
05/05/2024
ሀላባ : በጎርፍ የ5 ሰዎች ሕይወት አለፈ
| በሀላባ ዞን በትላንትናዉ እለት ነፋስና በረዶ ቀላቅሎ በጣለዉ ከባድ ዝናብ ባስከተለዉ ጎርፍ የ5 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ፖሊስ ገለፀ
ሆሳዕና ሚያዚያ 27 ቀን 2016 (ማ.ኢ.ፖ.ኮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀላባ ዞን ነፋስና በረዶ ቀላቅሎ በጣለዉ ከባድ ዝናብ ባስከተለዉ ጎርፍ 5 ሰዎች ተወስደዉ ህይወታቸዉ ማለፉ የዞኑ ፖሊስ ገለፀ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በጠፋዉ የሰዉ ህይወት ማዘናቸዉን ገልፀዉ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
በዞኑ በዌራ ዲጆ ወረዳ በሁሉም ቀበሌያት ከባድ ዝናብ በመጣሉ አካባቢዉ በጎርፍ መጥለቅለቁ ነዉ የተገለፀዉ።
በወረዳዉ በበንዶ ጮሎክሳ ቀበሌ (3)ሰዎች በኡደና ጮሎክስ (1) ሰው በሀለባ ቁሊቶ በገለቶና በገደባ መሀል (1) ሰው በአጠቃለይ ( 5)ሰዎች በጎርፍ የተወሰዱ ሲሆን ሲሆን የሶስት ሰዎች አስክሬን በፍለጋ ሲገኝ የሁለት ሰዎች አስክሬን ያልተገኘ በመሆኑ ፖሊስ ከአካባቢዉ መሀበረሰብ ጋር በመሆን የሟቾችን አስክሬን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሀይለኛ ወጀብና በረዶ የተቀላቀለበት ዝናብ በመጣሉ ምክንያት 5 ሰዎች ህይወታቸዉን በጎርፍ አደጋ ምክንያት በማጣታቸዉ በእጅጉ ማዘናቸዉ የገለፁት የሀላባ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሙህድን ሁሴን ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
ዋና አስተዳዳሪዉ አክለዉም ሀገራዊና ክልላዊ የዝናብ ትንበያ መረጃዎችን ከመከታተል ባለፈ በዞናችን የተለያዩ መዋቅሮች ሊኖር የሚችለውን የዝናብ/አየር ሁኔታዎች በመገናዘብ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።
በታጁ ነጋሽ(ምክትል ኮማንደር)