09/05/2023
✝️✝️✝️"በስመ አብ ወወልድ ወመንስፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!"
እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!
👉👉👉 እያቄም ወሃና ወለዱ ሰማየ፣
ወሰማዮሙኒ አስረቀት ጸሐየ።👈👈👈
መንፈሳዊ ግጥም
የግጥሙ ርዕስ ፡ #"ቅኔ_ልቀኝልሽ"
ልጀምር መወድስ ልጀምር ምስጋና፣
ታስበሽ ለኖርሽው በእግዚአብሔር ሕሊና።
ቀዳሚዊው አዳም ከእግዚአብሔር ተጣልቶ፣
ወረደ ወደ ምድር አንቺን አነግቦ።
ወለድሽለትና ዳግማዊውን አዳም፣
አውጥተሽ ከአሮንቃ አኖርሽው በለምለም።
የአቤል ደግነት የሴት ቸርነቱ፣
አንቺ ነሽ ምስጢሩ ለላሜህ እረፍቱ።
ንፂህት መስታወት የፍጥረታት መልክ፣
ከርከቤደል ነሽ ወላድተ አምላክ።
አንቺ የኖህ ርግብ የማቱሳላ ዕድሜ፣
እፀ ሳቤቃችን ልቀኝልሽ ቅኔ።
የሰሎሞን አትሮንስ የኤልሳ ማሰሮ
ፍጹም ላይመለስ ጠፋልን እሮሮ።
ይጠለሉብሻል የሰው ልጅ ከወጀብ
ከጎፈር እንጨት ኖህ በሰራው መርከብ፣
ኖህ ከነልጆቹ ከንፍር ወጣና፣
ሀሴት አደረገ በልቡ ተፅናና፣
ድንቅ ምልክት በሰማይ አየና።
የሕይወት መናን የያዘች ደመና፣
አመተ ምህረት ሊገባ ሲል ገና፣
ብቅ አለች በምስራቅ ጥምን ልታረካ።
የዘላለም ምግብ የያዘች ደመና፣
ሰማይን ወለዱ ኢያቄም ወሐና።
አማናዊ ዝናብ ከድንግል ዘነበ፣
የደረቀችን ነፍስ በፍቅሩ አጠገበ።
በኃጢያት ለሚኖር በድቅድቅ ጨለማ፣
ድህነት ተጀመረ ምስራች ተሰማ፣
መጣ የድኅነት ድምፅ ከላይ ከራማ።
ኃያላን መላእክት የሚያጫውቱሽ፣
ምድራዊ ጎረምሶች የማይጎበኙሽ፣
የሕይወቴ ምስጢር ድንግል ልዩ ነሽ።
የሰው ልጅ በሙሉ በኃጢያት ሲኖር፣
መጣችለትና ታቦተ ዘዶር፣
አውጥታ አኖረችው በገነት ምድር።
ከሰው ልጅ ራቀ ጥንተ አብሶ ጠፋ፤
ንፂህት በሆነችው በማክሰኞ እርሻ።
የምድር አርያም በሕይወቷ አብባ፣
ተራራው እፅዋቱ ሆኑልን እንጀራ።
ከአርያም ይልቅ ይረዝማል ስፋቱ፣
ማሕፀነ ድንግል የአምላክ ዙፋኑ።
እናትም ድንግልም ሙሉ በክልኤ፣
ይደንቃል ግሩም ነው ልቀኝልሽ ቅኔ።
ተነግሮ አያበቃም አምላክ የሰራልሽ፣
ድንግል ሁነሽ ሳለ እንደት ህፃን ወለድሽ።
ሰሜኑን ደቡቡን ምሥራቅ ምዕራቡን
ፈለገ አሻተተ አምላክ ማደርያውን
በረዶና እሳት አንድ ላይ ወረዱ፣
ስጋና መለኮት በድንግል አንድ ሆኑ።
ሱራፌል ኪሩቤል ይሸፋፈናሉ፣
በእሳተ መለኮት እንዳይቃጠሉ።
ይህን ሁሉ አይተው እነ አባ ጊዮርጊስ፣
እነ ቅዱስ ኤፍሬም ቅኔ ቢቀኙልሽ፣
እረ በምን በምን እንመስልሽ ቢሉሽ፣
ተቃጥለው ነደው ነው በእናትነት ፍቅርሽ።
የአብ ሙሽራ የወልድ ወላድቱ፣
የመንፈስ ቅዱስ ፅርሐ ቤቱ፣
ቅኔ ልቀኝልሽ እንደ ሊቃውንቱ።
መልካም በዓል🙏🙏🙏
"ልደትሽ ልደታችን ነው!"
ገጣሚ፦ ዲ/ን ኃይለ ማርያም