24/07/2025
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀደም ሲል ሰርተነው ለነበረው የዜና ዘገባ ተከታዩን ማስተካከያ ልኳል 👇
***
የ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብሩ ጉዳይ!...
የኢትዮጽያ ንግድ ባንክ በጠንካራ የውስጥ አሰራሩ በሕገ ወጥ መንገድ በባንኩ በሚገኙ 10 ሂሳቦች ተላልፎ የነበረ 7.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ሳይደረግ ማዳን መቻሉን ገልጿል። የድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይም በስልጣን አላግባብ የመገልገል የሙስና ክስ ተመስርቷል።
***
ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በሕገወጥ መንገድ ከባንኩ የውስጥ ሂሳብ በባንኩ በሚገኙ ሌሎች ሂሳቦች በማስተላለፍ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ሲሞክሩ ባንኩ ደርሶባቸው ገንዘቡን ተመላሽ ቢያደርግም በድርጊቱ በተሳተፉ 14 ግለሰቦች ላይ በሥልጣን አላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል ዋና አድራጊነትና የልዩ ወንጀል ተሳታፊነት ክስ ተመስርቷል። የወንጀል ክሱ የተመሰረተውም በ3 የባንኩና 2 የደህንነት ሠራተኞች በ9 ሌሎች ግብረአበሮቻቸው ላይ ነው።
ከተከሳሶቹ መካከል በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ የንፋስ ስልክ ዲስትሪክት የኮንዶሚኒየም ብድር ክትትል ባለሙያ አቶ ደጉ አሸናፊ በየነ ፥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወለጋ ሆሮ ጉዱሩ የሆሮ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ተፈሪ ዲንቄሳ በለጠ፣ አቶ እሱባለው ሽመልስ በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ የኢፕሊኬሽን ኦፊሰር፥ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የኢኮኖሚ ኢንተለጀንት ኦፊሰሮች መሀመድ ነጋሽ ገሰሰና ንጉሱ ኡምሩ ጉሪኖ ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የለሚ ኩራ ክፍለ ለተማ ስራና ክህሎት ጽ/ቤት የሥራ ስምሪት ባለሙያ አቶ ገብረሃና አለሙ ቸሩ፥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽ/ቤት የፕሮጀክት ዝግጅትና ሃብት ማፈላለጊያ ባለሙያ አቶ አንተነህ ካሳ መኮንን፥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽ/ቤት የፕሮጀክት ዝግጅትና ሃብት ማፈላለጊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ሸዋዬ እንዳለማውም እንደሚገኙበት በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቃቤ ሕግ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ክስ ያስረዳል፡፡
ሌሎች ሙሉጌታ ቀሪዓለም ደሴ፣ ሞላ ሽፈራው እጅጉ፣ ኤባኤል ተሻተ ፣ አንተነህ ካሳ መኮንን፣ ገላና አዴሳ ቦና የተባሉ ተከሳሾች በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ የሚኖሩ ናቸው።
እንደ ክስ መዝገቡ በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ይሰሩ የነበሩ በክስ መዝገቡ የተጠቀሱ ሠራተኞች ከሌሎች በክሱ ከተካተቱ ግብራበሮቻቸው ጋር በመሆን፥ በሥልጣን አላግባብ በመገልገል የጥቅም ትስስር በመፍጠር በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ 3 የውስጥ ተቀማጭ ሂሳቦች ላይ ከሰባት ነጥብ አምስት (7.5) ቢሊዮን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ በባንኩ ወደሚገኙ የተለያዩ የ10 ግለሰቦች ሂሳቦች ውስጥ ገቢ በማድረጋቸው ነው ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት ስልጣንን አላግባብ በመገልገል በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ወንጀል ተሳታፊነት የተከሰሱት።
በክስ መዝገቡ የተካተቱ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሥራና ክህሎት ጽ/ቤት የስራ ስምሪት ባለሙያዉ አቶ ገብረሃና አለሙ ቸሩ ከሌሎች በክሱ ከተጠቀሱ በግል ስራ ከሚተዳደሩ 3 ተከሳሾች ጋር በ 2017 አመተ ምህረት በጥር እና የካቲት ወራት በተለያዩ ጊዜያት ይህንን ገንዘብ ከባንክ እንዴትና በማን አማካኝነት እንደሚያወጡ ሲነጋገሩ ቆይተው ባንኩ ለሕጋዊ ሥራ በስጠው የሂሳብ ማንቀሳቀሻ ይለፍ ቃልን ተጠቅሞ ያለ ሕጋዊ አግባብና ሥልጣን ገንዘቡን ተቀናሽ አድርገው ወደ ሌሎች አስር ሂሳቦች ቢያስተላልፉም ባንኩ በዘረጋውን ጠንካራ የውስጥ ቁጥጥር ገንዘቡን ወጪ ሳያደርጉ በፊት ወደ ትክክለኛው የባንኩ የውስጥ ሂሳቦች ተመላሽ መደረጉን ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።
ይህ የባንኩ ሰራተኛ ከባንክ ተቀማጭ ገንዘብ በአቶ ኢያሱ ለማ ፀጋዬ ስም ወደተከፈተ የባንክ ሂሳብ አምስት ሚሊየን (5,000,000)ብር ገቢ በማድረግ፥ ሌሎች በክስ መዝገቡ የተጠቀሱ ሁለቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት የኢኮኖሚ ኢንተለጀንስ ሰራተኞችም ሁኔታዎችን በማመቻቸት በአቶ እስራኤል ደገፋ ስሜ ስም በተከፈተ ሁለት የተለያዩ አካውንቶች በድምሩ አራት ቢሊየን (4,000,000,000) ብር ገቢ በማድረግ፥ አቶ ጌታቸው ተገኝ አባዳማ በሚሰኝ ስም አንድ ቢሊየን (1,000,000,000)ብር እንዲሁም የአቶ ግዛቸው ዳምጠው ባለቤት በሆኑት በወ/ሮ ያለምዘርፍ ቢተው ገሰሰ ስም በተከፈተ እና ተከሳሹ በውክልና በሚያስተዳድሩት የባንክ ሂሳብ ቁጥር ሰላሳ ሚሊየን (30,000,000) ብር በተጨማሪም በተከሳሽ አቶ ሞላ ሽፈራው እጅጉ ስም በተከፈተ ሂሳብ ሁለት ቢሊየን (2,000,000,000)ብር፥ በክስ መዝገቡ በተካተተ ተከሳሽ ግዛቸው ዳምጠው ሽፈራው ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ አምስት መቶ ሚሊየን (500,000,000) ብር ገቢ በማድረግ፥ በአፍራ መሳሊክ ወይም አርዝቱልስ ኢምፖርተር ስም ሀመሳ ሚሊየን ሚሊየን (50,000,000) ብር እና በአቶ ሙባረክ ሀሰን አብዱ ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ቁጥ አንድ መቶ ሚሊየን (100,000,000) ብር በሕገ ወጥ መንገድ በባንክ ይሰሩ የነበሩ ተከሳሾች ሁኔዎችን በማመቻቸት የተጠቀሰውን ከሰባት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ አስተላልፈው ተገኝተዋል በሚል በክስ መዝገቡ ተገልጿል።
በአጠቃላይ ተከሳሶቹ ከፍተኛ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ለማስወጣት አስቀድመው በማዘጋጀት የማይገባቸውን ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ የተጠቀሰውን ገንዘብ በማስተላለፍ በፈፀሙት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ሁሉም ተከሳሾች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጸረ ሙስና ወንጀል ችሎት ቀርበው የዋስትና መብታቸው ተነፍጎ ጉዳያቸውን በማረሚያ ሆነው በመከታተል ላይ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ በሕገወጥ መንገድ ከባንኩ 3 የውስጥ ሂሳቦች በዚያው በባንኩ ወደሚገኙ 10 የተለያዩ ሂሳቦች ቢያስተላልፉም ባንኩ በዘረጋው ጠንካራ የውስጥ ቁጥጥር ከተላለፈው ገንዘብ ላይ ምንም ወጪ ሳይደረግ የተደረገው ማስተላለፍ ተቀልብሶ ገንዘቡ ወደ ነበረበት ትክክለኛዎቹ የባንኩ የውስጥ ሂሳቦች ተመላሽ መደረጉን ባንኩ መግለፁ ይታወሳል።