17/04/2023
በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ችግር ላይ መሆናቸውን ገለፁ፡፡
በአገሪቱ ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ሐይል መካከል በሱዳን መዲና ካርቱም የተነሳው ግጭት በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ችግር ላይ እንደጣላቸው በስፍራው የሚገኙ አንድ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮ ኢንሳይደር ተናገረዋል፡፡ ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት ኢትዮጵያዊያኑ በአሁኑ ስዓት በግለሰቦች ቤት ተጠልለው እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
በአቡድልፋታህ አልቡርሃን የሚመራው የሰዱን ጦር እና በሀምዳን ዳጋሎ በሚዘወረው የፈጥኖ ደራሽ ሐይል መካከል የተቀሰቀሰው ‹ የከተማ ግጭት › ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ የ100ሰዎችን ሕይወትን መቅጠፉ ተዘግቧል፡፡
በካርቱም የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያኑ ሁለቱ ሀይላት እየተዋጉ ያሉት ከተማ ውስጥ በመሆኑ ‹ ነገሩን ከባድ › አድርጎታል ባይ ናቸው፡፡ እኚሁ ኢትዮጵያዊ የሚመለከታቸው ሲሉ የጠሯቸው አካላት ከካርቱም መውጣት የሚችሉበትን መንገድ እንዲያመቻቹላቸው ጠይቀዋል፡፡
በካርቱም የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኤምባሲው ‹ ከግጭቱ ጋረ በተያያዘ ሊያጋጥም ከሚችል አደጋ ራስን መጠበቅ አስፈላጊ › መሆኑን አስታውሶ ‹ ኢትዮጵያዊያን ከግጭት አካባቢዎች በመራቅ፣ ከእንቅስቃሴ በመቆጠብ ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ› አሳስቧል፡፡
ኢትዮ ኢንሳይደር