18/09/2025
የሳውድ እና የፓኪስታን ስምምነት ወታደራዊ ዝግጅት ወይስ ሁለንተናዊ ትብብር ?
ሳውድ አረቢያ እና ፓኪስታን በታሪክ ወሳኝ የተባለውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት ወሳኝ የተባለ እስትራቴጂካዊ ወታደራዊ ስምምነት ሲሆን በአንድኛቸው ላይ የሚደርስን ማንኛውም ወታደራዊ ጥቃት በሌላኛው ላይ እንደደረስ ይቆጠራል ይላል።
ሪያድ ተገኝተው ስምምነቱን የተፈራረሙት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የሪያድ በመከላከያው ዘርፍ ለሙስሊሙ አለም ምሳሌ የሚሆን ስምምነት አድርገናል ብለዋል።
ስምምነቱ በመከላከያ እና በፀጥታ ዙሪያ ሰፊ ትብብርን የሚያካትት ሲሆን ሁለቱ ሀገራት ለውጭ ጥቃቶች በጋራ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው የጋራ መከላከያ ህግ ያካተተ ነው።
ይህ የጋራ ስምምነት በተለይ እስራኤል በኳታር ላይ በቅርቡ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ ክልላዊ ምላሽ ለመስጠት ለሚወሰደው እርምጃ እንደጅማሮ የሚታይ ነው።
እንደ ሳዑዲ አረቢያ እና ፓኪስታን ያሉ ሀገራት ነፃ የጸጥታ ትብብር እንዲፈጥሩ ያነሳሳው በአለም መንግስት እና ሃይሎች በሚሰጠው የደህንነት ዋስትና ላይ የመካከለኛው ምስራቅ መሪዎች ተስፋ መቁረጣቸውን ያሳያል።
የፓኪስታን ጦር የሳዑዲ ጦርን በማሰልጠን ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲሆን በሳዑዲ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በተለይም በየመን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል።
በአንፃሩ ሳውዲ አረቢያ ፓኪስታንን በብድር እና በፋይናንሺያል ፍላጎቶች ከፍተኛ ድጋፍ ታደርጋለች።
ይህን ስምምነት የሚለየው የረዥም ጊዜ ግንኙነቱን ወደ ተደራጀ እና አስገዳጅ እና ቁርጠኛ ወደሆነ መደበኛ ትብብር የተሸጋገረ መሆኑ ነው።
ሁለቱንም ሀገራት ከህንድ፣ እስራኤል እና ኢራን ሊደርሱ ከሚችሉ ስጋቶች ጋር በስትራቴጂያዊ መንገድ በጋራ ለመከላከልን ያካትታል።
ስምምነቱ በይፋ ቢታወቅም ዝርዝር ድንጋጌዎቹ ግን ለጊዜው በሚስጥር ተይዘዋል።
ስምምነቱ የፓኪስታንን የኒውክሌር አቅምን ይጨምራልን የሚለው ጥያቄ ግልጽ ባይሆንም የኒውክሌር አቅምንም የሚያካትት ከሆነ ክልላዊ አንድምታው ጥልቅ ሊሆን ይችላል።
ይህም በመካከለኛው ምስራቅ እና በደቡብ እስያ ያለውን የሃይል ሚዛኑን ሊቀርጽ ይችላል።
በተለይም የእስራኤልን መስፋፋት ሊቀለብሰው ይችላል።
በአጠቃላይ ስምምነቱ እስራኤል በኳታር ላይ ጥቃት በሰነዘረችበት እና በጋዛ የጀመረችው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት መደረጉ የመካከለኛው ምስራቅ መሪዎች ትልቅ መልእክት ነው።
ምናልባትም እስራኤል ጥቃት ብታደርስ ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት ወይም ለጦርነት ዝግጅትም ሊሆን ይችላል ተብሏል።
በውብሸት ደርብ