
13/10/2025
በአፋር ክልል በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ
- አንድ የ12 ዓመት አዳጊ ልጅ ሕይወት አልፏል
በአፋር ክልል፣ ኪልበቲ ረሱ ዞን፣ በርሃሌ ወረዳ ትላንት ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 43,456 ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ተሰማ። የመጀመሪያው ርዕደ መሬት ከደረሰበት ከትላንት ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም. ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ለስድስት ጊዜያት ያህል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን በርሃሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሁሴን ለ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል።
በወረዳው ካሉ ቀበሌዎች በርዕደ መሬቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው፤ ቡሬ እና አስ ጉቢ አላ የተሰኙ ቀበሌዎች መሆናቸውንም አቶ አሊ ገልፀዋል። በሬክተር ስኬል 5.6 በተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ በሁለቱ ቀበሌዎች በርካታ ቤቶችን ማፍረሱን ዘገባው አመላክቷል።
በዚህ ሳቢያ ከተፈናቀሉት ከ 43 ሺህ በላይ ሰዎች በተጨማሪ 6 ሰዎች መጎዳታቸውን እንዲሁም አንድ የ12 ዓመት አዳጊ ልጅ ሕይወት ማለፉን አስተዳዳሪው አስታውቀዋል። ከተጎጂዎቹ ውስጥ ሶስቱ ወደ በርሃሌ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። በትላንትናው ዕለት ከአፋር ክልል በተጨማሪ በትግራይ ክልል ሦስት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ነበር።
የመጀመሪያው 4.2 በሬክተር ስኬል የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ከመቐለ ሰሜን ምስራቅ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተ ነው። ሁለተኛው፤ ከውቅሮ ከተማ 32 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ቦታ ላይ ሲሆን 5.3 በሬክተር ስኬል የተመዘገበ ነው። ትላንት ማታ የተከሰተው ሦስተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ደግሞ በሬክተር ስኬል 5.6 ሆኖ የመዘገበ ነው