30/07/2026
ለምድራችን በረከት፣ ለዘላቂ ዕድገታችን አስተማማኝ መሰረት! አረንጓዴ አሻራ ለትውልዱ ተስፋን የምንተክልበት ታሪካዊ ሁነት!
ፓርቲያችን ያስቀመጠው በሀገራዊ አቅም ላይ መሰረትን ያደረገ የዘላቂ ዕድገት አቅጣጫ እውን እንዲሆን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የሀገራችንን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር፣ የደን መመናመንን በመግታት ለመጪው ትውልድ የለመለመች ኢትዮጵያን ለማሻገር ወሳኝ ነው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለምርታማነት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
የከርሰ ምድር ውሃ እንዲሞላ በማድረግ የውሃ ምንጮች እንዳይደርቁም ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ አረንጓዴ አሻራ የተለያዩ እንስሳትና እፅዋት እንዲሁም አዕዋፋት እንዳይጠፉና ወደ ሌሎች ሀገራትም እንዳይሰደዱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለብዝሀ ህይወት መጠበቅም ዋስትና ይሰጣል፡፡
የዝናብ ስርጭትን በማስተካከል ድርቅና እሱን ተከትሎ የሚመጣውን የምርታማነት ችግር ለማስወገድም አረንጓዴ አሻራ ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡
የደን ውጤቶች የበርካታ ሀገራት ኢንዱስትሪዎችም የጀርባ አጥንት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያም የአየር ንብረቷን ከማረጋገጥ ባሻገር ለተለያዩ የፈርኒቸር ምርቶች አስተማማኝ ግብዓት እንዲኖራት ስለሚያስችል ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ያነቃቃል፡፡
የክቡር ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ኢኒሸቲቭ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብራችን ለምግብነት የሚያገለግሉ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲተከሉ በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ርብርብም ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል፡፡
ሀገራችን በተለይም በቀንድ ከብት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፍ በመሆኗ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራማችን በእንስሳት መኖ ላይ የሚያጋጥመውን ሰፋ ያለ ችግር ለማቃለልም የማይተካ ሚና ያበረክታል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሳሰሉ ግድቦችን እየገነባች የታዳሽ ሀይል አቅርቦቷን በእጅጉ እያስፋፋች በመሆኑ ታላላቅ ግድቦቻችን የተመጣጠነ ውሀ እንዲኖራቸው በማድረጉ በኩልም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አስተማማኝ ዋስትና ነው፡፡
ለመዲናችን አዲስ አበበባ አንፀባራቂ ዕድገት ጉልህ ሚና እያበረከተ ለሚገኘው የቱሪዝን ዘርፍም መርሀ ግብሩ ትልቅ አቅም መፍጠሩን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ሀገር አቀፍ የህዝብ ተሳትፎን በማሳደግ ህዝባችን በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ስሜት ለጋራ ልማት በአብሮነት እንዲነሳ በማድረግ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ማህበራዊ መስተጋብርን ከፍ አድርጓል፡፡
ተዘርዝረው ከማያልቁ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎቹ ባሻገር በዲፕሎማሲው መስክም የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነት አሳድጓል፡፡ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት መዛባት መኖሩን በማስረዳት መተባበር እንደሚገባ ከመጠየቅ ወጥታ አንገቷን ቀና አድርጋ መሞገት የምትችልበትን ተጨባጭ ድል አስመዝግባለች፡፡ ሚሊዮኖችን በማሳተፍ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል የቻለችው ኢትዮጵያ ለምድራችን ልምላሜ፣ ለመጪው ትውልድ ብሩህ ተስፋ በታሪክ ሲዘከር የሚኖር አሻራዋን እያሳረፈች ትገኛለች፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት