16/10/2025
ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ከምናምን የፃፍሁልሽ ግጥም
አንች የኔ ኮከብ አንች የእኔ ጨረቃ
ሌሊት ስድስት ሰአት ከ45 ደቂቃ
ድንገት ገድ ቀንቶኝ ከእንቅልፌ ስነቃ
ከበ'ሬ ደጃፍ ላይ ሰማሁኝ ሙዚቃ
ምን ይላል መሰለሽ
"መሄዱንስ ሂጂ አልከለክልሽም
በሴቱም ሴት አለ እናቴ አይደለሽም
እህቴ አይደለሽም"
ይህ ገራሚ ሀሳብ ይህ ጥዑም ሙዚቃ
በደረቀው ሌሊት
ቤቴን እና ልቤን ደጋግሞ ሲደቃ
ላዜምልሽ ሳስብ
ድምፅህ
ውሻንም አይጠራ ብለሽኛል ለካ
ያኔ
ቃልሽን ባከብርም ከቤቴ ሳትወጭ
ዛሬ አብረሽኝ የለሽ
ይኧው አዜምሁልሽ ምናባሽ ታመጭ
መሄዱንስ ሂጂ አልከለክልሽም
በሴቱም ሴት አለ እናቴ አይደለሽም
እህቴ አይደለሽም"
(በዜማ ነው)
ይህ ጥዑም ሙዚቃ
ወደውስጤ ገብቶ ቀርጥፎ ሲበላኝ
የት እንደሰማሁት ብዙም ትዝ የማይለኝ
"ገደል ግቢ" የሚል ግጥም አስታወሰኝ
ይህንን ቃል ስልሽ
ገደል ግቢ ይላል ብለሽ አታስቢ
ክፋሽን አልስማ ገደልስ አትግቢ
ግን
በዚህ ድቅድቅ ምሽት በጥቁሩ ጨለማ
የጉዳቴ መጠን ለእግዜር እንዲሰማ
ሳጥናኤል በጆሮሽ
ነግቶልሻል ተነሽ
በሚል ሹክ ብሎሽ
ቀውሶ ሰአትሽ
የነጋልሽ መስሎሽ
በፍጥነት ሩጭ ከቤትሽ እርቀሽ
ከዛ
ከአውላላ ሜዳ ላይ አስር ጅብ ይክበብሽ
መኖር ግራ ይግባሽ ጭንቀትን ተጎንጭ
መሄጃው ጠፍቶብሽ
በቆምሽበት ቦታ ደጋግመሽ እርገጭ
የእንባ ሳግ ይነቅሽ በለቅሶ ፍረጭ
የሲኦልን ፍዳ
ከሰማይ ሳትሄጅ ከዚህ ምድር ጠጭ
እንዲህ ከሆንሽ ሗላ
የእግዜር ምህረት ደርሶ
ከዚህ ጭንቀት ውጭ
እንዲህም የምልሽ
የአንችን ክፉ ማየት ስለማልውድ እንጅ
እንደስራሽማ
ገደል መግባት ቀርቶ
አስር ጅብ ቢበላሽ ያንስብሻል ላንች።