) (1744-1775 )
✡ መርዕድ አዝማች አስፋወሰን (1775-1808 )
✡ መርዕድ አዝማች (ራስ) ወሰን ሰገድ (1808-1813)
✡ ንጉስ ሳህለ ስላሴ (1813-1847)
✡ ንጉስ ኃይለ መለኮት ( የእምየ ምኒልክ አባት) (1847-1856 )
✡ መርዕድ አዝማች ኃ/ሚካኤል (1856-1859 )
✡ በዛብህ (1860-1865)
✡ ንጉስ ምኒልክ (1865-1889 ) ) ናቸው ።

ሸዋ ከአቤቶ ነጋሲ ክርስቶስ ጀምሮ እስከ ንጉስ ምኒልክ (ንጉሰ ሸዋ) ድረስ ለሁለት ክ/ዘመን ያክል የተፈራረቁት የሸዋ ነገስታት የሸዋዎች ርስት ነው!!! የመጨረሻው ንጉስ ምኒልክ የመካከለኛው ዘመን የአባቶቻችን የአፄ አምደፅዮን፣ የአፄ ዘርዓያዕቆብ፣ የአፄ ዳዊት ርስት እና ግዛት ለማስመለስ የግዛት ማስፋፋት ያደረጉ ብቸኛው ንጉሰ ሸዋ ናቸው።

ይሁን እንጅ ዳሩ ውቅያኖንስ በማንኪያ ቢሆንብንም ስለ ሽዋ ልንናገር ልንመሰክርና እና ትውልዱም የአባቶቹን ገድል እየሰማ ፣እያወቀ ታሪክን ማስቀጠል ይችል ዘንድ ሀገርም ስሪቷን የረሳች ይመስላልና .....ለማስታወስና ወደ ከፍተዋ ልትመለስ የምትችለው የተሸመነችበትን ሸማኔዎቿን ስታከብር ፣ ያነጿትን አናፂዎቿን ማለትም ወርድና ቁመቷን በልኩ የሚያውቁትን ስታማክር ነውና ይህንንም ለመጠቆም ከታሪክ መዛግብት እያገላበጥን ሽዋን ልንዘክር የግድ ብሎናል ።

ከአሁን በኋላ "አኮማዳ " በሚል የመግቢያ ርዕስ ሽዋን እንዘክራለን
አኮማዳ ....

Address

Addis Ababa
WWW.MULTIETHNICSHOA.COM

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Multi Ethnic Shoa posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share