20/07/2024
አቡነ ጴጥሮስ
በ1880 በሸዋ ክፍለ ሀገር፣ ፍቼ የተወለዱት አቡነ ጴጥሮስ፣ ከአርበኞች ጋር ለነጻነት ትግል ሲያካሂዱ ተይዘው፣ በስምንት የጣሊያን ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ በአደባባይ በግፍ የተረሸኑት፣ የዛሬ 86 ዓመት ነበር፡፡
በ1920 ከእስክንድሪያ ቤተ ክርስቲያን በይፋ ማዕረገ ጵጵስናን ከተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ አራት ኢትዮጵያውያን አንዱ የኾኑት አቡነ ጴጥሮስ ከ1928 እስከ 1933 ለአምስት ዓመታት በዘለቀው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ለጠላት አንበገርም በማለት ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ክብር የሰጡ ሰማዕት ናቸው፡፡
ቀዳሚው የመጠሪያ ስማቸው ኃይለ ማርያም ሲኾን፣ ከገበሬ ቤተሰብ ነው የተወለዱት፡፡ ሀገራዊውን የቤተ ክህነት ትምህርት በደብረ ሊባኖስ ገዳም የተማሩት አቡነ ጴጥሮስ በ1908 ገደማ ነበር ሥርዓተ ምንኩስና የፈፀሙት፡፡
አቡነ ጴጥሮስ በጎጃም (ዋሸራ)፣ በጎንደር እና በቦሩ ሜዳ በሚገኙ ገዳማት ውስጥ ኖረዋል፡፡
የመምህርነት ሕይወታቸውን ወሎ፣ ሳይንት በሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም ቅኔ እና መጻሕፍት በማስተማር የጀመሩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ኋላ በቤተ ክህነት የማስተማር ብቃታቸው ተመስክሮላቸው ወላይታ ወደሚገኘው የደብረ መንክራት ገዳም ተዛውረዋል፡፡
… በ1916 በዝዋይ ሐይቅ ደሴት ላይ ለሚገኘው የደብረ ማርያም ገዳም በዋና መምህርነት ተመደቡ፡፡ በ1919 ደግሞ በገነተ ልዑል ግቢ በሚገኘው የመንበረ ልዑል ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መምህር ኾነው የተመደቡ ሲኾን፣ በዚያም የደጃዝማች ተፈሪ (ኋላ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሤ) የነፍስ አባት ኾኑ፡፡
እውቀታቸው፣ ለሃይማኖታቸው ያላቸው ቀናዒነት እና ከንጉሣዊው ቤተሰብ ጋር የነበራቸው ቅርበት፣ በ1920 ለጵጵስና ከተመረጡት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አንዱ ሆነው ለመመረጥ አስችሏቸዋል፡፡ “ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ሞአ” በሚል ማዕረግ፣ በሀገረ ግብጽ፣ እስክንድሪያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ገዳም ማዕረገ ጵጵስና ተቀበሉ፡፡ ከዚህ በኋላ፣ አቡነ ጴጥሮስ የሀገረ ስብከታቸውን ዋና ጽሕፈት ቤት ደሴ ላይ በማድረግ፣ የመንዝ አውራጃ እና የወሎ ክፍለ ሀገር ጳጳስ ኾነው ተሾሙ፡፡
በ1927 ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወርር፣ በዘመኑ እንደነበሩት አብዛኞቹ የቤተ ክህነት ሰዎች፣ አቡነ ጴጥሮስም ከአጼ ኃይለሥላሤ ጋር ወራሪውን ለመመከት ወደ ማይጨው ዘመቱ፡፡ ሆኖም የወራሪው ጠላት ኃይል አይሎ፣ ንጉሡ ሀገር ጥለው ሲወጡ፣ አቡነ ጴጥሮስ ከአርበኞች ጋር ለመቆየት ወሰኑ፡፡
መቀመጫቸውን በደብረ ሊባኖስ ገዳም በማድረግ፣ አርበኞች ለሀገራቸው ነጻነት የሚያደርጉትን ተጋድሎ ያደፋፍሩ ነበር፡፡
ሐምሌ 20 ቀን 1928 አቡነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፋሺስት ጦር ከመዲናዋ በአራት አቅጣጫ ለማጥቃት ሲወጠን አቡነ ጴጥሮስ የዕቅዱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በዕቅዱ ከመሳተፍ ባሻገር ራሳቸውም ጠብመንጃ ታጥቀው ከበስተ ሰሜን በኩል ጥቃት ከሚሰነዝረው የሰላሌው የአርበኞች ቡድን ጋር ተቀላቀሉ፡፡
በዕቅዱ መሠረት ጥቃቱ ሲፈፀም በተካሄደው ከባድ ውጊያ በጠላት ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረስ ቢችሉም፣ በደጃዝማች አበራ ካሳ የሚመሩት የሰላሌ አርበኞች እና ሌሎችም ቡድኖች ማፈግፈግ ግድ ሆነባቸው፡፡ በማፈግፈግ ላይ ሳሉ ግን፣ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያኖቹ እጅ ላይ ወደቁ፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 1928 በመሃል አዲስ አበባ፣ ዛሬ የስማቸው መጠሪያ በኾነው አካባቢ፣ በስምንት የኢጣሊያ ወታደሮች የእሩምታ ተኩስ በአደባባይ ተረሸኑ፡፡
ዮሐንስ አምባቸው
አዲስ አበባ