28/12/2025
*የአባይ ጮራ እና የሉዓላዊነት ማማ*
ታሪክ ሁሌም በጀግኖች ይጻፋል፤ ነገር ግን ታሪክን ሠርቶ ማለፍ ከፅሁፍ በላይ ይከብዳል። ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተተከለው ትልቁ የድል ሐውልት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።
ለዘመናት በግጥምና በዜማ "አባይ ማደሪያ የለውም" እየተባለ ሲዘፈንለት የነበረው ወንዝ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዘመን ቤቱን አገኘ። የግድቡ ውሀ መሞላት እና የኤሌክትሪክ ማመንጨት ጅምር፣ የኢትዮጵያውያንን የራስ መተማመን ከፍታ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው። ይህ ድል የኢንጂነሪንግ ውጤት ብቻ አይደለም፤ ይህ "የማይቻል የሚመስለውን የመቻል" ስነ-ልቦናዊ ድል ነው። ጨለማን በብርሃን የመተካት፣ ድህነትን በልማት የማሸነፍ ጽኑ ቆራጥነት ማሳያ ነው።
በዲፕሎማሲው መድረክም ቢሆን፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ (BRICS) አባልነት ስትቀላቀል እና በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ድምፅዋን ስታሰማ፣ የነበረው ጉዞ ቀላል አልነበረም። ውጣ ውረዶች፣ ጫናዎች እና ፈተናዎች ቢበዙም፣ መርከቧን በማዕበል ውስጥ አሽከሽኮ ለወደብ የማብቃት ጥበብ ታይቶበታል። ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በስንዴ ልማት ያሳየችው አስደናቂ ተአምር፣ ከለማኝ እጅ ወደ ሰጪ እጅ የመሸጋገር ጉዞ ወርቃማ ምዕራፍ ነው።
እነዚህ የድል ዓመታት፣ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ "እችላለሁ" ያለችበት፣ በአባይ ላይ ፊርማዋን ያኖረችበት እና የነገን ብርሃን በራሷ አቅም የለኮሰችበት የፅናት ዘመናት ናቸው።