
10/06/2025
''አትሌት ከመጀመርያው አንስቶ የገጠማት ችግር ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም''
አትሌት መሠረት ደፋር
"ብዙ ገለቴዎች አሉ" አትሌት ስለሺ ስህን
ለሀገሯ ይህን ያክል ዋጋ የከፈለችው አትሌት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የገጠማትን ችግር ለመፍታት በፍርድ ቤት ስለመንከራተቷ በቅርበት አውቃለሁ ያለችው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር፤ ሕግ ለዚህች የሀገር ባለውለታ ትክክለኛውን ፍትህ እንዲሰጣት እጠይቃለሁ ብላለች።
መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ መሠረት ደፋር አሳስባለች ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
የኢትዮጲያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ "ገለቴ ቡርቃ አደባባይ ወጥታ ጉዳቷን ተናገረች እንጂ ሌሎች ተመሳሳይ በደል እየደረሰባቸው ያሉ አደጋ የደረሰባቸው ብዙ አትሌቶች አሉ" ሲል ተናግሯል።
ፕሬዝዳንቱ አክሎም "ፌደሬሽኑ ላለፉት 3 ወራት ይሄንን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ስንሰራ ነበር። አሁን ላይ አትሌቶችን ከአደጋ የሚከላከል ኢንስቲቲዩት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን አቋቁመናል ሲል ፕሬዝዳንቱ ተናግሯል።
ብዙ የተጎዱ አትሌቶች አሉ። ብዙ ገለቴዎች አሉን። በወንዶች አትሌቶች ላይም ጭምር ነው አደጋው ያለው። ይሄንን ለማስቀረት እየሰራን ነው ብሏል።
እኛ እንደ ፌደሬሽን ከገለቴ ጎን መቆማችንን ለማሳወቅ እንወዳለን። ለሌሎች አትሌቶችም ከጎናቸው እንዳለን የኢትዮጲያ ህዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን" ስለማለቱ ብስራት ራዲዬ ዘግቧል።