16/02/2026
አንበሳው ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን
✍️
በሰሞኑ የሐበሻ ዑለሞች ዐቂዳ የጋራ አቋም ዙሪያ ማስረጃ ማቅረብ የገደዳቸው ወገኖች መነፅራቸውን ወደ ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን አዙረዋል። በርግጥ ለሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን ከመቆርቆር እምርታ የመነጨ እንዳልሆነ አይሰወርም። እንደተለመደው ብዥታዎችን በማስረጃ ከማጥራት ይልቅ የሌሎችን ስብዕና በማጉደፍ የሐገሪቱ ብቸኛ ሱፊይ ለመሆን መዉተርተር ይዘዋል።
ዳሩ ግን ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን ከሌሎች ዑለሞቻችን በተለየ መልኩ አሏህን "ጅስም" ብሎ መጥራትን በተመለከተ “ቀላዒዱልፈዋኢድ” በተሰኘ የተዉሒድ ኪታባቸው ከገፅ 23-24 ላይ አግራሞትን የሚያጭር የሆነን ትንታኔን አስቀምጠዋል።
➜ልብ ይበሉ ያብራሩት አሏህን ጂስም ነው ብሎ ስለማመን አይደለም ፤ ጅስም ብሎ ስለመጥራት ነው። መጥራቱ ከተከለከለ ማመኑ እርም መሆኑ ለማንም አይሰወርም።
ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን አንድ ሰው አሏህን ከአካል ባህሪያት አጥርቶ ማለትም አንዳንድ ከራሚያዎች ጅስም ስንል መዉጁድ[ያለ ነው] ለማለት ፈልገን ነው እንደሚሉት “ጅስም” ብሎ ቢጠራ ስህተት ላይ የወደቀ ይሆናል በማለት አስቀምጠዋል ፤
فإِنْ سَمَّاهُ أَحدٌ جسمًا وقالَ لا كالأجسامِ يعني في نفيِ لوازمِ الجِسميَّةِ كبعضِ الكرَّامِيَّةِ حيثُ أطلقَه عليه تعالى بمعنى موجود فإنَّمَا خطؤُه في إطلاقِ الاسمِ بالإجماعِ.
"አንድ ሰው አሏህን አካል (ጂስም) ብሎ ቢጠራውና ነገር ግን እንደ አካላት ያልሆነ ካለ ፤ ማለትም እንደ አንዳንድ ከራሚያዎች የአካልነትን ባህሪያት በመካድ 'አካል' የሚለውን ቃል 'ያለ ነው' (መውጁድ) በሚል ትርጉም ብቻ ቢጠቀመው ስህተቱ ስሙን በመጠቀሙ ላይ ብቻ መሆኑ በሊቃውንት ስምምነት የታወቀ ነው።"
እንግዲህ ስንልም የነበረዉ ይህንኑ ነው። አንድ ሰው አሏህ አካል ነው ግን አካልን አይመስልም ሲል ያለ ነው ግን ያሉ ነገራቶችን አይመስልም ለማለት ፈልጎ ከሆነ አይከፍርም። ነገር ግን ስህተት ላይ የወደቀ ይሆናል። ምክንያቱም ጂስም የሚለዉን ቃል ለአሏህ መጠሪያ ስም አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችል ሸሪዓዊ መረጃ ስላልተገኘ ነው በማለት ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል ፤
فإنه لم يوجَد في الكتابِ والسُّنَّةِ ما يُسَوِّغُ إطلاقَه لِيَجُوزَ على قولِ القَائلِين بالاشتِقَاق في الأسماءِ وهم المِعتزلةُ والقاضي الباقِلَانيُّ من أئمَّةِ الأشاعرةِ، ولِأَن الشرطَ بعد السَّمعِ أن لا يُوهِمَ نقصًا، واسمُ الجسمِ يَقتضيه مِن حيثُ اقتِضاؤُه الافتقارَ إلى أجزائه الَّتِي تَرَكَّبَ منها وهو أعظمُ مقتضٍ للحُدوث.
"ምክንያቱም በቁርኣንና በሐዲስ ውስጥ ይህን ስም ለመጠቀም የሚያስችል ማስረጃ አልተገኘም። ስሞች በኢሽቲቃቅ ይወጣሉ በሚሉት ሙዕተዚላዎችና እንደ ቃዲ አል-ባቂላኒ ያሉ የአሽዐሪያ መሪዎች ዘንድም ቢሆን መረጃ ሳይኖር አይፈቀድም። በተጨማሪም አንድን ስም ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታው ስሙ ጎዶሎነትን የማያመላክት መሆን አለበት። አካል[ጅስም] የሚለው ስም ግን ከአካላዊ ክፍሎቹ የመገንባት ባህሪን ስለሚይዝ ጉድለትን ያመለክታል። ይህ ደግሞ ለፍጡርነት ትልቁ ማሳያ ነው። "
ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን ጂስም[አካል] የሚለዉ ቃል የፍጡራን መለያ በመሆኑ አሏህ በዚህ ስም ለመጠራት የተገባ አይደለም በማለት አስረግጠዋል። ነገር ግን አንድ ሰው ጂስም[አካል] ሲል ምንም ነገር ሳያስብ አሏህን አካል ብሎ ከጠራ ይከፍራል የሚለው የዑለሞች አቋም ሚዛን ይደፋል ሲሉ እንዲህ ፅፈዋል፤
فمَن أطلقَهُ فهُو عاصٍ كما قال الكمال في المُسايرة ثم قال فيها بل كفَّرَه بعضُهم يعني رُكن الإسلام واستظهَر أي الكمالُ هذا القولَ فقال وهو أي التَّكفيرُ لِمَن أطلقَه أظهَرُ مِن عدمِ التكفير له.
“ይህን ስም የተጠቀመ ሰው አል-ሙሳይየራ በተሰኘው ኪታብ ላይ ከማል ኢብን ሁማም እንደገለጹት ወንጀለኛ ነው። እንዲያውም ሩክኑል ኢስላምን የመሳሰሉ ከፊል ሊቃውንት እንዲህ ያለውን ሰው በኩፍር ፈርጀውታል። አል-ከማልም ይህንኑ ንግግር በማጠናከር ይህን ስም ለተጠቀመ ሰው የክህደት ፍርድ መስጠቱ ካለመስጠቱ የበለጠ [አዝሃር] ነው ብለዋል።"
ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን ይህንን ሁሉ ካሉ በኋላ አንድ ሰው ጂስም የሚለዉ ቃል ጎዶሎ ባህሪያትን የሚያመላክት መሆኑን ካወቀ በኋላ ከተጠቀመው ግን በዑለሞች የጋራ ስምምነት ከእስልምና ይወጣል በማለት መድና ቀለማቸውን እንዲህ ሲሉ አዛምደዋል።
فإنَّ إطلاقَه مختارًا بعد عِلمِه بما فيه مِن اقتِضاء النَّقصِ استخفافٌ بجَناب الرُّبُوبِيَّةِ والاستخفافُ به كفرٌ وِفاقًا.
"አንድ ሰው ጅስም በሚለው ቃል ውስጥ ያለውን የጉድለት ትርጉም እያወቀ በምርጫው[ሳይገደድ] ይህን ስም መጠቀሙ፣ የጌትነትን ክብር ማሳነስ ነው። ጌትነትን ማሳነስ ደግሞ በዑለሞች የጋራ ስምምነት ክህደት ነው።"
አበልቃሲም በኪታባቸው ፍንትው አድርገው የተጅሲምን አስከፊነት ሰድረዉልናል። አይደለም አሏህን አካል ነው ብሎ ማመን አያከፍርም ሊሉ ይቅርና የአካልን ትርጉም ካወቁ በኋላ አሏህን አካል ብሎ መጥራት በዑለሞች የጋራ ስምምነት ከእስልምና ያስወጣል ብለዋል።
እንደ መወጣት ፤ መውረድ ፤ ባትን መግለጥ እንዲሁም አካላዊ የሰዉነት ክፍሎችን ለአሏህ የሚያረጋግጡ ሰዎችን ሙስሊም ለማለት የነፈዘ ህሊናን ይጠይቃል። በነገራችን ላይ ሸይኽ ታጁዲን ይህንን ኪታብ የፃፉት ሸይኽ ዑመር ኢማም ከመወለዳቸው በፊት ነበር። ይህንን ያልኳችሁ በለመደ ምላሳቸው ሸይኾቹን “ተጀንጅነው ነው” እንዳይሉብኝ ስለ ሰጋሁ ነው።
ሰሞኑን የተያዘው የሙጀሲም-ወሃብያ ጥብቅና ከሐገራችን ዑለሞች ኪታብ ምንም እዉቅና የለዉም። በእርግጥ የሐገራችን ዑለሞች ከቁርኣን ፤ ከሐዲስ እንዲሁም ከዑለሞች የጋራ ስምምነት[ዒጅማእ] ያፈነገጠ አቋምን አላሰፈሩም። አለ የሚል አካል በማስረጃ መሞገት ይችላል።
ሁሉ ነገራቸውን ሰዉተው ለእስልምና እየመከቱ ያሉ ወንድሞቻችንን ተክፊር በሚል የዳቦ ስም ለማሳደድ የሚደረገው ኢ-ሰበዐዊ እንቅስቃሴ አግባብነት የለዉም። ዑለሞቻችን የታሪክ ኪታብን ሲፅፉ እንኳን እስልምናን ከሚያበላሹ ነገራቶች ከማስጠንቀቅ ወደ ኋላ አላሉም ።
ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን “ኢዕላሙል አግቢያ” በተሰኘ ኪታባቸው ገፅ 701 ላይ አንዳንድ ጫት የሚቅሙ ሰዎች ከእስልምና የሚያስወጡ ፀያፍ ድርጊቶችን ይፈፅማሉ በማለት እንዲህ ኮንነዋል፤
وفي بعض تعظيمهم للقات كفر صريح كطلب المغفرة منها واعتقاد أنها مؤثرة.
"አንዳንዶች ለጫት ካላቸው የተጋነነ አክብሮት የተነሳ ከጫት ምህረትን መጠየቅ እና ጫት ጥቅምና ጉዳትን ይፈጥራል ብሎ ማመን የመሳሰሉ ግልጽ ክህደት (ኩፍር) ውስጥ ይወድቃሉ።"
ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን የታዘቡትን ሐቅ ያለ ምንም ማለባበስ አስቀምጠዋል። ምህረት የሚለመነው አሏህ ሆኖ ሳለ ጫትን ምህረት የሚጠይቁ እንዲሁም ጫት ጥቅምና ጉዳትን ይፈጥራል ብለው የሚያምኑ ሰዎች ሙስሊም አይደሉም ሲሉ ደምድመዋል።
ለመሆኑ ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን ይህንን በማለትዎ ተክፊር ይባሉ ይሆን ? ወይንስ የሚከፍረው ጫቱ ነው ?
ከዚህ በተጨማሪ ሸይኽ ቃሲም ታጁዲን “በህጃ” የተሰኘውን የአባታቸዉን ኪታብ ሲያሳትሙ ሙሐመድ ሐሚዲን አግዟቸዋልና እኛን አትውቀሱን አይነት እይታን ለማንፀባረቅ ተሞክሯል። ሲጀመር ኪታቡ የታተመው ከ21 አመት በፊት ነው። ለመሆኑ ያን ጊዜ ሙሐመድ ሐሚዲን ወሓብያ ነበር ወይ? መረጃ ካላችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ። እንደ አጠቃላይ ግን ሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲንን ሆነ ልጃቸውን ሸይኽ ቃሲም ታጁዲንን እንደማታዉቃቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዑለሞቻችን ያላችሁ የተንሸዋረር እይታ ትዉልድን ይበክላል።
የዛሬውን ሐሳቤን እዚህ ላይ ገታ እያደረኩ በአባዬ ሾንኪይ ስር ለመሸሸግ ያደረጋችሁትን ጥረትና የሙዐዉያን ጉዳይ አረሳሁትም ፤ በሌላ ፅሁፍ እመለሳለሁ ።
ለዛሬው ግን ከላይ ያለዉን የሸይኽ ሙሐመድ ታጁዲን አቋም ትቀበሉት ይሆን ?